(በአፎሚያ ሰይፈ  በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ /// የህክምና ተማሪ-C1)

በሃገራችን የራስን ጤና በመጠበቅ እና በመከታተል ረገድ ብዙ ጉድለቶች ቢኖሩም የአእምሮአችን ጤና ደሞ ከሌሎች አካላቶቻችን ጤና በላይ ትኩረት ሲነፈገው እንመለከታለን። እንዲሁም የአእምሮ ጤና እክሎችን  ከሌሎች አካላት በተለየ በመንፈሳዊ መንገድ በመረዳት ተገቢው የህክምና ክትትል ሳይደረግ ሲቀር እናያለን። ከዚህም በተጨማሪ የአእምሮ ህሙማን መጥፎ ስያሜዎች ሲሰጧቸው እና ለአካላዊ እና ስነልቦናዊ ጉዳቶች ሲጋለጡ መመልከት የተለመደ ነው። በዚህች ጽሁፍ ውስጥ ከብዙ የአእምሮ ህመሞች መሃል አንዱ የሆነውን ስኪዞፍሪኒያን(በገሀዱ አለም የማይታዩ እና የማይሰሙ ነገሮችን የማየት እና የመስማት ህመም) በጥቂቱ እንመልከት።

ስኪዞፍኒያ ምንድነው?

ስኪዞፍሬኒያ ጤናማ ሰዎች ከሚሰማቸው ስሜት ባፈነገጠ መልኩ የሚፈራረቅ የስሜት መጋነን እና መቀዛቀዝ እንዲሁም ከእውነታ ውጪ የሆኑ አስተውሎቶችን እና አመለካከቶችን የሚያመጣ የአእምሮ ህመም ነው። አንድ በመቶ ወይም ከዚያ በታች የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን የሚያጠቃ ሲሆን በቤተሰብ ውስጥ ከዚህ በፊት የስኪዞፍሪኒያ ታማሚ ካለ ግን ይህ ቁጥር ወደ አስር በመቶ ከፍ ይላል።ስለዚህ ስኪዞፍሪኒያ በዘር ሊተላለፍ ይችላል ማለት ነው። በሽታው ከሚታይባቸው ሰዎች መሃል አንድ ሶስተኛዎቹ በህይወታቸው አንድ ጊዜ ብቻ አጋጥሟቸው የሚያልፍ ሲሆን በቀሩት ላይ ግን በተደጋጋሚ የሚከሰት ነው። በመጀመሪያ የሚታይባቸውም ከ15 እስከ 25 አመት የእድሜ ክልል ሳሉ ነው።

በሽታው በሚጀምርባቸው ጊዜያት ከሰዎች መነጠልን፣የመንፈስ መጨነቅን እና ምክንያት የሌለው ከፍተኛ ፍራቻን ያመጣል። ከዚያም ከሳምንታት እስከአመታት ባለ ጊዜ ዉስጥ ተባብሶ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ይደርሳል። በዚህ ጊዜ የሚከተሉትን ምልክቶች ማሳየት ይጀምራል ።

    – በጣም የተጋነኑ ስሜቶች እና አስተውሎቶች

በገሃዱ አለም የሌሉ ድምጾችን መስማት፣ የሌሉ ነገሮችን ማየት መቅመስ ወይም ማሽተት በአጠቃላይ በቁም መቃዥት ይታይባቸዋል። ያለተገቢ ምክንያት ጸጸት ውስጥ ተዘፍቀው ልናገኛቸውም እንችላለን።

    – ከእውነት የራቁ አስተሳሰቦች እና የተሳሳቱ እምነቶች

እነኚህ ታማሚዎች ‘የተለየ ስጦታና ሃይል አለኝ’ ወይም ‘ከሌሎች የምበልጥ ነኝ’ ሊሉ ይችላሉ። አለበለዚያ ‘ሰዎች እያሳደዱኝ ነው’ ብለው ሊሸሹ እና ሊደበቁ ሲጥሩም ይታያሉ።

    – ከተገቢው በታች የተቀዛቀዙ ስሜቶች እና ፍላጎቶች

ስራ ለመስራት እና የየእለት ተግባራትን ለማከናወን ፍላጎት ማጣት ፣ በሁሉም ነገር መሰላቸት ይስተዋልባቸዋል። በተጨማሪም ስሜታቸውን የመግለጽ ችሎታቸው በጣም ስለሚቀንስ የደነዘዘ ፊት ይታይባቸዋል ።ስለዚህ እንደጤናማው ሰው በሃዘን እና በደስታ ጊዜ ተገቢውን ስሜት ማንጸባረቅ አይችሉም።

– የንግግር መዛባት

የተዘበራረቁ እና ተያያዥነት የሌላቸውን ሃሳቦች በአንድ ጊዜ ስለሚናገሩ ከሰው ጋር መግባባት ይቸግራቸዋል።

ትኩረት ሊሰጣቸው ሚገቡ ጉዳዮች እና ጥንቃቄዎች ምን መሆን አለባቸው?

በመግቢያው እንደተጠቀሰው ለአእምሮ ጤና የሚሰጠው ትኩረት ያነሰ በመሆኑ እና በብዛትም መንፈሳዊ ተደርጎ ሰለሚታይ ምልክቶች የከፋ ደረጃ ሳይደርሱ መቆጣጠር የሚቻልበት እድል ሲጠብ ይስተዋላል። ስለዚህ ግለሰቦች የራሳቸውንም ሆነ የወዳጅ ዘመዶቻቸውን የአእምሮ ጤና በመከታተል ያልተለመዱ የጸባይ ለውጦችንም በማስተዋል የህክምና ክትትል ማድረግ አለባቸው። ይህ በሽታው ሳይባባስ ለመቆጣጠር ስለሚረዳ እጅግ አስፈላጊ ነው። በተለይም በቤተሰብ ውስጥ ስኪዞፍሪኒያ ያለበት ሰው ካለ የተቀሩት የቤተሰብ አባላት ለአእምሮ ጤናቸው ልዩ ትኩረት መስጠት ይገባቸዋል። ስኪዞፍሪኒያ ያለበት ሰው በሽታውን ስለሚያባብሱ ከአልኮል እና ከአደንዛዥ እጾች መቆጠብ ይኖርበታል።

በሽታውን ሙሉ ለሙሉ የሚያስወግድ ፈዋሽ መድሃኒት ባይኖርም ምልክቶቹን በቁጥጥር ስር በማድረግ በኑሮ ላይ የሚያመጣውን ተጽእኖ መቀነስ ስለሚቻል የስኪዞፍሪኒያ ታማሚዎችን ወደ ህክምና ማምጣት እጅግ ጠቃሚ ነው።

በተጨማሪም የዚህንም ሆነ የሌሎች የአእምሮ ህመም ተጠቂ የሆኑ ሰዎችን ባልተገባ መልኩ እንደ ‘እብድ’ የመሰሉ ስያሜዎችን ሰጥቶ ማሸማቀቅ ግፋ ሲልም አካላዊ እና ጾታዊ ጥቃቶችን ማድረስ ማህበረሰባችን ሊያስወግደው የሚገባ እጅግ መጥፎ ልማድ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። የአእምሮ ህሙማን እንደልብ፣ ኩላሊት እና ሳንባ ህሙማን ሁሉ የታመሙ ናቸውና እንክብካቤ እና ተገቢየህክምና ክትትል ሊደርግላቸው እንጂ ጥቃት ሊደርስባቸው አይገባም።

ምንጮች

American psychiatric association (www.psychiatry.org)

Multicultural mental health Australia (www.mmha.org.au)

ይህ ፅሁፍ በዶ/ር ሄርሞን አማረ (የስነ አዕምሮ ህክምና ስፔሻሊስት) እና የጤና ወግ ኤዲተሮች የተገመገመ ነው።