ህሊና ከበረ (በአ.አ.ዩ ህ/ጤ/ሳ/ኮ የህክምና ተማሪ- C2 )
መግቢያ
አያድርሰውና፣ አንድ ሰው ሀዘን፣ በተለይም በቤተሰብ አባል ሞት ሳቢያ የሚመጣ ሀዘን ቢደርስበት ከሁኔታው ጋር በቀጥታ ተያይዘው ከሚመጡ ችግሮች ባሻገር ኢኮኖሚያዊና ስነ-ልቦናዊ ቀውስ ውስጥ እንዳይገባ የዕድር አባል መሆን ሊመርጥ ይችላል፡፡ ዕድርተኞቹም ምናልባት ነገ በራሳቸው ላይ ያልታሰበ ሀዘን ቢያጋጥም የሚረዷቸው ጎረቤቶች እንዳሉ ዋስትና ስላላቸው በሚያደርጉት ድጋፍ ምሬትና ቁጭት አይሰማቸውም፡፡ እንዲያውም ያለፈውን ሰው ህይወት መመለስ ባይችሉ እንኳን ለጎረቤታቸው በሚሰጡት ድጋፍና በሚፈጥሩት መረጋጋት እርካታ ይሰማቸዋል፡፡
ዕድር እነዚህን መርሆዎች ስለሚያጎላቸው በባህላችንና በተቋሙ ኩራት ሊሰማን እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ ውድ አንባቢ፣ እስቲ አንድ እርምጃ ወደኋላ መለስ እንበል፡፡ ይህ መተባበርና እርዳታ የሰው ህይወት ከማለፉ በፊት ቢሆን የሚኖረውን አስተዋፅኦ አስተውለዋል? ይህንን ጥያቄ ተንተርሶ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ጤና ሚኒስቴር እ.ኤ.አ. 2011 ጀምሮ ማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድንን መሞከሪያ ዕቅዶች በመንደፍ ጥናት ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡ በቅርቡ ደግሞ በመላው ኢትዮጲያ ተግባራዊ ለማድረግ እየሰራ ይገኛል ፡፡
ለመሆኑ ማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድን (ማአጤመ) ምንድን ነው?
ማአጤመ መደበኛ ባልሆነ ክፍለ-ኢኮኖሚ ስር ያሉ ማለትም በግብርና፣ በአርብቶ አደርነት፣ በጥቃቅንና አነስተኛ ስራዎች ወይም ከመንግስትና ግል ስራ ቅጥር ውጪ ያሉ ሌሎች ስራዎች በመስራት የሚተዳደሩ ሰዎች እንዲሁም ስራ የሌላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በህመም ምክንያት በሚወጣ ወጪ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እንዳይደርስባቸው ከለላ የሚሰጥ ዕቅድ ነው፡፡
ማአጤመ ልክ እንደ ዕድር ከአባላቶቹ በተወሰነ ጊዜ የሚሰበሰብ ዐረቦን ይኖረዋል፡፡ ከዚያም የተሰበሰበው ገንዘብ መንግስት ለጤና ወጪ ከመደበው ፈንድ ጋር አብሮ በመሆን በጤና ጣቢያዎችና ሌሎች የመንግስት ህክምና ተቋማት ውስጥ የሚሰጡትን አገልግሎቶች ወጪ ለመሸፈን ይውላል፡፡ ስለዚህም አንድ የማዐጤመ ተጠቃሚ የጤና አገልግሎት ማግኘት ሲያስፈልገው ባቅራቢያው ያለው ጤና ጣቢያ በመሄድ ያሉትን የጤና አገልግሎቶች፣ የህመሙ አይነት በጤና ጣቢያ ለማከም የሚከብድ ከሆነ ደግሞ ከፍ ወዳለ የመንግስት ጤና ተቋም ተመርቶ ሄዶ በዚያ ተቋም ያሉ አገልግሎቶችን በነፃ መጠቀም ይችላል፡፡
ማአጤመ ምን አይነት አገልግሎቶችን ይሸፍናል?
የማአጤመ አባልነት
የማአጤመ አባልነት ምዝገባ በቤተሰብ ደረጃ ነው፡፡ ይህም ዋና ቤተሰብና አብረው የሚኖሩ ተጨማሪ የቤተሰብ አባላትን ያካትታል፡፡ ዋና ቤተሰብ ስንል ባለቤትዎና 18 አመት ያልሞላቸው ልጆችዎ ናቸው፡፡ለዋና ቤተሰብ የሚከፈለው መዋጮ በአመት በአዲስ አበባ ብር 350፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ብር 180፣ በተቀሩት ክልሎች ደግሞ ብር 240 ሲሆን ዋና ቤተሰብዎ በቁጥር ብዙም ሆኑ አነስተኛ ዐረቦኑ ላይ ለውጥ አያመጣም፡፡ 18 አመት ያለፋቸው ልጆችዎን ወይም ሌሎች አብረዎት የሚኖሩ ዘመዶችዎን ካስመዘገቡ ግን ለእያንዳዳቸው በየክልሉ የሚለያይ የተወሰነ ክፍያ ይጨመራል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ክፍያውን ለማድረግ አቅማቸው የማይፈቅድ 10% የሆኑት የህብረተሰቡ አካላት በነፃ የዕቅዱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይደረጋል፡፡
የማአጤመ ጥቅሞች
ማአጤመ ከጤና ጋር ተያይዘው በሚመጡ ወጪዎች ኪሳችን እንዳይጎዳ ይጠቅማል ብለን በደፈናው ማለፍ ይቻላል፡፡ ነገር ግን የጤና አገልግሎት ወጪን መሸፈን አለመቻል አስቀድሞ ያሉ ልዩነቶችን በማስፋት ሌሎች ውስብስብ ችግሮችን ስለሚፈጥር ማዐጤመ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍም ያግዛል፡፡
ጥናቶች እንደሚያመላክቱት 2011 ጀምሮ የተደረጉት የሙከራ እቅዶች ካሳደሩት ተፅዕኖዎች ውስጥ የገንዘብ እጦት የሚያሳድረውን ተፅዕኖ በመቀነስ የጤና መሻት ባህሪን (Health seeking behavior) ማጠናከር አንዱ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ የሴቶች እኩል ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ነው፡፡ የማዐጤመ ተጠቃሚ እናቶች እንዳስረዱት ለልጆቻቸው ቅድሚያ በመስጠት፣ ባለቤቶቻቸውን ለመጠየቅ በመፍራትና ንብረት ላለማስሸጥ በሚሉ ምክኒያቶች ህመማቸውን በቤት ውስጥ ይዘው ይቆዩ የነበረ ሲሆን ማዐጤመ እነዚህን ስጋቶች እንዳይጋፈጡ ረድቷቸዋል፡፡
ስለዚህ ማዐጤመ ሲታመሙ በነፃ የሚታከሙበት፣ ጤናማ በሆኑ ጊዜ ደግሞ ከእርስዎ ምናልባት በብዙ ኪሎሜትሮች ርቀው የሚገኙ ወገኖችዎን የሚያሳክሙበት አገርአቀፍ ዕድር እንደማለት ነው፡፡ በጥቂት ቦታዎች ላይ የተሞከሩት ዕቅዶች ከላይ የተጠቀሱትን ይበል የሚያሰኙ ውጤቶች ካስገኙ በ100 ሚሊዮን ሰዎች ላይ ተግባራዊ ሲሆኑ ደግሞ የጤና አገልግሎት አቅርቦት ላይ የሚመጣውን ለውጥ ያስቡት፡፡ ከዚህም አልፎ ከግልና ከውጪ ድርጅቶች ከሚመጣ ድጎማ ይልቅ፣ መዋጮውን እንደዋነኛ የጤና አገልግሎት ወጪ መሸፈኛ መንገድ በመጠቀም ከጥገኝነት ልንርቅ እንችላለን፡፡ በመሆኑም የዚህን ወር ዕድር ሲከፍሉ የአመቱን የጤና መድን ዐረቦን መቆጠብ እንዳይረሱ!
ዋቢ
- Alula M. Teklu, Yibeltal K. Alemayehu, Girmay Medhin, et al (2021). The Impact of Community Based Health Insurance on Health Service Utilization, Out-of-Pocket Health Expenditure, Women’s Empowerment, and Health Equity in Ethiopia: Final Report. MERQ Consultancy PLC.
- Federal Democratic Republic of Ethiopia Ministry of Health (2008). Health Insurance Strategy.
- Sahlework Zewde (2021). Community Based Health Insurance Proclamation. https://chilot.me/2021/02/08/community–based–health–insurance–proclamation/amp/
- Solomon Feleke, Workie Mitiku, Hailu Zelelew, et al (2015). Ethiopia’s Community-based Health Insurance: A Step on the Road to Universal Health Coverage. USAID.
https://www.hfgproject.org/ethiopias–community–based–health–insurance–step–road–universalhealth–coverage/
ይህ ፅሁፍ በ ዶ/ር የቆየሰው ወርቁ (የህብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ኤክስፐርት) እና የጤና ወግ ኤዲተሮች የተገመገመ ነው።
ፀሃፊ ፦ ህሊና ከበረ (በአ.አ.ዩ ህ/ጤ/ሳ/ኮ የህክምና ተማሪ- C2 )