በዶ/ር ትንሳኤ አለማየሁ (የህፃናት ህክምና እስፔሻሊስትና የተላላፊ በሽታዎች ሰብ–እስፔሻሊስት)
በአለም ዙርያ በአመት ከ220 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በወባ ህመም ይጠቃሉ፡፡ ህመሙ ከፍተኛ የሞት ቁጥር ከሚያስከትሉ ተላላፊ በሽታዎች አንዱ ሲሆን በአመት ከ405000 በላይ ሰዎችን (በአብዛኛው እድሜያቸው ከ5 አመት በታች የሆኑ አፍሪካውያን ልጆችን) ይገላል (1) ፡፡ የወባ ህመም ከጊዜያዊ ህመሙ ባሻገር በተለይም ከባህር ወለል ከ1400 ሜትር ከፍታ በታች በሆኑ አካባቢዎች በተደጋጋሚ በመከሰት የደም ማነስ፣ የእድገት መቀጨጭ፣ ተደጋጋሚ በህመም የሚከሰት የትምህርት መቋረጥ በማስከሰት እና በዘላቂነት ወደ ሙሉ አቅማቸው የሚገኙ ምርታማ ዜጎች እንዳይቀየሩ ያደርጋል፡፡ ከፍተኛ ስርጭት ያለባቸው ከሰሀራ በታች የሚገኙ ሀገራት ባባዛኛው ህፃናት እና ወጣቶች የሚገኙበቸው ሲሆኑ (ለምሳሌ አማካይ የህዝቧ እድሜ 19 አመት የሆነችው ኢትዮጵያ) በአለም ካለው የወባ ስርጭት ሁለት ሶስተኛውን ይሸከማሉ፡፡
ለአመታት የወባ ህመምን ለመከላከል ፀረ-ነፍሳት ኬሚካሎች፣ አጎበሮች፣ የታቆረ ዉሀን ተከታትሎ በማጽዳት፣ በምሽት እጅጌ ሙሉ ልብሶችን በመጠቀም፣ ከፍተኛ የህመሙ ስርጭት ወዳለባቸው ቦታዎች ጉዞ ስናደርግ መከላከያ መድሀኒቶችን በመውሰድ በግለሰብ ደረጃ ወይም በማህበረሰብ ውስጥ የወባ ህመም እንዳይከሰት ስንጥር ቆይተናል፡፡
ለተለያዩ የባክቴርያ እና የቫይረስ ህመሞችን በክትባት የመከላከል ከ100 አመት በላይ ያሰቆጠረ ተሞክሮ ቢኖርም እንደ ወባ ህመም ያሉን በፓራሳይቶች የሚከሰቱ ህመሞችን በሚከሰቱበት ጊዜ ከማከም የዘለለ ለአንዳቸውም ክትባት ተገኝቶ አያውቅም፡፡ በዚህ ሳምንት በይፋ ከአለም የጤና ድርጅት ይሁንታን ያገኘው የወባ ክትባት ወይም የሞስኩዊሪክስ ወይም የ RTS-S/AS01 ክትባት ይህንን ክፍተት ለመጀመርያ ጊዜ የቀረፈ ታሪካዊ የህክምና ግኝት ነው፡፡
ይህ የወባ ክትባት ሰርከምስፖሮዞይት በተባለው የወባ ህመም አምጪ ተሃዋስ ውስጥ የሚገኝ ፕሮቲን ላይ መሰረት ተደርጎ የተፈበረከ ሲሆን ውጤታማነቱ ላይ መጀመርያ ጥናቶች መደረግ ከጀመሩ ከ35 አመት በላይ ይሆናል፡፡ በቅድሚያ ወረርሽኙ በስፋት ከሚያጠቃቸው ከሰሀራ በታች ካሉ የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ በሶስቱ ማለትም በጋና፣ በኬንያ እና በማላዊ በሚገኙ እድሜያቸው ከ2 አመት በታች በሆኑ ህፃናት ላይ ጥናቶች መደረግ የጀመሩ ሲሆን የመጀመርያዎቹ ውጤቶች አበረታች አልነበሩም፡፡ በነዚህ የመጀመርያ ጥናቶች የተሰጡት በ4 ዙር የተሰጡ ክትባቶች 36 ከመቶ ብቻ የመከላከል አቅም ያሳዩ ነበሩ(2)፡፡ በክትባት ህክምና በአብዛኛው አንድ አዲስ ክትባት ወደ ህብረተሰብ የጤና ፕሮግራሞች ከመቀላቀላችን በፊት በትንሹ እንዲከላከል የታሰበለትን ህመም 75 ከመቶ የመከላከል አቅም እንዲያሳይ ይጠበቃል፡፡ በተከታታይ በተደረጉ ጥናቶች (በተለይም በ2021 እ.ኤ.አ. በታተሙ የምርምር ውጤቶች እንዳሳዩን) የክትባቱን የመከላከል አቅም የሚጨምሩት ፕሮቲኖች ወይም Adjuvants አቅም በማሳደግ እና በማሻሻል የ RTS-S/AS01 የወባ ህመም ክትባት የተሻለ ውጤታማ እንዲሆን አስችለውታል፡፡
በምእራብ አፍሪካ በተለይም በቡርኪና ፋሶ እና በማሊ በሚገኙ በመቶ ሺዎች በሚቆጠሩ እድሜያቸው ከ2 አመት በታች በሆኑ ህፃናት ላይ ከ2019 እ.ኤ.አ ጀምሮ የተደረጉ ጥናቶች በተሻሻለ መልክ የተዘጋጀው የ RTS-S/AS01 የወባ ህመም ክትባት በ4 ዙር በሚሰጥበት ጊዜ የወባ ህመም የመከላከል አቅሙ በእጥፍ በማደግ እስከ 77 ከመቶ የመከላከል አቅም እንዳለው አሳይተዋል (3)፡፡
ይህ የክትባት ግኝት በዚህ ወቅት ለህክምና መቅረቡ ሌላው ጥቅም በየአመቱ እየጨመረ የመጣው መድሀኒትን የለመደ የወባ ህመም ስርጭት ነው፡፡ እንደ ክሎሮክዊን የመሳሰሉ የወባ መድሀኒቶችን የመላመድ አዝማሚያ በኢትዮጵያ መታየት ከጀመሩ ከ15 አመት በላይ ይሆናል፡፡ በነዚህ ጊዜያት በቢሾፍቱ (4)፣ በሃላባ (5) እና በመሳሰሉ አካካቢዎች የተሰሩ ጥናቶች የፕላስሞድየም ቫይቫክስ የወባ አምጪ ተህዋስ እስከ 15 በመቶ ድረስ ክሎሮክዊንን የመላመድ ሁኔታን አሳይቶ ነበር፡፡ በበፊት ጊዜያት በሩቅ ምስራቅ ሀገራት ብቻ ይታይ የነበረው እና ከአብዛኞቹ የወባ መድሀኒቶች ውጤታማ የሆኑት የአርቲሜተር ዘር መድሀኒቶቸ የመላመድ አደጋ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በምስራቅ አፍሪካ በተለይም በዩጋንዳ ታይቷል (6)፡፡ ስለዚህም የአዳዲስ የወባ ህመም መድሀኒቶች ግኝት እና ምርምር ፍጥነት እና የመድሀኒትን የተላመደ የወባ ህመም መስፋፋት ፍጥነት ሊጣጣም ስለማይችል መከላከልን መሰረት ያደረገ ህክምና ትኩረት ያሻዋል፡፡ ለዚህም በዚህ ሳምንት ግልጋሎቱ የፀደቀው የ RTS-S/AS01 የወባ ክትባት ከፍተኛ ጥቅም ይኖረዋል፡፡
ምንጭ:
- https://www.who.int/news-room/fact-sheets/detail/malaria
- https://pubmed.ncbi.nlm.nih.gov/25913272
- https://www.thelancet.com/journals/lancet/article/PIIS0140-6736(21)00943-0/fulltext
- https://malariajournal.biomedcentral.com/articles/10.1186/1475-2875-7-220
- https://parasitesandvectors.biomedcentral.com/articles/10.1186/1756-3305-4-46
- https://www.nejm.org/doi/full/10.1056/NEJMoa2101746?query=TOC