ዶ/ር ብሩክ አለማየሁ (የውስጥ ደዌ ስፒሻሊስት)
በኮሮና ቫይረስ ከተያዙ ወይም ተይዣለው ብለው ከጠርጠሩ ምን ማድረግ ይችላሉ ?
Tweet
ሳል፣ ትኩሳት፣ ትንፋሽ ማጠር እና ተያያዝ ምልክቶች በራስዎ ላይ ከተመለከቱና በኮቪድ-19 እንደተጠቃ ከሚጠረጥሩት ወይም ከተረጋገጠ ሰው ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ከነበርዎት ወይም በኮቪድ19 ወደተጠቁ አገራት/አካባቢዎች ተጉዘው ከነበረ ምን ማድረግ አለብዎት?
- በጣም አለመረበሽ፣ በተቻለ መጠን መረጋጋት
- እነዚህ ምልክቶች በኮቪድ19 ብቻ ሳይሆን በሌሎች በሽታዎችም (ለምሳሌ፡ ጉንፋን፣ ኢንፍሉዌንዛና የአየር ቧንቧ አለርጂ) ሊመጡ እንደሚችሉ አይርሱ፡፡
- ከቤት አለመውጣት፣ ሀኪምዎ ጋር መደወል
- ቀጥታ ወደቤት መሄድ፣ ቤትዎ ውስጥ ካሉ ደግሞ እዛው መቆየት፣ ራስዎን ከሌሎች ሰዎች መለየት፣ ከቤት አለመውጣት (ለህክምና ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር)
- የራስዎ ወይም በስልክ ሊያማክሩት የሚችሉት ሃኪም ካለዎት መደወል፣ ምን ማድረግ እንዳለብዎት ማማከር
- ያንን ማድረግ ካልቻሉ መንግስት ወዳዘጋጀቸው የጥቆማ ቁጥሮች (ለምሳሌ፡ 8335፣ 952…) ደውሎ ማማከር
- የሚሰጥዎን መመሪያ መጠበቅ
- አሁን ባለው ሁኔታ RRT (Rapid Response Team) ማለትም በፍጥነት እንዲመጣ የተመደበ ቡድን ወዳሉበት ቦታ (የጤና ተቋምም ሆነ ቤት ድረስ) በመምጣት ለይቶ ለማቆየት ወደተዘጋጀ ሆስፒታል በአምቡላንስ ይወሰዱ እና አስፈላጊውን ምርመራና ህክምና እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡
- ነገር ግን በበሽታው የሚጠቁ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ሲመጣ ለሁሉም ይህን ማድረግ አስቸጋሪ መሆኑ አይቀርም፡፡ እንኳን በሀገራችን በሰለጠኑት ሀገራት እንኳን ሁሉንም ታካሚዎች መመርመርና ሆስፒታል አስተኝቶ ማከም አስቸጋሪ ከመሆኑ አንፃር በቫይረሱ እንደተያዙ ቢጠረጠር/ቢረጋገጥ እንኳ ያለዎት ምልክቶች ቀላል ወይም መለስተኛ ከሆኑ ህክምናዎትን ቤትዎት ወስጥ ሆነው መከታተል የግድ ሊሆን ይችላል፡፡
- ራስን መለየት (Self Isolation)
- በተቻለ መጠን ቤትዎ ውስጥ ከሚኖሩ ሌሎች ሰዎች ተለይተው በአንድ ክፍል ውስጥ ይቆዩ
- ሌሎች ሰዎች እና የቤት እንስሳት አቅራቢያ ሲሆኑ እና ወደ ሃኪም ቤት ሲሄዱ የፊት ጭንብሎን (facemask) ያጥልቁ
- ሲያስሉና ሲያስነጥሱ ሳልዎን በሶፍት ይሸፍኑ፤ የተጠቀሙበትንም ሶፍት መዘጋት የሚችል ቆሻሻ መጣያ ውስጥ ያስወግዱ
- ካሳሉ ወይም ካስነጠሱ በኋላ እጅዎን በሳሙናና በውሃ ለ20 ሰኮንድ ይታጠቡ፡፡ ካልተቻለ ደግሞ ቢያንስ 60 በመቶ አልኮል ባለው ሳኒታይዘር እጅዎን ያፅዱ፡፡ በተጨማሪም ሽንት ቤት ከሄዱ በኋላ፣ ምግቦን ከማዘጋጀትዎ በፊትና ምግብ ከመብላትዎ በፊት ሁሉ በተደጋጋሚ ይህንን ያድርጉ፡፡
- ዓይንዎን፣ አፍንጫዎን እና አፍዎን ባልታጠበ እጅ አይንኩ፡፡
- የመጠቀሚያ ቁሳቁሶችን ከሌሎች ሰዎች ጋር አይጋሩ፡፡ ለምሳሌ፡ ሳህን፣ ብርጭቆ፣ ኩባያ፣ ማንኪያ፣ ሹካ፣ ሌሎች የመመገብያ እቃዎች፣ አንሶላ፣ ፎጣ፣ ልብሶች እና ሌሎችም
- እነዚህን ከተጠቀሙ በኋላ ሁልጊዜ በሳሙናና ውሃ በደንብ ማጠብ
- በክፍልዎ ያሉ በተደጋጋሚ የሚነኩ ቦታዎችን በየቀኑ ማፅዳት (ለምሳሌ፡ ጠረጴዛ፣ የበር መክፈቻዎች፣ የመብራት ማብሪያ/ማጥፊያዎች፣ ባኞ ቤትና ሽንት ቤት ውስጥ ያሉ እቃዎች፣ ሞባይል ስልክ፣ የኮምፒውተር ኪቦርድ፣ የራስጌ መብራት፣ ኮመዲኖ እና የመሳሰሉት
- እንደ ደም፣ ሽንት፣ ሰገራ እና ሌሎች የሰውነት ፍሳሾች የነካቸው ቦታዎችን በአግባቡ በሳሙናና ውሃ ካጠቡ በኋላ እንደ በረኪና ባሉ ኬሚካሎች ማፅዳት
- የቤት እንስሳትን በተመለከተስ?
- የቤት እንስሳትን በተመለከተ ብዙ መረጃ ባይኖርም ንክኪን ማሰቀረት ይመከራል፡፡
- ከተቻለም ሌሎች የቤተሰብ አባላት ቢንከባከቧቸው ይመረጣል፡፡
- ቤት ውስጥ ሌላ ሰው ከሌለ ግን ራስዎ በሚንከባከቡበት ጊዜ የፊት ጭንብልዎን (facemask) ማጥለቅ፣ ከመንከባከብዎ በፊትና በኋላ እጅን መታጠብ
- ካመመኝ በኃላ በሽታው እንዳይጠነክርብኝ ማድረግ የሚገባኝ ነገር አለ ወይ?
- እስካሁን ድረስ ኮቪድ19ን ለመከላከልም ሆነ ለማከም እንደሚረዳ የተረጋገጠ መደኃኒት የለም፡፡
- ሆኖም ግን የሚከተሉትን ማድረግ ጥሩ ነው፡-
- ሁልጊዜ መተኛት ባይመከርም፣ በቂ እረፍት ማድረግ
- በብዛት ፈሳሽ መውሰድ
- በቂ ምግብ መመገብ
- ትኩሳትና ህመም ከጠነከረብዎት ፓራሲታሞል መውሰድ
- ለስኳር፣ ደም ግፊት፣ አስም እና ለመሳሰሉ ነባር ህመሞች የታዘዙሎትን መድሃኒቶች በአግባቡ መውሰድ፣ ከተቻለ የሚከታተልዎን ኃኪም በስልክ ማማከር
- የህመም ስሜቶችዎን መከታተልና ወደ ሃኪም ቤት መሄድ
- የራስን ሙቀት በቀን ቢያነስ ሁለት ጊዜ እየለኩ መከታተል
- ሳል እና የትንፋሽ ማጠር እየመጣ መሆን አለመሆኑን መከታተል
- ያሉት ስሜቶች በተለይም የትንፋሽ ማጠሩ እየጨመረ ከመጣ ወደ ህክምና ተቋም መሄድ
- በራስዎ ወደሆስፒታል መሄድ ካልቻሉ መንግስት ወዳዘጋጀቸው የጥቆማ ቁጥሮች (ለምሳሌ፡ 8335፣ 952…) በመደወል አምቡንስ እንዲላክልዎ መጠየቅ
- ወደ ሃኪም ቤት ስሄድ ምን ላድርግ?
- ወደ ህክምና ተቋም ከመሄድዎ በፊት ከቻሉ ወደ ሀኪምዎ ወይም ወደተቋሙ አስቀድመው ይደውሉ፡፡
- ወደ ህክምና ተቋም ሲሄዱ የህዝብ መጓጓዣን አይጠቀሙ፡፡
- ወደተቋሙ ከመግባትዎ በፊት የፊት ጭንብልዎን (facemask) ማጥለቅ
- ቶሎ ብለው በኮቪድ19 ተይዘው ሊሆን እንደሚችል ያሎትን ጥርጣሬዎ ለባለሙያዎች ማሳወቅ
- በቫይረሱ ከተያዝኩ በኃላ የሚሻለኝ መቼ ነው?
- የማገገም ፍጥነት እንደ በሽታው ክብደት ደረጃ ይለያያል፡፡
- ቀላልና መለስተኛ ህመም
- ወደ 80 በመቶ የሚሆኑ ሰዎች ቀላልና መለስተኛ ምልክቶች ብቻ ይኖሯቸዋል፡፡
- ከ 1 እስከ 2 ሳምንት ባለው ጊዜ ውስጥ እንደሚያገግሙ ይጠበቃል
- ከባድ ህመም
- ከባድ ህመም የገጠማቸው ሰዎች ለማገገም ስድስት (6) እና ከዚያ በላይ ሳምንታት ይፈጅባቸዋል፡፡
- እስከ መጋቢት 15/2012 ባለው መረጃ መሰረት 20 በመቶ የሚሆኑ ታካሚዎች ከባድ ህመም የገጠማቸው ሲሆን 4.4 በመቶ የሚሆኑት ለ ህልፈተ ህይወት ተጋልጠዋል፡፡
- ነገር ግን ይህ ቁጥር እንደየሃገሩ፣ እድሜ እና ነባር የጤና እክሎች ከ 0.2 እስከ 15 በመቶ ሊለያይ ይችላል፡፡
ምንጮች
https://www.cdc.gov/coronavirus/2019-ncov/downloads/sick-with-2019-nCoV-fact-sheet.pdf
https://www.health.harvard.edu/diseases-and-conditions/coronavirus-resource-center#Sick