ዶ/ር ብሩክ አለማየሁ (የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት)

አንድ ሰው በቫይረሱ እንደተጠቃ ከተረጋገጠ በኃላ እና ሆስፒታል እንዲተኛ (Admission) ከተደረገ በኋላ ከሆስፒታል ወጥቶ ወደ ቤት ለመመለስ (Discharge)ማሟላት የሚጠበቅበት መለኪያዎች አሉ፡፡

አንድ ሰው በቫይረሱ እንደተጠቃ ከተረጋገጠ በኃላ እና ሆስፒታል እንዲተኛ (Admission) ከተደረገ በኋላ ከሆስፒታል ወጥቶ ወደ ቤት ለመመለስ (Discharge)ማሟላት የሚጠበቅበት መለኪያዎች አሉ፡፡ እነዚህን መለኪያዎች ሲያስሰፍሩ ሀገራት ግንዛቤ ውስጥ መክተት ያለባቸው ነገሮች አሉ፡፡ እነዚህም፡ የጤና ስርዓቱ አቅም፣ የላቦራቶሪና ተያያዝ አቅም እና የወረርሽኙን ባህሪ ናቸው፡፡

ከዚህ የተነሳ መለኪያዎቹ ከሀገር ሀገር የተወሰኑ ልዩነቶች ቢኖሯቸውም በአብዛኛው ግን ተመሳሳይ ናቸው፡፡

እነዚህ መለኪያዎች ምንድን ናቸው?

  1. ቢያንስ ለ48 ሰዓት (2 ቀናት) ያለምንም ማስታገሻ ከትኩሳት ነፃ መሆን አለበት (አንዳንድ መመሪያዎች ›3 ቀናት ይላሉ)
  2. ሌሎች የመተንፈሻ ችግር ምልክቶች (ለምሳሌ ሳል፣ ማፈን) ከፍተኛ መሻሻል ማሳየት አለባቸው፡፡
  3. በራጅ ወይም ሲቲ ስካን መጀመሪያ ላይ ምልክቶች ከነበሩ ለውጥ ማሳየት መጀመር አለባቸው፡፡
  4. እንደ ስኳር፣ ደም ግፊት ያሉ ነባር ህመሞች የተረጋጋ (Stable) ሁኔታ ላይ መሆን አለባቸው፡፡
  5. ቢያንስ ሁለት ጊዜ የrRT-PCR ምርመራ ኔጌቲቭ መሆን አለበት (በሁለቱ ምርመራዎች መሃል ቢያንስ የ24 ሰዓት ልዩነት መኖር አለበት)፡፡

IgG የተባሉት የሰውነታችን መከላከያ ኬሚካሎች (antibodies) መታየት መጀመራቸውን እንደ አንድ መለኪያ የተጠቀሙበትም አሉ (ለምሳሌ፡ ጣልያን)፡፡

የrRT-PCR ምርመራ መደረግ ያለበት መቼ ነው?

ምልክት ለነበራቸው፡- ምልክቶች ከጀመሩ ቢያንስ ከ7 ቀናት በኋላ እና ትኩሳት ከጠፋ ከ 3 ቀን በኋላ

ምልክት ሳይኖራቸው ተመርምረው ፖዘቲቭ ለሆኑ፡ ከመጀመሪያው ምርመራ ከ14 ቀናት በኃላ

ሆኖም ግን ወረርሽኙ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ከደረሰ እና ከሀገሪቱ ላቦራቶሪ የመመርመር አቅም በላይ ከሆነ ወይም የጤና ስርዓቱን ካጥለቀለቀ (overwhelm) አማራጭ መለኪያዎችን መጠቀም ግድ ይላል፡፡

ለምሳሌ፡ መለስተኛ ህመም ብቻ ያላቸውን ታካሚዎች የላቦራቶሪ ምርመራ ሳያደርጉ ከሆስፒታል እንዲወጡ ማድረግ ሊያስፈልግ ይቻላል፡፡

የአሜሪካው CDC ምርመራ ማድረግ በማይቻልባቸው ጊዜዎች መሟላት የሚገባቸውን መለኪያዎች አስቀጧል፡፡

  1.  ትኩሳት ከጠፋ ቢያነስ 3 ቀናት ከሆነ እና ሌሎች ምልክቶችም ከፍተኛ መሻሻል ካሳዩ
  2. ምልክቶች ከጀመሩ ቢያንስ 7 ቀናት ካለፉ

እነዚህን የሚያሟሉ ታካሚዎች የላቦራቶሪ ምርመራ ሳያደርጉ ከሆስፒታል እንዲወጡ እና ቤት ሲገቡ ግን ለ14 ቀናት ክትትል እየተደረገ ራሳቸውን ለይተው እንዲቆዩ ማድረግን እንደ አማራጭ መጠቀም ይቻላል፡፡

ቤት ሲቆዩ ራስን ከመለየት አንፃር ሊደረጉ ስለሚያስፈልጉ ጥንቃቄዎች ማወቅ ከፈለጉ እዚህ ይመልከቱ፡፡

ነገር ግን ቫይረሱ ለረጅም ጊዜ እንደሚቆይባቸው የሚታወቁ ታማሚዎች በዚህ መልክ መስተናገድ የለባቸውም፡፡

እነዚህም፡-

  1. በፅኑ የታመሙ
  2. የመከላከል አቅማቸው በከፍተኛ ደረጃ የወረደ
  3. ወደ እንክብካቤ ማዕከላት የሚመለሱ (ለምሳሌ እንደ ሜቄዶንያ መርጃ ማዕከል)

ከሆስፒታል ከተወጣ በኃላ ሊደረግ የሚገባ ጥንቃቄ

  1. ለሁለት ሳምንታት (14 ቀናት) ራስን ለይቶ መቆየት
  2. ልዩ ስሜት ካለ ለህክምና ቡድኑ ማሳወቅ
  3. ከወጡ ከ14 ቀናት በኃላ ቀርቦ መታየት (followup visit)

የቫይረሱ ዘረ-መል ለተወሰኑ ሳምንታት በሰውነት ፈሳሽ ውስጥ መታየቱ ሊቀጥል ይችላል፡፡ ነገር ግን መታየቱ ብቻ ታካሚው ለሌሎች የማስተላለፍ አቅም እንዳለው አያረጋግጥም፡፡ ከዚህ አንፃር ብዙ የማናውቃቸው ነገሮች ስላሉ ከላይ የተጠቀሱትን የጥንቃቄ መመሪያዎች መከተል ይመረጣል፡፡

በአሁኑ ወረርሽኝ በቫይረሱ ተጠቅተው ከዳኑ በኋላ እንደገና ምርመራቸው ፖዘቲቭ ውጤት ያሳየባቸው ታካሚዎች ታይተዋል፡፡ ነገር ግን ይህ እንደገና በቫይረሱ ተይዘው ነው ወይስ ከጅምሩም ከቫይረሱ ነፃ አልሆኑም ነበር የሚሉት ሃሳቦች እያወዛገቡ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ አንፃር ወደ እርግጠኝነት የሚወስድ (conclusive) የጥናት ውጤት እስኪገኝ ድረስ ከህመሙ ያገገሙ ሰዎች ለሁሉም የሚመከሩትን ጥንቃቄዎች እንዲተገብሩ ይመከራል፡፡

ምንጮች

  1. http://mohs.gov.mm/Main/content/publication/discharge-criteria-for-covid-19
  2. https://www.ecdc.europa.eu/sites/default/files/documents/COVID-19-Discharge-criteria.pdf
  3. https://www.england.nhs.uk/coronavirus/secondary-care/discharge/discharge-advice/
  4. https://www.cdc.gov/coronavirus/2019-ncov/hcp/disposition-hospitalized-patients.html
  5. https://www.who.int/docs/default-source/coronaviruse/who-china-joint-mission-on-covid-19-final-report.pdf �qb��.

የጤና ወግ

በመረጃ የተመሰረተ ሕክምና ብቻ ።  

………………………………………………………………………………………………………………………..

ይህ የጤና ወግ ድረ ገፅ ነው።
ስለ ጤንነታችሁ ማወቅ የምትፈልጉትን መረጃ የምታገኙበት ፣ በህክምና ባለሙያዎች የሚዘጋጅ የመረጃ ምንጭ ነው።
ሁልግዜም ከሀኪማችሁ ተማከሩ፣ ተጨማሪ መረጃ ከፈለጋችሁ የኛን ድረ ገፅ ጎብኙ።

በጥናት የተደገፈ መረጃ ብቻ እናቀርባለን።

የህክምና ባለሙያዎች ለህሙማኖቻችሁ የሚሆን የሚነበብ መረጃ ከፈለጋችሁ ይህን ግፅ ጠቁሟቸው። ህሙማኖቻችሁ እንዲያውቁት የምትፈልጉትን ነገር መረጃ ጠቅሳችሁ ፃፉልን፣ ስምችሁን ጠቅሰን እናወጣለን። የህክምና ተማሪዎች እንዲጽፉ እናበረታታለን።

በተጨማሪም በጤና ወግ ፖድካስት፣  በ ዩትዩብ ፣በ ትዊተር ፣ በ ፌስቡክ ፣ በቴሌግራም የተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ ገፆቻችን ታገኙናላችሁ ።

Share this: