ዶ/ር ዳዊት ወርቁ፣ የማህፀን እና ፅንስ ስፔሻሊሰት፣ የማህፀን ካንሰር ሰብ-ስፔሻሊሰት
- የኮቪድ -19 በሽታ ምንድን ነው ?
- እንደ አለም ጤና ድርጅት መሰረት ኮቪድ -19 የሚባለው በሽታ በ SARS-COV-2 (ኮሮና ቫይረስ) የሚከሰት ነው፡፡ የኮሮና ቫይረስ ከሰው ወደ ሰው ይተላለፋል፡፡ አንድ ግለሰብ በቫይረሱ ከተያዘ በኃላ እስከ 14 ቀን ባለው ጊዜ ውስጥ ምልክት ሊያሳይ/ልታሳይ ይችላል/ትችላለች፡፡ በአማካኝ ሲታይ ከ 4-5 ባሉ ቀኖች ውስጥ የበሽታው ምልክት ሊታይ ይችላል፡፡
2. የኮቪድ -19 በሽታ ምልክቶች ምንድን ናቸው ?
- በብዛት የሚታዩት የኮቪድ 19- በሽታ ምልክቶች ትኩሳት፤ ደረቅ ሳል እና የትንፋሽ መቆራረጥ ናቸው፡፡
3. የካንሰር በሽታ በኮሮና ቫይረስ የመያዝ እድልን ይጨምራል ?
- እስከ አሁን ባሉ መረጃዎች የካንሰር በሽታ በኮሮና ቫይረስ የመያዝ እድልን አይጨምረውም ሆኖም የካንሰር ታማሚ በኮሮና ቫይረስ ከተያዘ የሚከሰተው የበሽታ ደረጃ ከፍተኛ ሊሆን ይችላል፡፡
4. የካንሰር በሽታ በኮቪድ -19 ምክንያት የሚከሰተውን የህመም ደረጃ ከፍተኛ ያደርገዋል ?
- የካንሰር በሽታ እና የካንሰር ህክምና መንገዶች የሰውነት የመከላከል አቅምን ይቀንሱታል፡፡ በዚህም ምክንያት የኮቪድ -19 በሽታ በካንሰር ታማሚዎች ላይ ሲከሰት የበሽታው ደረጃ የከፋ ይሆናል፡፡ ይህም በበሽታው ምክንያት የመሞት እድልን ከፍ ያደርገዋል፡፡
5. የካንሰር ታማሚ በኮሮና ቫይረስ የመያዝ እድልን እንዴት መቀነስ ይችላል/ትችላለች ?
- እጅን በሳሙናና በውሀ(ቢያንስ ለሃያ ሰኮንድ ያህል) ደጋግሞ መታጠብ። በተለይ ወደ ስራ ቦታ ወይም ወደ ቤት በሚገባበት ጊዜ እጅን በሳሙና መታጠብ ። ሳሙናና ውሀ በማይኖርበት ጊዜ ከአልኮል በተዘጋጀ የእጅ ንጽህና መጠበቂያ (ሳኒታይዘር) መጠቀም፤
- ንጹህ ባልሆነ እጅ አይን፣ አፍንጫና አፍን አለመንካት፤
- በምታስልበት ወይም በምታስነጥስበት ጊዜ አፍና አፍንጫን በ ክንድ ወይም በመሐረብ መሸፈን፤ በሳል ወይም በማስነጠስ ጊዜ በእጅ አለመሸፈን።
- የኮሮና ቫይረስ ምልክት ከሚያሳዩ ሰዎች በሁለት የአዋቂ እርምጃ ውስጥ አለመሆን፤
- ከተቻለ ስራን ቤት ውስጥ ሆኖ መስራት፤ ማህበረሰባዊ ግንኙነቶችን መቀነስ፤ ህዝብ በሚበዛባቸው ቦታዎች አለመሆን፤ ወደ ቤት የሚመጡ እንግዶችን፣ ጓደኞችንና ቤተዘመዶችን መቀነስ፤
- በተጨማሪም አጠቃላይ ጤናን ሁኔታ ለማጎልበት የተመጣጠነ ምግብ መመገብ በቂ እንቅልፍ ማግኘት ጠቀሜታው አለው፡፡
6. የካንሰር መድሀኒት (Chemotherapy) ወይንም የጨረር ህክምና (Radiotherapy) በኮቪድ -19 ምክንያት የሚከሰተውን የህመም ደረጃ ከፍተኛ ያደርገዋል?
- መረጃዎች እንደሚያሳዩት የካሰር በሽታን ለማከም የካንሰር መድሀኒት (Chemotherapy) ወይም የጨረር ህክምና የወሰዱ የካሰር ታማሚዎች ከባድ ደረጃ በሆነ የኮቪድ -19 በሽታ የመያዝ እድላቸው ከፍ ያለ ነው፡፡ በተለይም የካንሰር ህክምናውን በወሰዱ ከ 1 ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ በኮሮና ቫይረስ ከተጠቁ ከፍተኛ ደረጃ በሆነ የኮቪድ በሽታ በመያዝ እድላቸው ይጨምረዋል፡፡
7. በኮቪድ -19 የተጠቃ የካንሰር ታማሚ የካንሰር ህክምናውን መቼ መጀመር ይኖርበታል ?
- በኮቪድ -19 የተጠቃ የካንሰር ታማሚ የካሰር ህክምና የሚጀምርበትን ጊዜ ከሚወስኑት ሁኔታዎች መካከል የካንሰሩ አይነት፤ የህመሙ ደረጃ እንዲሁም ሊሰጥ የታቀደው የህክምና መንገድ ( የካሰር መድሀኒት ፤ የጨረር ህክምና ፤ ኦፕሬሽ) ይገኙበታል፡፡
- የካሰር ህክምናውን መውሰድ አስቸኳይ ሆኖ በሚገኝበት ጊዜ ከኮቪድ -19 በሽታ ምልክቶች ቢያንስ ለ 72 ሰዓት ነፃ መሆንንና በላብራቶሪ ምርመራ ከቫይረሱ ነፃ መሆንን ይጠይቃል፡፡
- ባጠቃላይ የካሰር ህክምና የሚጀመርበትን ጊዜ ለመወሰን ታማሚው ከሀኪሙ ጋር መወያየት ይኖርበታል፡፡
ምንጮች
1. CDC. [Online] 2020. https://www.cdc.gov/coronavirus/2019-ncov/index.html.
2. Kenneth McIntosh, MD. Coronavirus disease 2019 (COVID-19). s.l. : UpToDate, 2020.
3. COVID 19: Elective Case Triage Guidelines for Surgical Care. surgeons, American collage of. March 27, 2020.
4. Cancer patients in SARS-CoV-2 infection: a nationwide analysis in China. s.l. : The lancet oncology, March 2020, Vol. 21.
የጤና ወግ
በመረጃ የተመሰረተ ሕክምና ብቻ ።
………………………………………………………………………………………………………………………..
ይህ የጤና ወግ ድረ ገፅ ነው።
ስለ ጤንነታችሁ ማወቅ የምትፈልጉትን መረጃ የምታገኙበት ፣ በህክምና ባለሙያዎች የሚዘጋጅ የመረጃ ምንጭ ነው።
ሁልግዜም ከሀኪማችሁ ተማከሩ፣ ተጨማሪ መረጃ ከፈለጋችሁ የኛን ድረ ገፅ ጎብኙ።
በጥናት የተደገፈ መረጃ ብቻ እናቀርባለን።
የህክምና ባለሙያዎች ለህሙማኖቻችሁ የሚሆን የሚነበብ መረጃ ከፈለጋችሁ ይህን ግፅ ጠቁሟቸው። ህሙማኖቻችሁ እንዲያውቁት የምትፈልጉትን ነገር መረጃ ጠቅሳችሁ ፃፉልን፣ ስምችሁን ጠቅሰን እናወጣለን። የህክምና ተማሪዎች እንዲጽፉ እናበረታታለን።
በተጨማሪም በጤና ወግ ፖድካስት፣ በ ዩትዩብ ፣በ ትዊተር ፣ በ ፌስቡክ ፣ በቴሌግራም የተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ ገፆቻችን ታገኙናላችሁ