በ ዶ/ር ትንሳኤ አለማየሁ / የሕፃናት እና የተላላፊ በሽታዎች ስፔሻሊስት, (የጤና ወግ )

የአሜሪካን ሃገር ፕሬዝዳንት ከቀናት በፊት በመግለጫቸው ሃይድሮክሲክሎሮክዊን የሚባለውን መድሃኒት         ለኮሮናቫይረስ ህመም መድሃኒት መሆኑን በመናገራቸው ብዙ አላስፈላጊ መደናግሮችና ጉዳቶች አስከትሏል። በናይጄሪያ ውስጥ ሁለት ሰዎች ይሄን መድሃኒት አላግባብ ከመውሰድ ጋር በተያየዘ መሞታቸውን የተለያዩ የዜና ተቃማት ዘግበዋል። ፕሬዝዳንቱ ይህን ያሉት ይህ መድሃኒት ኮሮናቫይረስ ላይ ያለውን ጥቅምና ጉዳይ ገና በባለሞያዎች ሳይረጋገጥና ስምምነት ሳይደረስበት ነበር።  የአሜሪካው የመድሃኒት አና ምግብ አስተዳደር ለ ኮቪድ 19 ይጠቅማል ብሎ ያፀደቀው መድሃኒት አስካሁን የለም።  

ሃይድሮክሲክሎሮክዊን እና ክሎሮክዊን ለ አዲሱ የ ኮሮና ቫይረስ ሕክምና ሊጠቅም ይችላል የሚለው ሃሳብ የመጣውና የአሜሪካው ፕሬዚዳንትም ያስተጋቡት በጣም ትንሽ ከሆኑ ጥናቶች ተነስተው ነው። ትክክለኛ አና ተአማኒ የሆነ ጥናት አስካሁን አልተደረገም።  እንደዚህ ያሉ አደገኛ የሆኑ ስህተቶችን ለማስወገድ መድሃኒትን እና በሽታን የተመለከቱ ማናቸውንም መግለጫዎች የህክምና ባላሙያዎች ብቻ ቢሰጡ ይመረጣል። ይህንን በተመለከተ የ አሜሪካንን የኮሮና ቫይረስ መከላከል እርምጃ የሚመሩት Dr Fauci  ያሉት ለሁላችንም የሚሆን መልክት ነው ።

አንደ ምሳሌ አንዱን ጥናት ወስደን ብናይ  ተመራማሪዎቹ በመጀመሪያ 36 ሰዎች ላይ ጥናታዊ የሆነ ምርመራ እንዲያደርጉ ተጋበዙ፤ ምርመራው ሃይድሮክሲክሎሮክዊን የተባለው መድሀኒት ለCOVID19 ላይ ያለውን ጥቅምና ጉዳት ማወቅ ነበር።  ከነዚህ 36 ሰዎች መሃል 20ዎቹ ለጥናቱ ተስማምተው መድሃኒቱን መውሰድ ሲጀምሩ የተቀሩት 16 ደግሞ መድሃኒቱን አንውስድም አሉ። ሃኪሞቹ ሁለቱንም (መድሃኒቱን የሚወስዱትንም ያልወሰዱትንም) ቡድኖች ለ6 ቀናት ክትትል አደረጉላቸው። ነገር ግን ተመራማሪዎቹ ከዚህ ጥናት ተአማኒ ውጤት ለማግኘት በሺዎች የሚቆጠሩ ታማሚዎችን መከታተል እንዳለባቸው ስለተረዱ አሁን ይህን ጽሁፍ በሚያነቡበት ሰአት ጥናቱ እንደቀጠለ ነው፡፡ ይህም ይሄ መድሃኒት COVID19ን ላይ ያለው ፍቱንነት ገና አልተረጋገጠም ማለት ነው።

ሆኖም በዚህ ጉዳይ ካለው የመረጃ ጥማት በመነሳት ጥናቱን ሊሰሩባቸው ካቀዱባቸው ከሺዎች የሚቆጠሩ ታማሚዎች ውስጥ ገና የመጀመርያዎቹን 36 ሰዎች ውጤት ይፋ አድርገዋል፡፡ በውጤቱም መሰረት ሃይድሮክሲክሎሮክዊን መድሃኒትን የወሰዱት የመጀመሪያዎቹ 20 ሰዎች መድሃኒቱ መውሰድ በጀመሩ በስድስተኛ ቀናቸው የነበራቸው የSARS-CoV-2 (የCOVID19 ህመም አምጪ ቫይረስ) መጠን ሲለካ ከሁለተኛው ቡድን አንፃር አነስተኛ እንደነበር ገልፀዋል፡፡

ከዚህ በፊት እንደሚታወቀው እንደ ጉንፋን ባሉ በተመሳሳይ የመተንፈሻ አካላት የቫይረስ ህመሞች ተይዘው የሚድኑ ታካሚዎች በመድሀኒት እርዳታ ሳይሆን የቫይረስ ህመሙ የተመደበለትን የቆይታ ጊዜ በማጠናቀቁ ምክንያት ቁጥሩ ሲቀንስ ይታያል፡፡ ስለዚህ ከላይ በተገለጸው ጥናት የታየው የቫይረስ መጠን ቅናሽን ከተሰጠው የሙከራ መደሀኒት ጋር ማገናኘት ለብዙ ሞያተኞች ከብዷል፡፡ በተጨማሪም በዚህ ጥናት ውጤት ላይ ተመስርቶ በአለም ላይ ላሉ በዘር፣ በቀለም፣ በጾታ፣ በእድሜ እና በሌሎች ብዙ ነገሮች ለሚለያዩ ታማሚዎች ህከምና መስጠት አስቸጋሪ ነው፡፡ 

ይሄን በቀላል ምሳሌ ለማስረዳት ፣  እንበል እና ከአዲስ አበባ በመነሳት ወደ ናይሮቢ የመኪና መንገድ ጉዞ ለመጀመር ብታስቡ ምን ምን ጥያቄዎችን ታነሳላችሁ? የመንገዱ ጥራት እንዴት ነው? የፀጥታው ሁኔታስ? እስከ ናይሮቢ ያለው የአየር ፀባይ ምን ይመስላል? መንገድ የማያሳልፉ ዝናባማ ጎርፋማ ቦታዎች አሉ? ግድ በመኪና መሄድ አለብኝ ወይስ ሌላ አማራጭ አለኝ? የመሳሰሉትን ትጠይቃላችሁ። አንድ ሺ አምስት መቶ ሀምሳ ሶስት (1553) ኪሜ. ስለሚረዝመው ከአዲስ አበባ ናይሮቢ ድረስ ስላለው መንገድ ጠይቃችሁ የምታገኙት ምላሽ “ከአዲስ አበባ  ሞጆ (70 ኪ.ሜ.) ምርጥ መንገድ ነው” ቢሆንስ? እየነዳችሁ ትሄዳላችሁ?

ሃይድሮክሲክሎሮክዊን/ ክሎሮክዊን ምን አይነት መድኃኒቶች ናቸው? 

እነዚህ መድኃኒቶች የወባ በሽታን ለመከላከል እና ለማከም የሚያገለግሉ  ሲሆን የሩማቶይድ አርትራይተስ እና ሉፐስ የሚባሉ (Autoimmune diseases ) ለማከምም እንጠቀምባቸዋለን ። ሆኖም እነዚህ መድኃኒቶች የራሳቸው የጎንዮሽ ጉዳት አላቸው። ያለ በቂ ማስረጃ እና ጥናት ማንም ሊጠቀማቸው አይገባም።  በሌሎች ሀገሮች እንዳየነው ሰዎች ካልተረጋገጡ ቦታዎች በሰማቸው ዜናዎች ለከፍተኛ ጉዳት  አልፎም ለሞት ሲዳረጉ አይተናል።  ይሄ ነገር አኛም ሀገር አንዳይደገም የጤና ጥበቃ አና የመድሃኒት አቅርቦት ባላስልጣን አስቀድመው ጥንቃቄ ሊወስዱ ይገባል።

ምን አይነት የጎንዮሽ ግዳት አላቸው

ሃይድሮክሲክሎሮክዊንም ሆነ ክሎሮክዊን በተወሰኑ ተጠቃሚዎች ላይ 

የአጥንት መቅኔ ጉዳት (የደም ማነስ፣ የነጭ ሴል መጎደልን ጨምሮ)፣ 

ራስ ምታት፣ 

የመስማትና የማየት አቅምን መቀነስ 

የደም የስካር መጠን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ 

የልብ ጉዳት፣ በተለይ ደግሞ የልብ አመታት መዛባትን እና ድንገተኛ ሞትን ሊያመጡ ይችላሉ።

ለዛም ነው ተጨማሪ መረጃ ሳይኖር የተካለበ የህክምና ውሳኔ ማድረግ የሌለብን። ተጠቃሚዎችም ያለህክምና ትእዛዝ ላልተፈለገ ጉዳት ሊዳርግ የሚችልን መድሀኒት ገዝቶ መጠቀም የለባቸውም፡፡

የጤና ወግ ። ሁሌም በጥናት የተደገፈ መረጃ ብቻ እናቀርባለን።