በ ሔቨን ምክሩ በሪሁን (የ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የ 5ተኛ ዓመት የ ሕክምና ተማሪ )
Heaven Mekeru Berihun, ( 5 Year Medical Student at St.Paul Hospital Millennium Medical College )
Reviewed and Approved by Dr.Misikr Anberbir (Gynecologist/Obstetrician )
በእርግዝና ጊዜ የሚከሰት የስኳር በሽታ ምንድነው?
በእርግዝና ጊዜ የሚከሰት የስኳር በሽታ የሚባለው አንዲት ከዚህ በፊት የስኳር በሽታ የሌለባት ነፍሰጡር ለመጀመሪያ ጊዜ በእርግዝና ወቅት የስኳር በሽታ እንዳለባት ሲረጋገጥ ነው። ልክ እንደሌሎች የስኳር በሽታ ዓይነቶች፣ በእርግዝና ወቅት የሚከሰት የስኳር በሽታም ህዋሶች(ሴሎች) ስኳር የሚጠቀሙበትን መንገድ ያስተጓጉላል።
መንስኤው ምንድን ነው?
Placenta (የእንግዴ ልጅ) በማደግ ላይ ላለው ህጻን አልሚ ምግቦች እና ውሃ ይሰጣል በተጨማሪም እርግዝናን ለመጠበቅ የተለያዩ ሆርሞኖችን ያመነጫል። እነዚህ ሆርሞኖች የሰውነቷ ሕዋሳት ኢንሱሊንን በአግባቡ እንዳይጠቀሙ ያደርጓቸዋል፣ እንደወትሮው ለኢንሱሊን መልስ መስጠትም ያቆማሉ። ይህም በደም ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን እና የሰውነቷን የኢንሱሊን ፍላጎት ይጨምራል።
በእርግዝና ጊዜ ለሚከሰት የስኳር በሽታ አጋላጭ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?
* ከእርግዝና በፊት ከመጠን ያለፈ ውፍረት መኖር
* አካላዊ እንቅስቃሴ አለማድረግ
*ከእርግዝና በፊት የቅድመ የስኳር (prediabetes) በሽታ መኖር
* በቀድሞ እርግዝና ወቅት በእርግዝና ጊዜ የሚከሰት የስኳር በሽታ ከነበረ
* የስኳር በሽታ ያለበት የቅርብ የቤተሰብ አባል መኖር
* ከዚህ ቀደም 4 ኪሎግራም (ከ9 ፓውንድ) በላይ የሚመዝን ህፃን ልጅ ከወለደች
በእርግዝና ጊዜ የሚከሰት የስኳር በሽታ ምልክቶቹ ምንድን ናቸው?
ብዙ ጊዜ በእርግዝና ወቅት የሚከሰት የስኳር ህመም ግልፅ የሆኑ ምልክቶችን አያሳይም። ነገር ግን ቶሎ ቶሎ ውሀ የመጠማት እና ብዙ ጊዜ የሽንት መሽናት ምልክቶች ሊታዩ ይችላሉ።
እንዴት መከላከል ይቻላል?
በእርግዝና ወቅት የሚከሰት የስኳር በሽታን ለመከላከል ከእርግዝና በፊትም ሆነ በእርግዝና ወቅት ጤናማ የአኗኗር ዘዴዎችን መከተል ጠቃሚ ነው።
* ጤናማ ምግቦችን መመገብ። በፋይበር የበለፀጉ እና ዝቅተኛ ስብ እና ካሎሪ ያላቸው ምግቦችን መምረጥ ጠቃሚ ነው። ፍራፍሬዎች፣አትክልቶች እና እህሎች ላይ በማተኮር የተመጣጠነ ምግብን መመገብ ይመከራል።
* በሳምንት ውስጥ ለተወሰኑ ቀናት እንደ የእግር ጉዞ ያሉ መጠነኛ እንቅስቃሴዎች ማድረግ
* ጤናማ በሆነ ክብደት እርግዝናን መጀመር፦ አንዲት ሴት ለማርገዝ እያሰበች ከሆነ መደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግ እና የአመጋገብ ልምድን በማስተካከል ከመጠን ያለፈ ውፍረትን በመቀነስ በእርግዝና ጊዜ የሚከሰት የስኳር በሽታን መከላከል ትችላለች።
በእርግዝና ጊዜ የሚከሰት የስኳር በሽታ ምርመራ መቼ ይሰራል?
የነፍሰጡሯን እና የልጇን ጤና ለመጠበቅና ህክምና ለመጀመር በእርግዝና ጊዜ የስኳር በሽታ ምርመራ ማድረግ አስፈላጊ ነው።
በእርግዝና ጊዜ የሚከሰት የስኳር በሽታ አብዛኛውን ጊዜ የሚያጋጥመው በ24ኛው የእርግዝና ሳምንት አካባቢ ነው። ስለዚህ አንዲት ነፍሰጡር ለቅድመ ወሊድ ክትትል ወደ ጤና ተቋም ስትሄድ ተጋላጭነቷ ታይቶ በ24 እና 28 የእርግዝናዋ ሳምንታት መካከል ልትመረመር ትችላለች። ለዚህ ምርመራ ልዩ የተዘጋጀ ግሉኮስ ይወሰዳል። ከዚያም በመቀጠል በደምዋ ውስጥ ያለው የስኳር መጠን ይለካል።
ሕክምናው ምንድነው?
በእርግዝና ጊዜ የሚከሰት የስኳር በሽታ ሕክምና በደም ውስጥ የሚገኘውን የስኳር መጠን መቆጣጠር እና በማህፀን ውስጥ የሚገኘውን ህፃን እድገትና ጤንነት መከታተል ላይ ያተኩራል። ጤናማ ምግብን በትክክለኛው ጊዜ መመገብ እና መጠነኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ በደም ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን ይቀንሳል። እንዲሁም ሰውነታችን ኢንሱሊንን በአግባቡ እንዲጠቀም ያደርጋል። ጤናማ አመጋገብ እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የደምን ስኳር መጠን ለመቆጣጠር በቂ ካልሆኑ መድሃኒት ሊጀመር ይችላል።
የሚያስከትላቸው ተዛማጅ የጤና ችግሮች ምንድን ናቸው?
* በእርግዝና ወቅት ለሚከሰት የደም ግፊት መጨመር ያጋልጣል።እንዲሁም በቀዶ ህክምና (C-section) የመውለድ እድልን ይጨምራል።
ከዚህ በተጨማሪም የሚወለደውን ህፃን ለሚከተሉት ችግሮች ሊያጋልጥ ይችላል፦
* ከመጠን በላይ ውፍረት ያለው ህፃን ፦ በደም ውስጥ ያለው የስኳር መጠን ከመደበኛው መጠን ከፍ ያለ ከሆነ የልጁ ክብደት እንዲጨምር ያደርጋል። 4.1ኪሎ እና ከዛ በላይ የሚመዝኑ ህፃናት በወሊድ ጊዜ በማህፀን ውስጥ የመታፈን ችግር ሊያጋጥማቸው ይችላል። ይህንንም ለመከላከል ሲባል በቀዶ ጥገና( C-section) የመውለድ እድልን ይጨምራል።
* ያለጊዜው መወለድ ፦ ቀደም ብለው የተወለዱ ሕፃናት የመተንፈሻ አካላት እድገታቸውን ስላልጨረሱ የመተንፈስ ችግር ሊያጋጥማቸው ይችላል።
* ዝቅተኛ የደም ስኳር (hypoglycemia)፦ አንዳንድ ጊዜ ህፃናት ከተወለዱ ብዙም ሳይቆይ በደም ውስጥ ያለው የስኳር መጠን ዝቅተኛ ይሆናል።በዚህ ጊዜ በፍጥነት የሕፃኑ/ኗን አመጋገብ በማስተካከል በደም ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን ወደ መደበኛው መመለስ አስፈላጊ ነው።
* የሚወለዱት ህጻናት ወደፊት ከመጠን ላለፈ ውፍረት እና ለዓይነት 2 የስኳር በሽታ ተጋላጭ ናቸው።
* ያልታከመ በእርግዝና ጊዜ የሚከሰት የስኳር በሽታ ልጁ ከመወለዱ በፊት በማህፀን ውስጥም ሆነ ከተወለደ በኋላ ብዙም ሳይቆይ የሕፃኑን ሞት ሊያስከትል ይችላል።
ብዙውን ጊዜ ልጁ ከተወለደ በኋላ በእናትየው ደም ውስጥ ያለው የስኳር መጠን ወደ መደበኛው ይመለሳል። ሆኖም 50% የሚሆኑት የእርግዝና ወቅት የስኳር በሽታ የነበረባቸው ሴቶች ወደፊት በዓይነት 2 የስኳር በሽታ ይያዛሉ። የዚህን ተጋላጭነት ለመቀነስ ከወሊድ በኋላ ጤናማ የሰውነት ክብደት እንዲኖራት ይመከራል። ከዚህ በተጨማሪም በየጊዜው ወደ ጤና ተቋም በመሄድ በደሟ ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን መመርመር ተገቢ ነው።
የጤና ወግ
ጠቃሚ እና የተረጋገጠ መረጃ ለጤናዎ ።
የጤና ወግን በነዚህ ሊንኮች መከታትል ይችላሉ ።