ስለ ሪህ በሽታ (GOUT) ምን ያህል ያውቃሉ?
በዶ/ር አብዮት ያረጋል (በጥቁር አንበሳ ሆ/ል የውስጥ ደዌ እስፔሻላይዜሽን ሲኒየር ሬዝደንት)
ሪህ በመገጣጠሚያዎቻችን ላይ ከሚከሰቱና ከፍተኛ ህመም ሊያመጡ ከሚችሉ በሽታዎች በዋነኝነት የሚጠቀስ ሲሆን መንስኤውም የዩሪክ አሲድ (uric acid) ቅንጣጢቶች በአንጓዎቻችን ውስጥ ከመጠን በላይ መከማቸት ነው። ዩሪክ አሲድ ከተለያዩ ምግብና መጠጦቻችን የሚፈጠር ተረፈ ምርት ሲሆን ሰውነታችን በሽንት በኩል በአግባቡ ሊያስወግደው ካልቻለ በደማችን ውስጥ በመጠራቀም ለሪህ ህመም ሊያጋልጥ ይችላል። ከሪህ በተጨማሪም ክምችቱ የኩላሊት ጠጠሮችን ሊፈጥር ይችላል።
ምልክቶቹ ምንድን ናቸው?
በድንገት ሌሊት ላይ የሚከሰት ከባድ የመገጣጠሚያ ህመም ዋናው ምልክት ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ ከእግር አውራ ጣት ይጀምራል፡፡ ይሁን እንጂ ቁርጭምጭምት ፣ ጉልበት እና ሌሎች መገጣጠሚያዎች ላይም ይከሰታል፡፡ ከህመሙ በተጨማሪ የመገጣጠሚያ መቅላት እና ማበጥ ሊከሰት ይችላል፡፡ ሪህ ካልታከመ የዩሪክ አሲድ ቅንጣጢቶች አንድ ላይ በመሰባሰብ እባጮችን (Tophi) ይፈጥራሉ፡፡ እባጮች አብዛኛውን ጊዜ መገጣጠሚያዎች፣ ክርን እና ጆሮ ላይ የሚፈጠሩ ሲሆን በሽታው የከፋ መሆኑን ያመለክታሉ ፡፡ እኒህ እባጮች መገጣጠሚያ ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ሲሆን በጀርም ሊበከሉ እና ኢንፌከሽን ሊፈጥሩም ይችላሉ ፡፡
አጋላጭ መንስኤዎች፡
ውፍረት ፣ የስኳር በሽታ ፣ የኩላሊት በሽታ ፣ የደም ግፊት ፣ የሰውነት ቅባት (ኮሌስቴሮል) መጨመር ፣ የእድሜ መግፋት፣ ማረጥ ፣ በቤተሰብ የሪህ በሽታ መኖር ፣ ለተለያዩ ህመሞች የሚታዘዙ መድሃኒቶች (ለምሳሌ ዳዩሬቲክስ/Diuretics)፣ የዩሪክ አሲድ መጠንን የሚጨምሩ ምግቦች እና መጠጦች (ለምሳሌ ቀይ ስጋ ፣ ጉበት ፣ አንዳንድ የዓሳ ዝርያዎች ፣ አልኮል እና ጣፋጭ/ስኳራማ የለስላሳ መጠጦች) ወዘተ
ለሪህ ህመም የሚያስፈልጉ ምርመራዎች
- ከደም ናሙና በመውሰድ የዩሪክ አሲድ መጠንን መለካት
- የተጠቃውን መገጣጠሚያ በራጅ ወይም ሶኖግራፊ መመርመር
- ከመገጣጠሚያ (አንጒ) መሀከል የሚገኝን ፈሳሽ ናሙና በመውሰድ በላቦራቶሪ መመርመር ሊያስፈልግ ይችላል።
የሪህ ሕክምና
የህክምናው አላማ ብግነትን (inflammation) በማስቆም ምልክቶችን ማስታገስ፣ ደግመው እንዳይከሰቱ ማድረግና የመገጣጠሚያን ጉዳትን መቀነስ ነው፡፡
- የህመም ምልክቶችን የሚያስታግሱ መድሃኒቶች፡- ኮልቺሲን ፣ NSAID (ለምሳሌ ኢንዶሜታሲን ፣ ዳይክሎፈናክ ፣ አይቡፕሮፌን) እና ስቴሮይድ (ለምሳሌ ፕሪዲንሶሎን)። እነዚህም መድሀኒቶች በኪኒን ወይም በመርፌ ሊሰጡ ይችላሉ።
- የመገጣጠሚያ ጉዳትን ለመከላከል እና በደማችን ውስጥ የሚገኘውን የዩሪክ አሲድ መጠን ለመቀነስ ከሚያግዙ መድሀኒቶች፡- አሎፕሪኖል (Allopurinol) ዋናው ነው፡፡
- ከመድኃኒቶች ውጭ ያሉ ሕክምናዎች፤
- ክብደትን መቀነስ፡- ከመጠን በላይ ውፍረት ከሪህ ጋር ይዛመዳል ስለዚህ ክብደትን መቀነስ ሪህን ለማስታገስ እና ለአጠቃላይ ጤንነት ጥሩ ውጤት አለው ፡፡
- ጤናማ አመጋገብ፡- የሪህ ምልክቶችን ለማስወገድ እና ክብደት ለመቀነስ ይረዳል ፡፡
- “አጋላጭ መንስኤዎች” ከሚለው ስር የተጠቀሱትን ምግቦች እና መጠጦችን ማስወገድ
- ፍራፍሬዎችን ፣ አትክልቶችን እና ጥራጥሬዎችን አዘውትረው መመገብ፡፡
- በቂ ውሃ መጠጣት፡፡
- በሚያምዎ ቦታ ላይ በረዶ ማድረግ፡፡
የሕክምናው ለውጥ በደም ውስጥ ያለውን የዩሪክ አሲድ መጠን በመለካት ይገመገማል፡፡ ዓላማው የደምዎ ዩሪክ አሲድን መጠን ከ 6 mg/dl በታች እንዲቀንስ ማድረግ ነው። ነገር ግን ዩሪክ አሲድ ከ 6mg/dl በታች ቢሆንም አስቀድሞ በመገጣጠሚያዎች እና በሌሎች አካባቢዎች የተከማቹ የዩሪክ አሲድ ቅንጣጢቶች ሟሙተው እስኪያልቁ ድረስ የሪህ ምልክቶች ሊቀጥሉ ይችላሉ ፡፡
ስለ መድኃኒቶቹ
- የኩላሊት ወይም የጉበት በሽታ ወይም የመድማት ችግር ካለብዎት NSAID የሚባሉት መድሀኒቶች ( ኢንዶሜታሲን ፣ ዳይክሎፌናክ እና ኢቡፕሮፌን) የጎንዮሽ ጉዳት ሊኖራቸው ስለሚችል ሀኪምዎን ያማክሩ ፡፡
- አሎፕሪኖልን ምግብ ከተመገቡ በኋላ ይውሰዱት። መድሀኒቱ አጥጋቢ ውጤት ለማምጣት ብዙ ሳምንታትን ሊወስድ ይችላል፡፡
- አሎፕሪኖልን መውሰድ ሲጀምሩ ምልክቶቹ ለጥቂት ቀናት ሊባባሱ ይችላሉ፡፡ ይህ ከተከሰተ መድሀኒቱን ሳያቆሙ ምልክቶችን ለማስታገስ የሚያግዙ መድኃኒቶች መውሰድ ያስፈልጋል፡፡
- አሎፕሪኖል የጉበት እና የኩላሊት ችግር ሊያስከትል ይችላል፤ ብዙ ያልተለመደ ቢሆንም ከፍተኛ አለርጂ ሊያመጣም ይችላል፡፡ ስለዚህ ከሚከተሉት የአለርጂ ምልክቶች አንዱ ከተከሰተ አፋጣኝ የህክምና እርዳታ ያግኙ፤
- በቆዳ ፣ በአይን ፣ በአፍንጫ ወይም በጉሮሮ ላይ እንደ ሽፍታ፣ ቁስለት፣ ማሳከክ፣ ውሀ መቋጠር ወይም መላጥ ከተከሰተ፣
- የፊት ፣ የአፍ ፣ የከንፈር ፣ የምላስ ወይም የጉሮሮ እብጠት፣
- የትንፋሽ ማቃተት (ሲር ሲር ማለት)፤ ለመተንፈስ መቸገር፣ ለመናገር መቸገር ወይም ደረትን ሰቅዞ መያዝ፣
ያስታውሱ
- “አጋላጭ መንስኤዎች” በሚለው ስር ከተጠቀሱት እንዲሁም ሌላ ማንኛውም በሽታ ካለብዎ ወይም የባህል መድኃኒቶችን ጨምሮ ማንኛውንም መድሃኒት የሚወስዱ ከሆነ ለሐኪምዎ ይንገሩ ፡፡
- ነፍሰጡር ከሆኑ ወይም መሆን ካቀዱ ወይም ጡት የሚያጠቡ ከሆነ ለሐኪምዎ ይንገሩ ፡፡
- ሐኪምዎ ካላዘዘ በስተቀር የሪህ ምልክቶቹ ቢጠፉም ወይም የዩሪክ አሲድ መጠን ቢቀንስም ሪህ ተመልሶ ስለሚመጣ አሎፕሪኖልን አያቋርጡ!
- ቶሎ ካልታከሙ በስተቀር ሪህን ጨምሮ የመገጣጠሚያ ህመሞች የማይድን ጉዳትን ስለሚያስከትሉ ፈጥነው ወደ ሕክምና ተቋም ይሂዱ ። የህመም ስሜት ባይኖሮትም ክትትልዎን አያቋርጡ።