Samuel Mesfin ( 4th year medical student, AAU, School of Medicine)
በዚህ ፅሁፍ የምናነሳቸው ነገሮች
• ስትሮክ ምንድን ነው?
• ለስትሮክ ተጋላጭነትን የሚጨምሩ ነገሮች ምንድናቸዉ?
• በስትሮክ የተያዙ ሰዎች ሊያሳያቸዉ የሚችሉ ምልክቶች ምንድናቸዉ?
• አንድ ሰው ስትሮክ እንዳለበት እንዴት ማወቅ ይችላል?
• አንድ ሰዉ ስትሮክ እንዳለበት እንዴት ማረጋገጥ ይቻላል?
• ስትሮክ እንዴት ሊታከም ይችላል?
• ስትሮክ ከመከሰቱ በፊት አስቀድሞ መከላከል ይችላል?
• ከስትሮክ ቡሃላ ሊከሰቱ የሚችሉ ጉዳቶች ምንድናቸዉ?
• የስትሮክ የመልሶ ማቋቋም (Stroke Rehab)
• ከስትሮክ በኋላ ሙሉ በሙሉ የማገገም እድሎች በምን ይወሰናሉ?
• በሌላ ስትሮክ በድጋሚ ላለመያዝ ምን ማድረግ አለብኝ?
ስትሮክ ምንድን ነው?
• በኢትዮጵያ ስለስትሮክ ያለዉ መረጃ ውስን ቢሆንም በዓለም አቀፍ ደረጃ በየአመቱ 16.9 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በስትሮክ ይያዛሉ ፣ በዚህም ምክኒያት 5.9 ሚሊዮን የሚሆኑት ይሞታሉ ፡፡ ከዚህም መካከል ከሁለት ሦስተኛ በላይ የሚሆነዉ የስትሮክ ሞት የሚከሰተዉ በዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገሮች ነዉ፡፡
• ስትሮክ በተለያዩ ምክኒያቶች በአንጎል ዉስጥ የደም ፍሰት ችግር ሲያጋጥም የአንጎል ክፍል መጎዳትን ለማመልከት ሐኪሞች የሚጠቀሙበት ቃል ነው ፡፡ ስትሮክ የሚከሰተዉ
- ወደ አንጎል የሚሄደዉ የደም ቧንቧ በመዘጋቱ ምክኒያት የአንጎል ክፍል ረዘም ላለ ጊዜ ያለ ደም ሲቆይ
(ischemic stroke)
2. የደም ቧንቧ ወደ አንጎል እና ወደ አከባቢው ደም ማፍሰስ ሲጀምር (Hemorrhagic stroke)
ለስትሮክ ተጋላጭነትን የሚጨምሩ ነገሮች ምንድናቸዉ?
1. ወደ አንጎል የሚሄደዉ የደም ቧንቧ በመዘጋቱ ምክኒያት ለሚከሰተዉ ስትሮክ፡
• ዕድሜ፡ ከ 40 ዓመት በላይ
• የልብ ህመም
• ከፍተኛ የደም ግፊት
• ማጨስ
• የስኳር በሽታ
• ከፍተኛ የደም ኮሌስትሮል መጠን
• አደንዛዥ ዕፅ መጠቀም
• የእርግዝና እና የድህረ-ወሊድ ግዜ
• እንቅስቃሴ-አልባ የአኗኗር ዘይቤ እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ
• ከመጠን በላይ ውፍረት
• በቤተሰብ የልብ ህመም ወይም የደም ቧንቧ በሽታ ታሪክ ያላቸዉ
2. ወደ አንጎል እና ወደ አከባቢው ደም በመፍሰሱ ምክኒያት ለሚከሰተዉ ስትሮክ፡
• ከፍተኛ የደም ግፊት
• ማጨስ
• አደንዛዥ ዕፅ መጠቀም (በተለይም ኮኬይን)
• የጭንቅላት ላይ አደጋና የደም መፍሰስ
• የwarfarin ወይም ሌሎች የደም ማቅጠኛ መድሃኒቶች መጠቀም
በስትሮክ የተያዙ ሰዎች ሊያሳያቸዉ የሚችሉ ምልክቶች፡
• ፊት – ድንገተኛ ድክመት (droopiness of the face) ወይም የእይታ ችግሮች
• ክንድ – የአንዱ ወይም የሁለቱም ክንዶች ድንገተኛ መዛል ወይም የመደንዘዝ
• ንግግር – ለመናገር መቸገር
አንድ ሰው ስትሮክ እንዳለበት እንዴት ማወቅ ይችላሉ?
የአንጎል በሽታ ምልክቶች የሚያስታውሱበት ቀላል መንገድ አለ። እስቲ “FAST” የሚለውን ቃል አስቡበት ፡፡
• F-Face (ፊት): የግለሰቡ ፊት በአንደኛው ጎን ያልተስተካከለ ይመስላል?
• A-Arm (ክንድ): ግለሰቡ በአንዱ ወይም በሁለቱም ክንዶቹ ውስጥ ድክመት ወይም መደንዘዝ አለው?
• S-Speech (ንግግር): ግለሰቡ የመናገር ችግር አለበት? የእሱ አነጋገር እንግዳ ይመስላል?
• T-Time (ጊዜ): ከእነዚህ ምልክቶች መካከል አንዳቸውን ካስተዋሉና ለአምቡላንስ በመደወል ቶሎ ሕክምና
እንዲገኙ ካድረጉ ህመምተኞች ከበሽታዉ የማገገም እድላቸዉ ከፍተኛ ይሆናል
አንድ ሰዉ ስትሮክ እንዳለበት እንዴት ማረጋገጥ ይቻላል?
• የስትሮክ ምልክቶችን ያሳየ ማንኛውም ሰው በድንገተኛ ክፍል ውስጥ አስቸኳይ የህክምና እርዳታ ይፈልጋል ፡፡ ከነዚህም መካከል ፡
• የደም ምርመራዎች እና የአንጎል ምስል – ሐኪሙ ታካሚውን ከመረመረ በኋላ ብዙውን ጊዜ የደም ፍሰትን እና የአንጎልን የደም ሥሮች (በአንገትና በአንጎል ውስጥ ያሉትን) የሚያሳይ የአንጎል እና የአዕምሮ ምርመራን (CT Scan ወይም MRI Scan) ያዛል ፡፡ በተጨማሪም ሐኪሙ በአንጎል ውስጥ ጉዳት የደረሰበትን የአንጎል አካባቢ መመልከት እንዲሁም የስትሮኩን ዓይነት ማረጋገጥ ይችላል
• በተጨማሪም የልብ ምርመራ ሊታዘዝ ይችላል – ኤሌክትሮካርዲዮግራም (ECG) ስትሮክ አለባቸው ተብሎ ለሚታሰብ ብዙ ሰዎች ሊታዘዝ ይችላል፡፡ ወደ አንጎል የሚሄደዉ የደም ቧንቧ በመዘጋቱ ምክኒያት የሚከሰተዉ ስትሮክ ያለባቸዉ ሰዎች አብዛኛዉን ጊዜ ተጓዳኝ ለሆነ የልብ የደም ቧንቧ በሽታ (coronary artery disease) ተጋላጭ ስለሚሆኑ ECG መታዘዙ የሕክምና ባለሙያዉን በተቻለ መጠን ማንኛውንም የልብ ችግር ለመመርመርና በጊዜ ለማከም ይረዳዋል፡፡ ሌሎች የልብ ምርመራዎችም እንደ ኢኮካርዶግራም የመሳሰሉትንም መጠቀም ይመከራል።
ስትሮክ እንዴት ሊታከም ይችላል?
• ትክክለኛው ሕክምና የሚወሰነው እንደስትሮኩ አይነት ነዉ፡፡ በመሆኑም ወደ አንጎል የሚሄደዉ የደም ቧንቧ በመዘጋቱ ምክኒያት የሚከሰተዉ ስትሮክ ያለባቸዉ ሰዎች የተዘጋዉን ደም ቧንቧ እንደገና ለመክፈት የሚረዱ ሕክምናዎችን ያገኛሉ፡፡ ሌላኛዉ ህክምና አዲስ የደም መርጋትን ለመከላከል የሚረዳ ሲሆን ይህም ወደፊት የሚከሰትን ስትሮክ አስቀድሞ ለመከላከል ይረዳል ፡፡
የደም ቧንቧ ወደ አንጎል እና ወደ አከባቢው ደም ማፍሰስ ሲጀምር የሚከሰተዉ ስትሮክ ያለባቸዉ ሰዎች ደግሞ በአንጎል ውስጥ ወይም በአከባቢው ደም በመፍሰሱ ምክንያት የሚመጣውን ጉዳት ሊቀንሱ የሚችሉ ህክምናዎች ይደረግላቸዋል፡፡ ሌላኛዉ አማራጭ የደም መፍሰስን የሚጨምሩ መድሃኒቶችን መውሰድ ማቆምና የደም ቧንቧውን ለመጠገን ወይም የደም መፍሰሱን ለማስቆም ቀዶ ጥገና ማድረግ ነዉ፡፡
ስትሮክ ከመከሰቱ በፊት አስቀድሞ መከላከል ይችላል?
አዎ፡-
1. መድሃኒቶችዎን በታዘዘዉ መሰረት በትክክል መውሰድ ፡፡ በስትሮክ የመያዝ እድልን በእጅጉ ሊቀንሱ የሚችሉ መድሃኒቶች የሚከተሉት ናቸዉ፡-
• የደም ግፊት መድሃኒቶች
• ኮሌስትሮልን ዝቅ የሚያደርጉት መድኃኒቶች
• የደም መርጋትን ለመከላከል የሚረዱ እንደ አስፕሪን አይነት ያሉ የደም ማቅጠኛ መድሃኒቶች
• በደም ዉስጥ ያለ ስኳርን በተቻለ መጠን ወደ ጤናማ መጠን ለማቅረብ የሚረዱ መድሃኒቶች (የስኳር በሽታ ካለብዎ)
2. የአኗኗር ለውጦችን ማድረግ-
• የሚያጨሱ ከሆነ ማጨስን ያቁሙ
• መደበኛ የአካል እንቅስቃሴ ያድርጉ (ቢያንስ በቀን ለ 30 ደቂቃዎች ፣ በሳምንት አብዛኛዉን ቀናት)
• ከመጠን በላይ የሆነ ዉፍረት ካለ ክብደትዎን ያቀንሱ
• በፍራፍሬዎች ፣ በአትክልቶች ፣ እና ዝቅተኛ ስብ ካላቸዉ የወተት ተዋጽኦዎች የበለጸጉ ምግቦችን ይመገቡ
እንዲሁም ጣፋጮች እና የተጣራ እህል (እንደ ነጭ ዳቦ ወይም ነጭ ሩዝ) ያሉን ይቀንሱ
• ያነሰ ጨው (ሶዲየም) ይጠቀሙ
• የሚጠጡትን አልኮሆል መጠን ይገድቡ
ከስትሮክ ቡሃላ ሊከሰቱ የሚችሉ ጉዳቶች ምንድናቸዉ?
• ስትሮክ የሚያስከትለው ውጤት ጊዜያዊ ወይም ዘላቂ ሊሆን ይችላል
• ስትሮክ ሊያስከትለዉ ከሚችለዉ በጣም የተለመዱ የረጅም ጊዜ ችግሮች እነዚህ ናቸው፡-
➢ የመናገር ችግር – መናገር አለመቻል ፣ ንግግርን አለመረዳት
➢ ድክመት እና የመንቀሳቀስ ችግሮች – የጡንቻ ድክመት ፊት ፣ ክንድ እና እግር ላይ ተጽዕኖ ሊያሳርፍ
ይችላል ፡፡ እንዲሁም በእግር መጓዝ ፣ የታቀዱ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ፣ ነገሮችን በእጅ መያዝ ወይም
ሚዛን መጠበቅ ሊያቸግር ይችላል።
➢ ከፊል የስሜት መቀነስ – በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ የስሜት መቀነስ (loss of sensation)
➢ የመብላት ወይም የመዋጥ ችግር – ይህንን ችግር ለመቋቋም አንዳንድ ሰዎች የመመገቢያ ቱቦ ይፈልጋሉ ፡፡ ሌሎች የሚበሏቸውን እና የሚጠጡ ምግቦችን እና ፈሳሾችን በመቀየር መላመድ ይችላሉ ፡፡
➢ ጭንቀት፡ ለድብርት ተጋላጭ መሆን
➢ አንዳንድ ጊዜ ሽንትና ሰገራን የመቆጣጠር ችግር ሊያጋጥም ይችላል
የስትሮክ የመልሶ ማቋቋም (Stroke Rehab)
• በመልሶ ማገገም ወቅት ሰዎች ያጧቸውን ችሎታዎች እንደገና ለማገገም ይሰራሉ ፡፡ ምንም እንኳን አንጎል በስትሮኩ ቢጎዳም ከዚህ በፊት አንዳንድ ነገሮችን እንዴት እንደሚያከናውን እንደገና መማር ይችላል ፡፡ ማገገም ብዙውን ጊዜ “የመልሶ ማቋቋም” ተቋም ውስጥ የሚሰጥ ሕክምናን ያጠቃልላል፡፡
ለምሳሌ፡-
የአካል (physical) ቴራፒስት አረማመድዎን ማሻሻያ መንገዶችን ሊያሳይዎት ይችላል/የሥነ አእምሮ ሐኪም
ድብርት ለማከም መድኃኒቶችን ሊያዝዙ ይችላል፡፡
ከስትሮክ በኋላ ሙሉ በሙሉ የማገገም እድሎች በምን ይወሰናሉ?
• የተጎዳዉ የአንጎል ክፍል የትኛዉ ነዉ?
• ግለሰቡ ዕድሜው ስንት ነው? (ወጣቶች በእድሜ ገፍ ካሉ ሰዎች በተሻለ ሁኔታ ያገግማሉ)
• ግለሰቡ ሌሎች ተጓዳኝ የጤና ችግሮች ካሉት (ለምሳሌ የልብ ችግር/ካንሰር)
• ከስትሮኩ በፊት ግለሰቡ ታሞ ከነበረ
• ግለሰቡ ከስትሮኩ ቡሃላ ዘግይቶ ህክምና ከገኘ
በሌላ ስትሮክ በድጋሚ ላለመያዝ ምን ማድረግ አለብኝ?
• ወደ አንጎል የሚሄደዉ የደም ቧንቧ በመዘጋቱ ምክኒያት የአንጎል ክፍል ረዘም ላለ ጊዜ ያለ ደም ሲቆይ የሚከሰተዉ ስትሮክ ከነበረብዎ ፣ዶክተርዎ ያዘዘሎትን መድሃኒቶች ሳያቆራርጡ በመዉሰድና እና የአኗኗር ዘይቤ ለውጦችን በማድረግ በሌላ ስትሮክ የመያዝ እድልዎን መቀነስ ይችላሉ ፡፡
Reference:
- Up-To-Date
ይሄ አስተማሪ የህክምና ፅሁፍ የቀረበው የጤና ወግ እና የ ኢትዮጵያ ሕክምና ተማሪዎች ማህበር ባዘጋጁት የህክምና ተማሪዎችን የመረጃ አስበሰብ እና ህብረተሰቡን የማስተማር አቅማቸውን ለማዳበር ለታለመ የበጎ ፍቃድ ውድድር ነው። እያንዳንዱ ፅሁፍ በ ጤና ወግ የታየ እና እርማት ተደርጎበት የቀረበ ነው ።