written by –  ዶ/ር ሰምሀል ሃይሉ onco pathology center ጠቅላላ ሐኪም

Reviewed by – Dr. Kirubel Girmay( Final year Psychiatry resident at Tikur Anbessa Specialized Hospital)

 

 

ዮጋ ከህንድ የመነጨ ጥንታዊ ልምምድ ሲሆን አእምሯዊ እና መንፈሳዊ ሰላምን የሚሰጥ ተግባር ነው ። “ዮጋ” ለሚለው ቃል  ተቀራራቢ ትርጉሙ  “መዋሃድ”   ሲሆን ይህም የአካል እና የአዕምሮ አንድነትን የሚያመላክት ነው። ይህ ተግባር  ከ3000 አመት በላይ የቆየ ሲሆን በአብዛኛው በምስራቁ የዓለም ክፍል ላይ ሲተገበር የቆየ ሲሆን ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በምዕራቡ የዓለም ክፍል (  በአሜሪካ ብሄራዊ የህክምና ተቋም)  ሁለገብ ህክምና (ሆሊስቲክ ሜዲሲን)  ዘርፍ  ከሌሎች ህክምናዎች ጋር አብሮ የሚሰጥ ተጨማሪ ህክምና ተደርጎ ተወስዷል።

የዮጋ ዋና አላማ አካላዊ፣  አእምሯዊ እንዲሁም መንፈሳዊ ጤንነትን ማዳበር ነው። በተጨማሪ  ከራስ ጋር ያለን ሰላም እና መግባባት ከፍ በማድረጉ በመንፈሳዊው የኤዢያ ማህበረሰብ ውስጥ ተመራጭ ያደርገዋል።

የዮጋ ስነልቦናዊ ጥቅም በጥናቶች የተደገፈ ነው፤ አንድ ጥናት በአንጎል ውስጥ የሚገኙ ንጥረነገሮችን በማመጣጠን (የሴሮቶኒን መጠንን ከፍ በማድረግ እና ሞኖ አማይን ኦክዴዝ የሚባለው ኢንዛይምን መጠን በመቀነስ) የድባቴ ህመምን የማሻሻል አቅም ያለው ሲሆን እንደተጓዳኝ ህክምና በአሁኑ ሰዓት እየታዘዘ ነው።

ዮጋ ከመነፈሳዊ ጥቅሙ በተጨማሪ አተነፋፈስን ማስተካከል፣ የሰውነት መጋጣጠሚያ የመሳሳብ አቅምን እንዲሁም የአካል ጥንካሬን  የማሻሻል ጥቅም ስላለው የተለያዩ የጡንቻ እና የመገጣጠሚያ ህመሞችን ለማስታገስ ይረዳል። ከዚህ በተጨማሪ የስነ-ልቦና ጤናን የማሻሻል አቅሙ እንደ ጭንቀት እና ድባቴ ላሉ የአእምሮ ጤና እክሎች ከመድሃኒት እና ከንግግር ህክምና በተጓዳኝነት የሚወሰድ ጥሩ  የህክምና አማራጭ ያደርገዋል።

ዮጋ በሁሉም ዕድሜ እና የአካል ብቃት ደረጃ ላሉ ሰዎች ተስማሚ ነው። ጀማሪዎች መሰረታዊ አቀማመጦችን እና ቴክኒኮችን ለመማር  ለጀማሪ ተስማሚ በሆኑ ክፍሎች መጀመር ይችላሉ።

ዮጋ የተለያዩ ጥቅሞች አሉት። ዮጋ ጠቃሚ ሊሆን ከሚችልባቸው ዋና ዋና መንገዶች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል

አካላዊ ጥቅሞች

– ሚዛንን እና የጡንቻ ጥንካሬን ያሻሽላል

– የልብና የደም ዝውውር ጤንነት ያሻሽላል

– እንደ ጀርባ ህመም ያለ  ህመምን ለማስታገስ ይረዳል

– ጤናማ የሰውነት ክብደትን ለመጠበቅ ይረዳል

የአእምሮ እና ስነ-ልቦናዊ ጥቅሞች

– ጭንቀትን  እና  የመንፈስ ጭንቀትን ይቀንሳል

– ትኩረትን  ያሻሽላል

– የእንቅልፍ ጥራትን ከፍ ያደርጋል

 

በጥቅሉ ሲታይ ዮጋ አካላዊ ፣ አእምሯዊ  እና መንፈሳዊ ጤናን የሚያዳብር ሁለገብ ተግባር ነው ።