በዶ/ር ኤርምያስ ካቻ (MD )

ሺሻ (ሁካ) በብዙ በተለያዩ ጣዕሞች ውስጥ የሚመጡ ልዩ የትንባሆ ድብልቅዎች ናቸው።  እነዚህ የትንባሆ ድብልቆች በከሰል አሳት በሚሞቁበት ጊዜ የሚወጣው  ጭስ ውሃ በተሞላ ክፍል ውስጥ በማለፍ ወደ ማጨሻው ቱቦ ይሄዳል። ከዚያም ተጠቃሚው ጭሱን በቱቦው አማካኝነት በመማግ ወደሳንባ ያስገባል፡፡ ሁካ ተጠቃሚዎች ብዙውን ጊዜ ሲጋራ ከማጨስ የበለጠ ጉዳት የለውም ብለው ያስባሉ፣ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ግን  ጭሱ እንደ ኒኮቲን፣ ታር እና ከባድ ብረቶች ያሉ በሲጋራ ጭስ ውስጥ የሚገኙ በርካታ ተመሳሳይ መርዛማ ንጥረ ነገሮችን ይይዛል። 

የሁካ ስርጭት 

ሁካ ጥቅም ላይ መዋል የጀመረው ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት በጥንቷ ፋርስ እና በሕንድ ነበር፡፡ ዛሬ የብሪታንያ፣ ፈረንሳይ፣ ሩሲያ፣ መካከለኛው ምስራቅ እና አሜሪካን ጨምሮ በዓለም ዙሪያ የሺሻ ቤቶች ተሰራጭተው ይገኛሉ። እ.ኤ.አ. በ2018 የተደረገ ጥናት አንደሚያመለክተው በአሜሪካ ውስጥ 7.8% የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪዎች ሁካን ትንባሆ ለማጨስን ተጠቅመው ነበር ፡፡ ከ19-30 ዓመት እድሜ ያላቸው ወጣቶች መካከል 12.3% ወጣቶች ባለፈው አንድ ዓመት ሁካን ተጠቅመዋል። የ ተለያዩ ጥናቶች አንዳመለከቱት ይህ ቁጥር በኮሌጅ ተማሪዎች ዘንድ በጣም ከፍ ያለ ነው (22 – 40%)። 

ወደ ሀገራችን ኢትዮጵያ ስንመጣ ጉዳዩ በጊዜ ሂደት አሳሳቢ አየሆነ አየመጣ ነው። በተለያዩ ወቅቶች በዜና አውታሮች አንደምንመለከተው ብዙ ወጣቶች ለዚህ ሱስ ተገዢ ሆነዋል። እንደ በበለጸጉ አገራት ሁሉ ትንባሆ እና የአልኮል መጠጦች በኢትዮጵያ ወጣቶች መካከል ለቤተሰብ እና ለእኩዮቻቸው ተጋላጭ በሆኑት መካከል ይጨምራል። ምንም አንኩአን  ሰፊ የሆነ የጥናት መረጃ ባይኖርም፣ የተወሰኑ ጥናቶች የጉዳዩን አሳሳቢነት አስፍረዋል። ለምሳሌ ያህል በቅርብ በተደረገ ጥናት ኢትዮጵያ ውስጥ 11 % የሚሆኑ ጎረምሶች የሲጋራ ተጠቃሚ ናቸው። ሺሻና ሲጋራን መጠቀም በዋነኛነት ከጫት መቃም ጋር ተያይዞ ታይቷል። ይህም የተለያዩ የሀገሪቷ ክፍሎችን በተለያየ መጠን አጥቅቷል።  ለምሳሌ በሰሜን ኢትዮጵያ በአንድ ከተማ በተደረገ ጥናት 82% የሚሆኑ የሺሻ ተጠቃሚዎች አድምያቸው ከ 35 ዓመት በታች ነበር። ከዚ  ውስጥ አንድ ሶስተኛ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ነበሩ። 

በአሜሪካ በትውልደ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ላይ በተደረገ ጥናት፣ ሁካን መጠቀም በከፍተኛ ደረጃ አየጨመረ ያለ ሱስ ሆኖ ተገኝቷል። ይህም ጉዳቱን ያላመዘነ ማህበራዊ ተቀባይነት ያለው ልምድ አየሆነ ነው። የኢትዮጵያዊና  እና ኤርትራዊ አሜሪካን  ማህበራዊ ዝግጅቶች ፣ የባህል ፌስቲቫሎች ፣ የስፖርት ጨዋታዎች እና ሙዚቃ ኮንሰርቶች ማስታወቂያዎች  ብዙውን ጊዜ  ሁካን በተጨማሪ አንዳለ ይናገራሉ። በግምት 400 ተሳታፊዎች በተሳተፉበት ጥናት ወደ 80% የሚሆኑት ሁካን በተወሰነ የድሜ ክፍል ውስጥ ሞክረዋል። 43% የሚሆኑት ደሞ በባለፉት ሰላሳ ቀናት ውስጥ ሁካ አጭሰዋስል። ሁካን መጠቀም ከ 24 እስከ  29 ዕድሜ ላይ ባሉ ሰዎች መካከል በይበልጥ ታይቷል። ይህ ጥናት አንዳመለከተው ሁካን መጠቀም በፆታ፣ በሥራ አይነት ወይም በትምህርት ደረጃ የተለየ አልነበረም። ይህ በዋነኛነት ሺሻ ማጨስ  ሲጋራ አንደ ማጨስ ጉዳት የለውም ከሚል የተሳሳተ አስተሳሰብ የመነጨ ነው። 

የሁካ የጤና እክሎች 

ሁካ ጭስ እና ካንሰር

  • የሁካ ትምባሆን ለማሞቅ የሚያገለግለው ከሰል ከፍተኛ የካርቦን ሞኖክሳይድ፣ ብረቶች እና ካንሰር አምጭ ኬሚካሎች በማመንጨት የጤና አደጋዎችን ይፈጥራል። 
  • ምንም አንኳን ጭሱ በውሃ ውስጥ አልፎ ቢመጣም ከፍተኛ የሆነ መርዛማ ኬሚካሎችን ይይዛል። 
  • አነዚህም ኬሚካሎች የሳንባን ጨምሮ የአፍና የፊኛ ካንሰርን ያመጣሉ።

የሁ ጭስ ሌሎች የጤና እክሎች 

  • የሁካ ትንባሆ ጭስ የደም ቧንቧዎች ላይ ጉዳት የሚያደርሱ አንዲሁም የልብ ህመም ሊያስከትሉ የሚችሉ በርካታ መርዛማ ወኪሎች ይዘዋል ፡፡
  • ሁካን ተጋርቶ በማጨስም በሽታ ካንዱ ወደሌላው ሰው ሊተላለፍ ይችላል። 
  • ሁካ የሚያጨሱ አናቶች የሚወልዷቸው ልጆች ክብደታቸው ያነሰ ሆኖ ተገኝቷል። 
  • ሁካ በሚያጨሱ አናቶች የተወለዱ ሕፃናትም የመተንፈሻ አካላት አደጋ ተጋላጭ ናቸው።

ሁካ ማጨስ ከሲጋራ ማጨስ ጋር ሲነፃፀር

ምንም አንኳን ብዙ ሰዎች ሁካ ከሲጋራ ማጨስ ያነሰ አደጋ አለው ብለው ቢያስቡም፣ እውነታው የሚያሳየው ግን ሁለቱም ተመሳሳይ የሆነ ጉዳት አንዳላቸው ነው። 

  • ሁለቱን ለሱስ የሚያጋልጠውን ኒኮቲን ይዘዋል።    
  • የሁካን ጭስ ለማውጣት የሚጠቀመው ሙቀት አንደ ሲጋራ ሁላ አደገኛ መርዛማ ንጥረ ነገሮችን ይፈጥራል። 
  • ከሁካ አጠቃቀም የተነሳ የሁካ አጫሾች ከሲጋራ አጫሾች የበለጠ በሲጋራ ጭስ ውስጥ የሚገኙትን መርዛማ ንጥረ ነገሮችን በተጨማሪነት ሊወስዱ ይችላሉ ፡፡
  • የአንድ ሰዓት ርዝመት ያለው የሁካ ማጨስ ክፍለ ጊዜ 200 puffs (የጭስ መጠን) ሲጠቀሙ አንድ ሲጋራ ማጨስ ደግሞ 20 የጭስ መጠን (puffs) ያካትታል።
  • በአንድ ሁካ ማጨስ ክፍል ጊዜ ውስጥ የሚወጣው ጭስ መጠን ዘጠኝ ሊትር ነው ፣ አንድ ሲጋራ ማጨስ ከዚ አንፃር ግማሽ ሊትር ጭስ ያመነጫል። 

ሁካ አጫሾች እንደ ሲጋራ አጫሾች ተመሳሳይ ለሆኑ በሽታዎች ተጋላጭ ሊሆኑ ይችላሉ ፡፡ እነዚህም የሚከተሉትን ያካትታሉ፣

  • የአፍ ካንሰር
  • የሳምባ ካንሰር
  • የሆድ ካንሰር
  • የሆድ እጢ ካንሰር
  • የሳንባ ተግባር መቀነስ
  • የመራባት መቀነስ 

ሁካና እና የእጅ አዙር ጭስ (Secondhand smoke)

ሁካ እንደ ሲጋራ ሁሉ በቅርብ ያሉ የማያጨሱ ግን ለጭስ የተጋለጡ ሰዎች ላይ ተመሳሳይ የሆነ የጤና አክል ይፈጥራል። 

ማጣቀሻዎች

  1. CDC
  2.  Int J Pediatr. 2019 May 8;2019:4769820
  3. BMC Public Health. 2019 Jul 12;19(1):938
  4.  Open J Epidemiol. 2013 Nov;3(4): 184– 92
  5. Journal of Health Care for the Poor and Under-served, Volume 30, Number 1, February 2019, pp. 378-391 (Article)
  6. American Lung Association 

የጤና ወግ

በመረጃ የተመሰረተ ሕክምና ብቻ ።  

………………………………………………………………………………………………………………………..

ይህ የጤና ወግ ድረ ገፅ ነው።
ስለ ጤንነታችሁ ማወቅ የምትፈልጉትን መረጃ የምታገኙበት ፣ በህክምና ባለሙያዎች የሚዘጋጅ የመረጃ ምንጭ ነው።
ሁልግዜም ከሀኪማችሁ ተማከሩ፣ ተጨማሪ መረጃ ከፈለጋችሁ የኛን ድረ ገፅ ጎብኙ።

በጥናት የተደገፈ መረጃ ብቻ እናቀርባለን።

የህክምና ባለሙያዎች ለህሙማኖቻችሁ የሚሆን የሚነበብ መረጃ ከፈለጋችሁ ይህን ግፅ ጠቁሟቸው። ህሙማኖቻችሁ እንዲያውቁት የምትፈልጉትን ነገር መረጃ ጠቅሳችሁ ፃፉልን፣ ስምችሁን ጠቅሰን እናወጣለን። የህክምና ተማሪዎች እንዲጽፉ እናበረታታለን።

በተጨማሪም በጤና ወግ ፖድካስት፣  በ ዩትዩብ ፣በ ትዊተር ፣ በ ፌስቡክ ፣ በቴሌግራም የተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ ገፆቻችን ታገኙናላችሁ