በ ዶ/ር ትንሳኤ አለማየሁ 

የ ህፃናት እና ተላላፊ በሽታዎች ሕክምና ስፔሺያሊስት

በጊዜያዊ ከሀገር ወጥተን ለምንመለስ ኢትዮጵያውያን የመንግስት ድጋፍ ታክሎበት በትንሹ ለ14 ቀናት ቤታችን ውስጥ ራሳችንን ብንገድብ ለግልም፣ ለቤተሰብም፣ ለሀገርም የተሻለ የበሽታ መከላከያ መንገድ ነው፡፡

መጋቢት 2 ቀን 2012 አ.ም. የአለም የጤና ድርጅት ባስተላለፈው ሰርኩላር መሰረት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በ79 ሀገራት (8 የአፍሪካ ሀገራትን ጨምሮ) ተሰራጭቷል፡፡ ከነዚህ 79 ሀገራት ውስጥ የኢትዮጵያ የአየር መንገድ በቀጥታ በረራ (በሌሎች የአየር መንገዶች በቦሌ አለምአቀፍ ኤርፖርት ትራንዚት የሚያደርጉትን ሳይጨምር) ከ41 ሀገራት ጋር ይገናኛል፡፡

ኢትዮጵያ ካላት ተጋላጭነት እና ከህዝባችን መብዛት አንፃር የተጋለጠውን ተጓዥ ከቤተሰብ እና የስራ ባልደረቦች ጋር ሁሉንም ለመመርመር በቂ መሳርያ አለን ማለት የዋህነት ነው፡፡ ያደጉት ሀገራት እንኳን የቫይረሱን የመስፋፋት ከመመርመሪያ እቃዎች አቅርቦት ጋር ማስታረቅ ከብዷቸዋል፡፡ በጣልያን ሀገር ያላቸውን መጠነኛ ባለሙያ እና መሳርያ በጣም ለተጎዱት ወይም ለከፋ ጉዳት ይጋለጣሉ ለተባሉት ለአረጋውያን እና የበሽታ የመከላከል አቅማቸውን ያዳከመ ህመም ላለባቸው ብቻ እየተጠቀሙ ነው  (The Atlantic) 

ስለዚህም በጊዜያዊ ከሀገር ወጥተን ለምንመለስ ኢትዮጵያውያን የመንግስት ድጋፍ ታክሎበት በትንሹ ለ14 ቀናት ቤታችን ውስጥ ራሳችንን ብንገድብ ለግልም፣ ለቤተሰብም፣ ለሀገርም የተሻለ የበሽታ መከላከያ መንገድ ነው፡፡ ይህን ስናደርግ የህመም ምልክት ቢኖረንም ባይኖረንም፣ ከላይ የተጠቀሱት ሀገራት ብንሄድም ባንሄድም መሆን አለበት፡፡ 

ብንታመም ሀገራችን በእርዳታ ከምታገኘው ጥቂት ከሆኑት መመርመርያዎች በመጠቀም ራሳችንን ለማወቅ ለከፋ ጉዳት ይጋለጣሉ ከተባሉት ቡድን ውስጥ ካልሆንን አንችልም (ከላይ ይመልከቱ)፡፡ ይህንን ስል እውነታውን ለማስረዳት ነው እንጂ የኢትዮጵያን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የመከላከል ስራን ለመውቀስ አይደለም፡፡ አሜሪካን ጨምሮ በመላው አለም የመመርመሪያ እቃ እጥረት ተከስቷል ‘ (usatoday )  ፡፡ 

በነዚህ 14 ቀናት ስራችንን ከቤት ሆነን መስራት ከቻልን ጥሩ ነው፡፡ ካልሆነ ግን ካለው ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት ለ14 ቀናት ቤት ውስጥ ሆኖ ከአቅም በላይ አስገዳጅ ሁኔታ ካልሆነ (እሱም በጥንቃቄ) አለመውጣት የግድ ነው፡፡ መስሪያ ቤቶችም ይህንን ለየት ያለ አጋጣሚ በመገንዘብ ከሰራተኞች ጋር ላለመጋጨት አሰራራቸውን ማስተካከል ያስፈልጋቸዋል፡፡ ሲሆን በይፋ ይህንን አስመልክቶ ጊዜያዊ ሀገራዊ ህግ መውጣት አለበት፡፡