ከእምነት ሰለሞን (ጎንደር ዩ/ህ/ጤ/ሳ/ኮ የህክምና ተማሪ-C2)
❖ ከብዙ የአእምሮ ህመሞች መካከል አንዱ ሲሆን በሰው ሀሳብ፣ስሜት እና ባህሪ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያሳድራል፤ አንዳንዴም ከገሃዱ አለም ጋር ያልተቆራኙ ሊያስመስል ይችላል።
❖ አንድ ሰው በዚህ በሽታ በህይወት ዘመኑ የመጠቃት እድሉ 1 በመቶኛ ሲሆን በቤተሰብ ውስጥ የዚህ በሽታ ታማሚ ካለ እድሉ ወደ 10 በመቶኛ ያድጋል።
❖ በሁለቱም ጾታ ላይ እኩል የሚከሰት ሲሆን በብዛት የሚጀምርበት እድሜ ለወንዶች ከ10~25፤ ለሴቶች ደግሞ ከ25~35 ባለው የእድሜ ክልል ወስጥ ነው።
የስኪዞፍሬንያ መንስኤዎች፡-
• የዘረመል ተጋላጭነት (genetic factor ) ሲኖር
• በቤተሰብ/በዘመድ ውስጥ ታማሚ ከነበረ በዘር ሊተላለፍ ይችላል ∙
• በጽንስ እና በወሊድ ወቅት የሚከሰቱ ኢንፌክሽኖች በተለይም በእርግዝና በመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት ላይ ፣እንዲሁም በእርግዝና ወቅት የምግብ እጥረት ሲያጋጥም
• ሌላው ደግሞ በአእምሮአችን ውስጥ ዶፓሚን የተባለው ንጥረ ነገር በብዛት መለቀቅ ሲሆን በህመሙ ለሚታዩ ምልክቶች ትልቅ ድርሻን እንደሚወስድ ይታመናል።
ምልክቶቹ
በጤነኛ ሰው ላይ የማይታዩና በታማሚው ላይ የሚታዩ ልዩ ምልክቶች
∙ ሀሉሲኔሽን~ማለትም በገሀዱ ያልተፈጠረን ነገር አእምሮአችን እንደተከሰተ ሲያስብ ነው። በአብዛኛው የሚከሰተው የድምጽ ሀሉሲኔሽን ሲሆን ታማሚው የሹክሹክታ አንዳንዴም የዛቻ፣የወቀሳ ወይም የስድብ ይዘት ያለው ድምጽ ሊሰማው ይችላል። አልፎ አልፎም በገሀድ የማይታዩ ነገሮች ሊታያቸው ይችላል።
∙ ዴሉዥን ~ይህ ማለት እውነትነት የሌለውን ነገር በጸና አቋም ማመን ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ታማሚ ሰዎች እያሴሩበት እና ሊገሉት እንደሚያሳድዱት ሲያምን፤ ባስ ካለም ተጠራጣሪ ሊሆን እና በህክምና የሚሰጠውን መድሃኒት እስካለመውሰድ ሊደርስ ይችላል።

ጤነኛ ሰዎች ላይ ያሉ በታማሚው ላይ በጎላ መልኩ የሚታዩ ምልክቶች
∙ ሀሳብን እና ስሜትን ለመግለጽ መቸገር
∙ በማህበራዊ ህይወት ውስጥ ምንም ነገር ለማድረግ ፍላጎት እና ተነሳሽነት ማጣት
∙ የማስታወስ ችግር ይህም በስራ ላይ መዘናጋት፣ ቀጠሮ መርሳት እና የትኩረት መቀነስ ናቸው፡፡
እነዚህ ምልክቶች በሌላ የአእምሮ ህመም አልያም በአደንዛዥ እጽ አማካኝነት ሊከሰቱ ይችላሉ። ስለዚህ ምልክቶቹ ለዚህ በሽታ ጠቋሚ የሚሆኑት በጥቂቱ ለ6 ወር እና ከዛም በላይ የቆዩ ሲሆን በተጨማሪም በታማሚው የእለት ተእለት ህይወት እና ግንኙነት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ሲፈጥሩ እና ሌሎች ምክንያቶች አለመኖራቸው በሀኪም ሲረጋገጥ ነው፡፡
የህክምና እና የማገገሚያ መንገዶች
የህክምና አማራጮች ~ግቡ የአእምሮን የመስራት ችሎታና በተሻለ መንገድ የመኖርን አቅም ማስጠበቅ እና ማጎልበት ነው።
በርከት ያሉ የህክምና መንገዶች ቢኖሩም በዋነኝነት በሁለት ፈርጅ የሚቀመጡ ናችው።
1 የመድሃኒት ህክምና (psychopharmacology )¬ይህ በዋነኝነት ጥቅም ላይ የሚውል ነው።
2 የስነ ልቦና ምክር (psychosocial therapy) – ይህ መንገድ ለዋናው ህክምና እንደ አጋዥ በመሆን ያገለግላል በውስጡም የተለያዩ ዘዴዎችን ያካትታል
¬የማህበራዊ ክህሎት ስልጠና (social skill training )
¬የግል ወይም የቡድን የባለሙያ ምክር (Individual or group therapy) ¬ቤተሰብ አቀፍ ህክምና (family therapy)
በማንኛውም የህክምና መንገዶች መዘንጋት የሌለበት የስኪዞፍሬንያ በሽታ ተመልሶ የማገርሸት ባህሪ እንዳለው ነው፡፡ ይህም በአብዛኛው ታማሚው ለጭንቀት በተጋለጠ ጊዜ ወይም መድሃኒት በትክክል በማይወስዱ ታማሚዎች ላይ ይታያል፡፡ ስለዚህ ለታካሚው በሽታው ከበድ ያለ እና ረጅም ጊዜ የሚቆይ መሆኑን ማስረዳት ያስፈልጋል፡፡
የበሽታው ሂደትና እና ዘላቂ ምልከታዎች
የመልካም ሂደት እና ምልከታ ጠቋሚዎች (good prognosis factors)
∙ የበሽታው ምልክቶች በድንገት መጀመራቸው
∙ የታወቀ የበሽታው መንስኤ
∙ ተመሳሳይ የቤተሰብ የህክምና ታሪክ አለመኖሩ
∙ የሌሎች ተጓዳኝ ህመሞች አለመኖር
∙ ጥሩ ቤተሰባዊ ድጋፍ እና አካባቢያዊ ሁኔታ መኖር
∙ መድሃኒት በአግባቡ መውሰድ ጥቂቶቹ ናቸው።
ስለ አእምሮ በሽታ በማህበረሰባችን ዉስጥ በቂ ግንዛቤ የለም፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ከመንፈሳዊ ተጽእኖ ጋር ስለሚገናኝና በህክምና እንደሚድን ስለማይታመን በሽታው ተባብሶ ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል፡፡ በተጨማሪም በታማሚዎች ላይ የሚደርሰው መገለል ቀላል አይደለም።
ጥናቶች እንደሚያሳዩት በታዳጊ አገራት የዘላቂ ምልከታ ውጤቶች አመርቂ ሆነው ተገኝተዋል ይህም ከ40~60 በመቶኛ የሚሆኑት ታካሚዎች በአነስተኛ እክል ወደ ጤንነታቸው መመለስ ችለዋል፡፡
ስለዚህም የአእምሮ ህሙማን እንደ ማንኛውም ታማሚ መሆናቸውን በመገንዘብ እና በጊዜ ከታከሙ ሊድኑ እንደሚችሉ በማሰብ ቶሎ የህክምና እርዳታ እንዲያግኙ ማድረግ የሁላችንም ሃላፊነት ነው።
ዋቢ
Coffey M. Schizophrenia: a review of current research and thinking. Journal of clinical nursing. 1998 Nov 1;7(6):489-98.
Sadock BJ. Kaplan & Sadock’s synopsis of psychiatry: behavioral sciences/clinical psychiatry.
Alem A, Kebede D, Fekadu A, Shibre T, Fekadu D, Beyero T, Medhin G, Negash A, Kullgren G. Clinical course and outcome of schizophrenia in a predominantly treatment-naive cohort in rural Ethiopia. Schizophrenia bulletin. 2009 May 1;35(3):646-54.
American Psychiatric Association, American Psychiatric Association. Diagnostic and statistical manual of mental disorders: DSM-5. Arlington, VA. 2013.

ይህ ፅሁፍ በዶ/ር ሄርሞን አማረ (የስነ አዕምሮ ህክምና ስፔሻሊስት) እና የጤና ወግ ኤዲተሮች የተገመገመ ነው።