(በ ዱሬቲ ጋሮማ በጎንደር ዩ/ህ/ጤ/ሳ/ኮ የህክምና ተማሪ- C2)
ቀላል የሚባሉትን ኢንፌክሽኖች ማከም የማንችልበት ጊዜ ሊመጣ እንደሚችል ያውቃሉ?
የተለመዱትን እንደ ሳምባ ነቀርሳ ፣ ሳንባ ምች ፣ ጨብጥ እና እንደ ምግብ ወለድ ያሉ ኢንፌክሽኖችን ማከም ከባድ እየሆነ ነው፡፡ይህም እየጨመረ ከመጣው የባክቴርያዎች ፀረ ባክቴርያን መላመድ ጋር የተያያዘ ነው፡፡እስከዛሬ የምንጠቀምበትን በሰር አሌክሳንደር ፍልሚንግ የተሰራውን ፔንሲሊን የተሰኘውን የመጀመሪያ ፀረ-ባክቴሪያ ጨምሮ በኋላም የመጡ ፀረ-ባክቴሪያዎች የአለምን ህዝብ ጤና ለበጎ ከቀየሩ ግኝቶች ዋነኞቹ ናቸው፡፡በዚህ ግኝት ምክንያት ገዳይ የነበሩ ኢንፌክሽኖችን በቀላሉ ማከም ተችሏል፡፡ አሁን ላይ ግን ፀረ-ባክቴሪያን በግድየለሽነት በመጠቀማችን ማለትም ለጉንፋን እና ለሆድ ቁርጠት ሁሉ ያለምርመራ እንደ አሞክሳሲሊን አምፒሲሊን ያሉ ፀረ-ባክቴሪያዎችን በመውሰዳችን ወደ ቅድመ ፀረ-ባክቴሪያ ዘመን ወደመመለስ ጎዳና ላይ ያለን ይመስላል፡፡እያየን ያለነው ፀረ-ባክቴሪያን በተላመዱ ባክቴሪያዎች እየተከሰተ ያለዉ የሞት ቁጥር በእጅጉ ያሳስባል፡፡በ2017 በተጠናዉ ጥናት በዐለም ደረጃ በዐመት 700000 ሞት በመድሀኒት መላመድ ምክንያት ተከስቷል፡፡
የፀረ-ባክቴሪያ መላመድ ምንድን ነው ? እንዴትስ ይከሰታል?
ባክቴሪያዎች እንዲያጠፋቸው ታስቦ የሚሰጠውን መድሃኒት ተቋቁመው መኖር ሲችሉ ፀረ-ባክቴሪያውን ተላመዱ ይባላል፡፡ የማይገል ነገር ያጠነክራል ሲባል ሰምተን ይሆናል፣ ይህ ስሌት ለባክቴሪያም ይሰራል፡፡ ባክቴሪያዎች ለማያጠፋቸው የፀረ-ባክቴሪያ መጠን በተጋለጡ ቁጥር ተላምደው መኖር የሚያስችላቸውን ዘረመል ይፈጥራሉ፣ በሌላ ጊዜም ፀረ-ባክቴሪያውን በመቋቋም አይጠፉም ማለት ነው፡፡ ይህ ፀረ-ባክቴሪያን በአግባቡ ባለመጠቀም የሚከሰት ነው፡፡
አግባብ ያለው የፀረ-ባክቴሪያ አጠቃቀም ምንድን ነው?
በጤና ባለሙያ ትዕዛዝ በትክክለኛው መጠን፣ የጊዜ ርዝመት፣ የጊዜ ልዩነት እና ለትክክለኛው ምክንያት መውሰድ ነው፡፡ ከዚህ ያፈነገጠ ማንኛውም አይነት የፀረ-ባክቴሪያ አጠቃቀም ያላግባብ ሊባል ይችላል፡፡ በሀገራችንም ይህ ያላግባብ አጠቃቀም ተንሰራፍቶ ይገኛል፡፡ራስን በራስ የማከም ልምዳችን ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ይህም እራሳችን በሽታችንን ገምተን መድሀኒት የምናዝበት ሁኔታ ነው፡፡በመድሃኒት ቤቶች ያለ ትዕዛዝ ወረቀት ፀረ-ባክቴሪያን ማግኘቱ ጥፋቱን ያባብሰዋል፡፡
ፀረ-ባክቴሪያዎችን እንደ ህመም ማስታገሻ በመቁጠር የበሽታው ምልክት ስለጠፋ መድሃኒቱን ማቋረጥ ከተለመዱት የስህተት አካሄዶች አንዱ ነው፡፡ መካፈል በባህላችን የሚመሰገን ቢሆንም ፀረ-ባክቴሪያን ተካፍሎ መጠቀም ግን እንደ ችግር የሚታይ ነው፡፡
የጤና ባለሞያዎች የመድሃኒት ትዕዛዝን በሚፅፉበት ጊዜ መካተት የሚገባውን መረጃ በሙሉ በአግባቡ ባለማካተታቸው እና ለታካሚው ለመረዳት ቀላል በሆነ መልኩ የመድሃኒቱን አወሳሰድ ባለማስረዳታቸው ምክንያት የሚከሰተው ያላግባብ አጠቃቀም ቀላል አይደለም፡፡
ይህ በህክምና አሰጣጡ ላይ እየፈጠረ ያለው ተግዳሮት ምንድነው?
በሀገራችን እየተከሰተ ያለው የፀረ-ባክቴሪያ መላመድ ውጤታማ እና የተሳካ የሆነን የኢንፌክሽን በሽታዎችን ህክምና ስጋት ውስጥ ከቶታል፡፡ ምክንያቱም እጃችን ላይ በነበሩ ፀረ-ባክቴሪያዎች ሲታከሙ የነበሩ በሽታዎች ምላሽ የማይሰጡ እየሆኑ በመምጣታቸው ነው፡፡ ይህም ሞትን እና የተለያዩ የጤና እክሎች እያስከተለ ይገኛል፡፡
እንደ ሀገር ከኢኮኖሚያዊ ጉድለታችን ላይ ቀንሰን የምናመርታቸውም ሆነ ከውጪ የምናስገባቸው ፀረ-ባክቴሪያዎች በባክቴሪያዎች መላመድ ምክንያት ከጥቅም ውጪ እየሆኑ ነው፡፡ ይህ ለከፍተኛ ወጪ ዳርጎናል፡፡ እንደ ግለሰብም ቢሆን በህክምና ተቋማት ውስጥ ያለንን ቆይታ በማራዘም ላልታሰበ ወጪ ይዳርጋል፡፡
በ2050 በመድሀነኒት መላመድ ምክንያት ይከሰታል ተብሎ የሚገመተው ሞት ወደ 10ሚሊየን የህክምና ወጪ ደግሞ 100 ትሪልየን ዶላር ያድጋል ተብሎ ይገመታል፡፡
መፍትሄው ምንድን ነው?
- በግለሰብ ደረጃ ሀላፊነት የተሞላበት በዕውቀት ላይ የተመሰረተ የፀረ-ባክቴሪያ አጠቃቀም ያስፈልጋል፡፡ከሁሉ በፊት ግን እራሳችንን ከተለያዩ የባክቴሪያ ኢንፌክሽኖች ለመጠበቅ የግል የአካባቢን እና የምግብን ንፅህና መጠበቅ እንዲሁም ጊዜውን የጠበቁ ክትባቶችን መውሰድ ያስፈልጋል፡፡ ይህም ፀረ-ባክቴሪያን የምንጠቀምበትን አጋጣሚ በመቀነስ መላመድን ይከላከላል፡፡
- የጤና ባለሞያዎች የፀረ-ባክቴሪያን ባላደራነት መለማመድ ይገባቸዋል፡፡ ይህም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ብቻ ፀረ-ባክቴሪያን ማዘዝ እንዲሁም የመድሀኒት ትዕዛዝ ሲፅፉ መሉ መረጃ (መጠን፣ የጊዜ ርዝመት እና ልዩነት) ባካተተ መልኩ መፃፍ ይኖርባቸዋል፡፡
- በመንግስት ደረጃ ለኢንፌክሽን መከላከል እና ለክትባት መርሃግብሮች ትኩረት መሰጠት አለበት፡፡በተጨማሪም ፀረ-ባክቴሪያውች እንደተፈለጉ የሚገዙ ሸቀጦች ሳይሆኑ በባለሞያ ትዕዛዝ ብቻ ጥቅም ላይ አንዲውሉ ቁጥጥር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
- አግባብ ያለው ፀረ-ባክቴሪያ አጠቃቀምን እና ፀረ-ባክቴሪያን መላመድ በሚመለከት ህብረተሰቡን ግንዛቤ ከማስጨበጥ አንፃር የመገናኛ ብዙሃን ከፍተኛ ሚና ሊጫወቱ ይገባል፡፡
ዋቢ
- Ibrahim RA, Teshal AM, Dinku SF, Abera NA, Negeri AA, Desta FG, et al. 2018. Antimicrobial resistance surveillance in Ethiopia: Implementation experiences and lessons learned. African journal of laboratory medicine. 7(2):1-4.
- Muhie OA. 2019. Antibiotic use and resistance pattern in Ethiopia: systematic review and meta-analysis. International journal of microbiology;2019.
- Sweileh WM. 2021. Global research publications on irrational use of antimicrobials: call for more research to contain antimicrobial resistance. Globalization and Health. 17(1):1-12.
- Worku F, Tewahido D. 2018. Retrospective assessment of antibiotics prescribing at public primary healthcare facilities in Addis Ababa, Ethiopia. Interdisciplinary perspectives on infectious diseases.;2018.
ይህ ፅሁፍ በዶ/ር ትንሳኤ አለማየሁ (የህፃናት ህክምና ስፔሻሊስት/የተላላፊ በሽታዎች ሰብ ስፔሻሊስት) እና የጤና ወግ ኤዲተሮች የተገመገመ ነው።