ደስታን ከየት ነው ምናገኘው

ያፌት ከፈለኝ (ካውንስሊንግ ሳይኮሎጂስት)

አብርሆት ሳይኮሎጅካል መአከል

 

 “የሰው ልጅ መብላት እና መጠጣት ያውቃል  ማጣጣም የሚያውቁ ግን ጥቂቶች ናቸው” 

የምትለው ሰዎች ከክርስቶስ ልደት በፊት ጀምሮ ይጠቀምዋት የነበረ አባባል ነው፡፡ 

የሰው ልጅ በየዘመኑ ኑሮን ለማሸነፍ ብዙ ብልሀትን ፈጥሯል፡፡ ከአደን ወደ እርሻ ብሎም ማብሰል፣ ከዋሻ ወደ ቤት  ብሎም ሰማይ ጠቀስ ሀንጻ፣ ከስዕል ወደ ስነ ፅሁፍ ብሎም የማሽን ቁዋንቌን እያገኘ ከትውልድ ወደ ትውልድ የተሻለ ሕይወትን ለመኖር ፍለጋ ሁሉም በየዘመኑ ያገኘውን እያበረከተ ግብአትን እያስተላለፈ ብሎም በቀመር፣ በስሌት፣ በልኬት እያለ ሳይንስን ወልዶ ዛሬ ያለንበትን ነጥብ ላይ ደርሰናል፡፡ ሳይንስም ቅርንጫፍ ዘርግቶ የሙያ ዘርፎችም አፍርቶ ከተረከበው የተሻለ ህይወት ላይ ለማድረስ ብሎም ለቀጣዩ ለማስተላለፍ ይዳክራል፡፡

ገና ሳይንስ ሀ ብሎ አቡጦ ሲወጣ ለሰው ልጅ ኑሮ እና ህይወት የተሻለ እና ትርጉም እንዲኖረው ለማድረግ እነሆ የምስራች ካላቸው የሙያ ዘርፎች አንዱ ሳይኮሎጂ ነው፡፡ ይህም ዘርፍ በመጀመሪያ ሰውኛን ለመረዳት እያደረ ደግሞ ሰውን ለመርዳት የሳይንስን ህግን አክብሮ እና አሟልቶ ዛሬ ከ57 በላይ ዘርፎችን አፍርቶ ከሰውም አልፎ እንስሳትን ጨምሮ ሲያጠና የተሻለ ሕይወት እንድንመራ ከተፈጥሮ ጋር አመቻችቶን ወይም ተፈጥሮን ከራሱ ጋር አስማምቶ የሳይንስ ዘዴን መሠረት አርጎ የሚሰራ አንጋፋ እና አንቱ የተባለለት የሙያ ዘርፍ ነው፡፡

ታዲያ በዚህ ዘርፍ ውስጥ ከሰው ልጅ በየዘመኑ የተሻለ የህይወት ጣዕምን ፍለጋ ከሚነሱለት ጥያቄዎች ውስጥ፡-

  1. በሰው ልጅ በሕይወት መንገድ ላይ ጤናማ እና ደስተኛ አርጎ የሚያቆየው ምንድን ነው? 
  2. የወደፊት ማንነታችን የተሻለ እና ደስተኛ አና ሕይወታችን ጣዕም እንዲኖረው ግዜአችንን እና ጉልበታችንን ምን ላይ ብንሰራ የተሻለ ይሆናል?

የሚሉት ከዘመን ዘመን ትውልድ ተሻጋሪ የሆኑ ጥያቄዎች ሆነው ለኛም ደርሰውናል፡፡ ይህንንም በጥናት ለመመለስ እየተሰራ ይገኛል፡፡ በ ሚሊኒያ ትውልዶች ላይ በተደረገ መጠይቅ የተገኘው፡-

ከሰማንያ በመቶ በላይ ገንዘብ እና ሀብት ማካበት ነው ሲሉ በተመሳሳይ እድሜ ላይ ያሉት ሌሎች ደግሞ ታዋቂና ዝነኛ ሰው መሆን ሊሰጥ ይችላል ብለው መልሰዋል፡፡

ወደፊት የተሻለ እና ደስተኛ ሕይወት እንዲኖረን ለማግኘት አሁን ቀን ከማታ እንቅልፍ እና እረፍት ቀንሰን የለፋን ከሆነ ነው የሚገኘው ብለው ብዙሀን አስቀምጠዋል፡፡ ታዲያ በዚህ ሙያ ውስጥ በሳይንሳዊ ጥናት እውነት ለሰው ልጅ ህይወት ሀሴት እና ደስታ፣ ጤናን ሊሰጠው ምን እንደሚችል በምን ማወቅ ይቻላል?

ይህን ጥያቄ ለመመለስ ብዙውን ጊዜ ከመረጥናቸው ሰዎች ሙሉ የሕይወታቸውን ዘመን ገፅታ ላይ የመረጡትን የአኗኗር ዘይቤ ተሞክሮ እና ከዛም ሆነው የተገኙትን ውጤት ለማጤን መረጃዎችን ለመሰብሰብ መሞከር ነበር፡፡ ይህንንም ለማግኘት ብቸኛው መንገድ ተሞክሮአቸውን በመጠየቅ እያስታወሱ እንዲነግሩን ነበር፡፡ የዚህ መረጃ መሰብሰቢያ ዘዴ ትልቁ ፈተና ደግሞ እነዚህ ተሳታፊዎች አብዛውን በመርሳት ወይንም ትውስታው ውስጥ ሳይታወቅ ፈጥሮ በመሙላት የጥናቱን አስተማማኝነት እና ልክነቱን ሲፈታተኑት ቆይተዋል፡፡ ታዲያ ምን ተሻለ? አትሉም

የሰውን ልጅ የሕይወት ዘመን ከጊዜ ፈልቅቀን እንደ ቪድዮ ክሊፕ ወደ ኋላ እና ወደ ፊት ማየት ቢቻልስ ኖሮ ?፣ መቼስ ምኞት እና ፈስ አይከለከል፡፡

እሚደንቀው ከወደ ምዕራቡ ከእውቁ ሀርቨርድ ዩኒቨርሲቲ የተሰማው የኔን ምኞት ተስተካካይ ይመስላል፡፡ በዚህ ስመጥር ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የተጠናው ጥናት እና ምርምር ምናልባትም በግል በሰው ሕይወት ዙሪያ ላይ ከተሰሩ ጥናቶች በአለም ደረጃ ለረጅም ጊዜ ያለማቋረጥ ከተከወኑት ውስጥ በመሪነት የተቀመጠ ነው፡፡

ይህ ጥናት በ724 ሰዎች ላይ ከወጣትነት ማለትም ከአስራዎቹ እድሜ ክልል ጀምሮ እስከ ጎልማሳነት እና እርጅና እድሜአቸው የቀጠለ ጥናት ነው፡፡ ጥናቱም ለሰባ አምስት (75) አመታት የዘለቀ ከመሆኑም በላይ አሁንም ጥናቱ የቀጠለ ሲሆን ከነዚህ ተሳታፊዎች ውስጥአሁን በሕይወት ካሉት 60ዎቹ ሰዎች ጋር እና 2000 ከሚጠጉ ከልጆች እና በ ልጅ ልጆታቸው ጥናቱ ውስጥ በማሳተፍ የቀጠለ ነው፡፡ 

ታዲያ በሳይንሱ ዘርፍ እንደዚህ ያሉ ጥናቶች እና ምርምሮች እጅግ ኤመንት ናቸው፡፡ መቼስ ለምን ብትሉ መልሱን ለመገመት አያዳግትም፡፡ በተለይ በዚህ የሙያ ዘርፍ እና ሌሎችም ጥናት ምርምሮች ብዙ ግዜ ወይ በበጀት እጥረት፣ በተመራማሪው ሞት ወይም የጥናት ለውጥ ፣ በጥናቱ ተሳታፊዎች ችግር እናም ሌላ ብዙ ብዙ ምክንያት ሲቋረጡ መስማት የተለመደ ነው፡፡

ይህ ጥናት ግን አንድም በተመራማሪዎቹ ተተኪ የትውልድ ቅብብሎሽ  ፅናት እና ቁርጠኝነት በሌላም እድል ተጨምሮበት እና ታክሎበት እዚህ ደርስዋል፡፡

ይህ የጥናት ሂደት የተጀመረው እ.ኤ.አ በ1938 ዓ.ም ሲሆን በጥናቱ የተሳተፉት 724 ሰዎች በሁለት ቡድን ተከፍለው የተሰበሰቡ ሲሆን አንደኛው ቡድን ከኮሌጅ መግባት የቻሉ ሲሆን ሁለተኛው ቡድን ደሞ እጅግ አነስተኛ ኢኮኖሚ ውስጥ እና በዘመኑ በጣም የተቸገሩ ከሚባለው የተውጣጡ ውስጥ የነበሩ ናቸው፡፡

በጥናቱ የተሳተፉት ሁለቱም ቡድን ውስጥ ያሉት ሁሉም በአስራ ቤት እድሜ ክልል ውስጥ የነበሩ ናቸው፡፡ በዚህ በ75 አመታት የጥናት ሂደት ውስጥ ተሳታፊዎቹ ወደ ጉልምስና (45ቱ) እድሜ ክልል ውስጥ ሲደርሱ አንዳንዶቹ የፋብሪካ ሰራተኞች፣ ጠበቆች፣ አናጢ፣ ሐኪም፣ ብሎም ከተሳታፊዎቹ አንድ የዩናይትድ ስቴት ፕሬዚዳንት አንዳንዶች ደግሞ የአልኮል እና የሌሎች ሱስ ተጠቂ ጥቂት ደሞ በ ስኪዞፈርነያ የተጠቁ ሲሆን በለውጡ ሂደት ውስጥም ከምንም ወይም ከታች ተነስተው እራሳቸውን ትልቅ ቦታ ያደረሱም አንዳሉ በተገላቢጦሽ ከላይ ወደታች ያሽቆለቆሉም ነበሩ፡፡

የሄ ጥናት በታታሪ ተመራማሪዎቹ ከሁሉም ተሳታፊዎች በቂ መረጃ በየአንዳንድ ሕይወት የተከሰተውንና ያለፉበትን ለመሰብሰብ ከእያንዳንዱ መኖሪያ ቤት በመሄድ ቃለ መጠይቅ በመውሰድ፣ የሕክምና መረጃ በመውሰድ፣ የደም ናሙና በመውሰድ፣ የአንጎላቸውን እና የአእምሮ ስራተ ሂደት በመፈተሻ ማሽን (MRI) በመመርመር፣ ልጆቻቸውን በማነጋገር፣ ከባለቤቶቻቸው ጋር ስለሚያሳስባቸው ነገሮች በሚወያዩበት ወቅት በቪድዮ በመቅረፅ ማስቀረት፣ (በሂደት ሚስቶታቸውን ሙሉ ለሙሉ ጥናቱ ውስጥ ተካተዋል) እና በሌሎችም መረጃ መሰብሰቢያ ዘዴ ተጠቅመው ከአስር ሺህ በላይ የሚያልፉ ሁሉን አቀፍ የመረጃ ሰነድ ተሰብስበዋል፡፡

በዚህ መረጃ መሰብሰብ ሂደት ውስጥ በሁለተኛው ቡድን ውስጥ የነበሩት ማለትም እጅግ አነስተኛ ኢኮኖሚ ከሚያገኙት አብዛኞቹ ተሳታፊዎች ይጠየቁ የነበረው ጥያቄ “የኔ ህይወት የዚህን ያህል ለመጠናት የሚስብ ነገር ምኑ ነው? ምንስ አለው” የሚል ነበር፡፡ ከሚደንቀው ከቡድን አንድ ከነበሩት ማንም ይህንን ጥያቄ ፈፅሞ ጠይቆ አያቁም ነበር፡፡

ታዲያ ከዚህ አንድ ምዕተ አመት ሊሞላ ጥቂት እድሜ ከቀረው ጥናት ምን ተገኘ? በተሳታፊዎቹ ሙሉ የሕይወት ሂደታቸው ውስጥ ከወጣትነት እስከ እርጅና ድረስ በሳይንሳዊ ዘዴ ከተቀዳው ምንስ ያስተምረናል?

እንግዲህ በሳይንሳዊ ሂደት ከተረጋገጠው አንዱ ሀብት ማካበት፣ ታዋቂ ወይም ዝነኛ ሰው መሆን አልያም እጅግ በርትቶ መስራት ደስታን አይሰጥም!!! የሕይወት ጣዕም እንድናጣጥማት አይፈቀድልንም ማለቱ ነው እንግዲህ፡፡

ከሚሊንያ በሚባሉት ትውልድ ላይ በተሰበሰበ መረጃ ለደስታ እና ለጥሩ ህይወት መሠረታዊ ብለው ያስቀመጡት ሀብት እና ዝነኝነት እንዳሉት በዚህም ጥናት የተሳተፉት በ2ኛ ያለም ጦርነት አካባቢ ጊዜ በተመሳሳይ እድሜ ተመሳሳይ መረጃ ነበር የተሰበሰበው፡፡

 እርግጥ ከክርስቶስ ልደት በፊት ገና ሳይንስ ሀ ሳይል አርስቶትልም “መልካም ሕይወት ደስታን የምንመራው በራሱ እንጂ በሌላ ነገር አስታከን አይደለም… የሰው ልጅ የሚሻው ክብርም ሆነ አዋቂነት ትርፋቸው ደስታ ነው” “ጥበብ ከፒላጦስ” ከሚለው ካነበብኩት ትዝ አለኝ፡፡

እና ምንድነው ጥናቱ ደስታን ከየት ነው ምናገኘው የሚለው?

ከዚህ ከ75 ዓመት በላይ በፈጀ ጥናት የተገኘው ቁልጭ እና ግልጥ ያለው መልስ ጤናማና ደስተኛ አርጎ የሚያቆየን ጥሩ ግንኙነት (Good relationship) ነው፡፡ ከምን ጋር አትሉም?፡፡ ትልልቅ ሶስት አንኳር ነጥቦችን አስቀምጧል፡፡

1ኛው ግንኙነታችን ከማህበራዊ ጋር ያለው መስተጋብር ሲሆን ከተሳታፊዎቹ ከተሰበሰበው መረጃ ውስጥ ጥሩ የሚባል ማህበራዊ ግንኙነት ሕይወት ከቤተሰብ፣ ከጉደኛ፣ ከማህበረሰቡ ጋር ያላቸው ደስተኞች ከመሆናቸውም በላይ በተጨማሪ በአካል፣ በጤንነት እና ከተመዘገበው የእድሜ ጣሪያ በመኖር የተሻለ ሆነው ተገኝተዋል፡፡

በአንጻሩ ግለኛ እና ብቸኛ ሆነው ከተመዘገቡት ተሳታፊዎች በሕይወታቸው የሚያጣጥሙት ደስታ እጅግ ያነሰ ነበር፡፡ ከዚያም በላይ ግን በተለይ ወደ ጎልማሳነት እድሜዎቹ ውስጥ በሚገቡበት ወቅት የአካላዊ ጤናቸው ላይ እና የአንጎል ስርአተ መስተጋብር ላይም አሉታዊ ተፅኖ አሳድረዋል፡፡

እንግዲህ ከሚያሳዝነው ነገር እንደ ዓለም አቀፍ ጤና ድርጅት በቅርቡ ካወጣው መረጃ ውስጥ በአለማችን ከ5 ሰው ውስጥ አንድ ብቸኛነትን ሪፓርት አድርግዋል ይላል፡፡

2ኛው አንኩዋር ነጥብ ከጥናቱ የተገኘውም በብዙ ቤተሰብ ወይም ጓደኛ ስላለን ወይም ታማኝ የትዳር አጋር ስላለን ሳይሆን ትልቁ ቁም ነገር ያለው በመሀከላችን ያለው የግንኙነቶችን ጥራት (relationship quality) ላይ የወደቀ ነው፡፡ ስለዚህም በአብዛኛው በግጭቶች እና ባለመግባባቶች በስራ፣ በትዳር፣ በትምህርት በሌሎችም ከተከበበ የሚታወከው ሳይኮሎጂካል ጤናችን ብቻ ሳይሆን አካላዊ ጤንነትም ላይ አሉታዊ ተፅኖ ያድርበታል ማለት ነው፡፡

ይህንን ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ከተጠቀሙት የምርምር ዘዴዎች መካከል፡-

በጥናቱ ሙሉ ሂደት ውስጥ ተሳታፊ ከነበሩት መካከል በሰማንያ እድሜ ክልል ውስጥ የደረሱትን መረጃ በመያዝ እነዚሁ ሰዎች በጎልማሳነት (ከ 45 በላይ) እድሜ በነበሩበት ሲመሳከር የወደፊት ጤንነታቸውን በተሻለ የተነብይ የነበረው በደማቸው ውስጥ ያለው ኮሌስትሮል አልነበረም፡፡ የሆነው ግን በቀጥታ ተያያዥ ሆኖ የተገኘው ግን የነበራቸው የግንኙነት ጥራት (relationship quality) ነበር፡፡ 

ከተመዛገቡት መረጃዎቹ ውስጥ አንዱ ደስተኛ ከተባሉት ውስጥ በሰማንያ እድሜ ክልል ውስጥ ከገቡ በኋላ አካላዊ ህመም በሚሰማቸው ወቅት ያሉበት የደስታ መጠን ሲለካ የነበረበት ላይ ወይም ለውጥ ሳያሳይ እዛው ደስታ ደረጃ ላይ ነበሩ፡፡ በተፃራሪው ደስተኛ ካልነበሩት ውስጥ በተመሳሳይ እድሜ (80ዎቹ) ውስጥ ሆነው አካላዊ ሕመም ሲያጋጥማቸው በተጋነነ መልኩ ስሜታቸው ላይ ከፍተኛ ተፅኖ አድርጎ ታይቷል፡፡

3ኛው ትልቁ አንኳር ነጥብ ጥራት ያለው ግንኙነት የአካላችን ጤንነት ብቻ የጠበቀ ሳይሆን የአንጎላችንንና የእምሯችን ስርዓት-ትግበራም ላይ ጭምር ነበር፡፡ ከዚህም ውስጥ ጥራት ያለው ጥሩ ግንኙነት ውስጥ ካሉት– በችግር በሚያጋጥሟቸው ወቅት ወይም ሰው እንዲደርስልን በሚያስፈልገን ወቅት በርግጠኝነት የደርሱልናል ብለው የሚያምኑት ሰዎች አሉን ያሉት በጥናቱ ውስጥ ከተሳተፉት የላቀ የማስታወስ ክህሎት አስመዝግበዋል፡፡ በተቃራኒው የለንም ያሉት እጅግ ያነሰ ሆኖ ተመዝግብዋል፡፡

ይህም ጤናማ የሆነ ጥሩ ግንኙነት ማለት ከጥል ወይም ከአለመግባባት የፀዳ ብቻ ማለት ሳይሆን ስንቸገር ወይም ሰው ሲያስፈልገን የደርስልኛል ብለን አመኔታ የጣልንበት ግንኙነት መመስረት መቻላችን ነው ማለት ነው እንግዲህ፡፡

ስለዚህ የዚህ ጥናት መልዕክት ጥራት ያለው ጥሩ ግንኙነት የጤናችንና የደስታችን ብሎም የሕይወታችን የጣዕም ምንጭ ነው፡፡ ይህንንም ክህሎት ማካበት የሕይወት ትልቁ ጥበብ ነው፡፡

ለምንድን ነው እክሎች ሲያጋጥሙን ሁሌ ምንፈልገው እንደ ፈጣን ጎሚስታ ቶሎ ጊዚያዊ ማስተካከያ ወይም ቀዳዳውን ለጥፎ ቶሎ ለመሄድ ፈረንጆቹ “Quick Fix” የሚሉትን የምንፈልገው?

እርግጥ ነው ግንኙነት መመስረት ውጣውረድ አለው፣ አንዳንዴም ይወሳሰባል ከዚያም በላይ ማለቅያ የሌለው የእድሜ ልክ ዝርጋታ ነው፡፡ ይህም ከ75 ዓመት በላይ የፈጀው ጥናት ያሳየው ከተሳታፊዎቹ ጡረታ ሲወጡ የስራ ቦታ ጓደኞቻቸውን በጡረታ ዘመናቸው ያስቀጠሉትና የሳተፉት ከፍተኛ ደስታን አስመዝግበዋል፡፡

 እናንተስ ይህን የምታነቡት ምናልባት እድሜያችሁ አንበል 18 ወይ 25 ወይ 35 ወይ 50ዎቹ የግንኙነታችን ጥራት ከስራችን ወይም ትምህርት፣ ከጓደኛ ወይም ከትዳር አጋራችን፣ ከቤተሰብ፣ ከተፈጥሮ፣ ከመንፈሳዊነት፣ከማህበረሰቡ፣ ከራሳችን በጠቅላላ በዙርያችን ካሉ ነገሮች ጋር ያለን የግንኙነት ጥራቱ ምን ይመስላል? እሚለውን የቤት ስራ ለናንተ እየተውኩ … ለእኔ ደሞ ደስታ እንዴት እንደሚለካ እና ለማግኘት ክህሎቶቹን እንዴት እናሳድግ የሚለውን ለቀጣይ የቤት ስራ እወስዳለሁ፡፡ በጥቅስ እንደ ጀመርኩ በጥቅስ ልዝጋው እንግዲህ፡፡

 

“ሰው ከሐሳብ እና ስቃይን ማምለጥ እንጂ ደስታን አይፈልጋትም”    ሶቅራጠስ 

 

የጤና ወግ 

ጠቃሚ እና የተረጋገጠ መረጃ ለጤናዎ ።

የጤና ወግን በነዚህ ሊንኮች መከታትል ይችላሉ ።

https://linktr.ee/Yetena_Weg