በ ጆኬቤድ ክንፈሚካኤል ሱጋ (ሚዩንግሱንግ ህክምና ኮሌጅ የ፬ አመት ተማሪ) / Jochebed Kinfemichael Suga, 4th year medical student at Myungsung Medical College

Approved by: Dr. Misikir Anberbir (Gynecologist/Obstetrician)

 

አንዲት ሴት እርጉዝ ሆና የቅድመ-ወሊድ ክትትል ስትጀምር ከሚደረግላት የመጀመሪያ ምርመራዎች ዉስጥ አንዱ የኤችአይቪ ምርመራ ነዉ፡፡ ይህንን ምርመራ ማድረግ ያስፈለገበት ዋነኛ ምክንያት ከእናት ወደ ልጅ መተላለፊያ መንገዶችን በመቀነስ ከቫይረሱ ነፃ የሆነ ልጅ መዉለድ እንዲያስችላት ነዉ፡፡

 

የቫይረሱ ከእናት ወደ ፅንሱ የመተላለፍ አቅሙ በብዙ ሁኔታዎች ላይ ይወሰናል፡፡ አጠቃላይ የኤችአይቪ ቫይረስ ስርጭት 15-45% ነው:: ከዚሀ ዉስጥ አንዲት የኤችአይቪ ቫይረስ በደሟ ውስጥ ያለ እናት ያለ ምንም ክትትል እና መድሃኒት የቫይረሱ መተላለፍ አቅም በእርግዝና ወቅት 10-15% ገደማ፣ በምጥ እና ወሊድ ወቅት ከ35-40%፣ ለረጅም ጊዜ ጡት በማጥባት ደግሞ ከ35-40% ገደማ እንደሆነ ያሳያሉ፡፡ ስለዚህ  አስቀድሞ የእናቶችን የቫይረሱ በደማቸዉ ዉስጥ መኖር እና አለመኖር ማወቅ አስፈላጊ ነዉ፡፡

ከእናት ወደ ልጅ የመተላለፍ አቅም ብዙ አዎንታዊ እና አሉታዊ ተፅዕኖዎች ሊጨምሩት አሊያም ሊቀንሱት ይችላሉ፡፡ የመተላለፍ አቅምን ከሚጨምሩ አሉታዊ ተፅዕኖዎች ዉስጥ

  • የቫይረሱ መጠን በእናትዬዉ ደም ዉስጥ ጨምሮ መገኘት 
  • የእናትዬዉ CD4 መጠን ቀንሶ መገኘት 
  • እናትዬዉ ለቫይረሱ የተሰጣትን መድሃኒቶች በአግባቡ አለመዉሰድ
  • የእናትዬው በቂ እና ተመጣጣኝ ምግቦች አለመመገብ
  • የእናትዬዉ በሌሎች ተጨማሪ የተራቀቁ ወይም የከፉ በሽታዎች መያዝ
  • የእናትዬዉ በእርግዝና ወይም በምጥ ጊዜ በሌሎች ቫይረሶች ወይም ጥገኛ በሽታዎች መያዝ
  • የእናትዬዉ በሌሎች አባላዘር በሽታዎች መያዝ 
  • ለረጅም ጊዜ (በአማካይ ከ4 ሰአት በላይ) የቆየ የእንሽርት ዉሃ መፍሰስ
  • በወሊድ ጊዜ በእናትዬዉ ላይ የመውለጃ አካል (genital tract) ጉዳት ከደረሰ
  • ልጁ ከተወለደ በኋላ ለልጁ የሚሰጡ ድህረ ወሊድ እንክብካቤዎች መጉደል
  • ከ1 በላይ (የመንትያ) እርግዝና
  • ልጁ ከተጠበቀበት ጊዜ አስቀድሞ ከመጣ
  • ልጁ ሲወለድ ሊኖረዉ ከሚገባ የክብደት መጠን ቀንሶ ሲገኝ
  • ልጁ ከተወለደ በኋላ 6 ወር ሳይሞላዉ ተጨማሪ ምግቦችን ማስጀመር
  • ልጁን ከ2 አመት በላይ ማጥባት

ኤችአይቪ ቫይረስን ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ እንዴት እንከላከል?

የኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በቫይረሱ ተይዘዉ የሚወለዱ ህፃናት ቁጥርን ለመቀነስ 4 ዋነኛ መከላከያ ስትራቴጂዋችን በማስቀመጥ ይሰራል፡፡

  1. አስቀድሞ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎችን ለመቀነስ የሚደረጉ መከላከያዎች ላይ መስራት፡፡ ይህንንም በመቀነስ በቫይረሱ ቀድሞዉንም የተያዙ እናቶች ቁጥርን በመቀነስ ከቫይረሱ ጋር የሚወለዱ ህፃናትን ለመቀነስ የሚሰራ መከላከያ መንገድ ነዉ፡፡ ይህንንም ከግብ ለማድረስ ሰዎች የ”መ” ህጎችን ልማዶች እንዲያዳብሩ እና ቫይረሱን አስቀድሞ በማወቅ መድሃኒት ስለሚያስፈልጋቸዉ እንዲጀምሩ ይደረጋል፡፡
  2. ቫይረሱ በደሟ ዉስጥ ባለባት ሴት ያልታሰበ እና ያልታቀደ እርግዝና እንዳይኖር የወሊድ መቆጣጠሪያ መንገዶችን በስፋት ለህብረተሰቡ ማስተማር
  3.  ቫይረሱ በደሟ ዉስጥ ያለባት ሴት ካረገዘች አስፈላጊ የሆኑ መድሃኒቶችን እና ቫይረሱ ወደ ልጁ ሊያስተላልፉ ከሚችሉ አሉታዊ ሁኔታዎች ላይ ግንዛቤን በመስጠት የመተላለፍ አቅምን መቀነስ ነው፡፡
  4. ቫይረሱ  በደማቸዉ ያለባቸውን እናቶች፣ የትዳር አጋሮች እና ልጆች አስፈላጊ የሆኑ እንክብካቤዎችን ለመስጠት የሚያስችል ክትትልን ማድረግ ነዉ፡፡

 

በቫይረሱ የተያዙ እናቶች በቅድመ እርግዝና ጊዜ ምን ማድረግ አለባቸዉ?

በቫይረሱ የተያዙ እናቶች በእያንዳንዱ ጤና ጣቢያ እና አብዛኛዉ ሆስፒታሎች የሚሰጡ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት እንዲያገኙ ጠንክሮ ይመከራል፡፡ ይህንንም በማድረግ በዚህ ሰአት ልጅ ያስፈልገኛል? ያልታሰበ እና ያልታቀደ እርግዝናን ዉጤታማ በሆኑ መከላከያዎች እንዴት ማስቀረት እችላለዉ? ልጅ እንዲኖረኝ ሳስብ መጀመሪያ ላደርጋቸዉ የሚያስፈልጉ ነገሮች ምንድን ናቸዉ? ከቫይረሱ ነፃ የሆነ ልጅ እንዲኖረኝ ሊኖረኝ የሚገባዉ የጤና ደረጃ ምንድን ነዉ? እና የመሳሰሉትን ሀሳቦች አገልግሎት ከሚሰጡ አካሎች ጋር በግልፅ መማከር የሚያስችል ይሆናል፡፡

            በቫይረሱ የተያዙ እናቶች በቅድመ ወሊድ ጊዜ ምን ይጠበቃል?

  • ከየትኛዉም እናቶች በላይ በቫይረሱ የተያዙ እናቶች ሊሰጣቸዉ የሚገቡ እንክብካቤዎች የተለየ ጥንቃቄ እና ልዩ ትኩረት ስለሚያስፈለገዉ ማንኛዉም በቫይረሱ የተያዘች እናት አስፈላጊዉን የቅድመ-ወሊድ ክትትል ያለማቋረጥ እንድትከታተል ይመከራል፡፡ 

 

  • ማንኛዉም በቫይረሱ የተያዙ እናቶች ለቫይረሱ የሚሰጡ መድሃኒቶች ከመጀመራቸዉ በፊት ድጋሚ ምርመራ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ይህም አላስፈላጊ መድሃኒቶችን ሳያረጋግጡ ከመስጠት ለመቆጠብ የሚደረግ ጥንቃቄ ነዉ፡፡

 

  • በቫይረሱ የተያዙ እናቶች ለቫይረሱ የተሰጣቸዉን መድሃኒቶች ያለማቋረጥ በአግባቡ መዉሰድ ይኖርባቸዋል፡፡ 

 

  • ማንኛዉም ደረጃቸው ዝቅ ያሉ (low risk) የኤድስ ምልክቶች የሚያሳዩ እናቶች የኤችአይቪ ኤድስ እና የቅድመ ወሊድ ክትትል በሚያደርጉበት የጤና ማእከል መቀጠል ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ደረጃቸው ከፍ ያሉ (high risk) የኤድስ ምልክቶችን የሚያሳዩ እናቶች የኤችአይቪ ኤድስ ክትትላቸውን ወደ ኤችአይቪ ኤድስ ክትትል አገልግሎት ክፍል በማዘዋወር አስፈላጊዉን ክትትል እና በቅርብ ምልከታ መታየት ያስፈልጋቸዋል፡፡

 

  • በደሟ ዉስጥ ያለዉን የቫይረስ መጠን በማወቅ እየተሰጧት ያሉት መድሃኒቶች ረድተዋታል ወይስ አልረዷትም የሚለዉን በቅርብ መከታተል ያስፈልጋል፡፡

 

  • በቅድመ ወሊድ ጊዜም ከእናት ወደ ልጁ የሚተላለፍበትን አሉታዊ ተፅዕኖዎች ከእናትዬዉ ጋር በመወያየት ለማስቀረት የሚሰሩ ስራዎችም መሰራት አለባቸዉ፡፡ የልጁ እድገትንም በአልትራሳዉንድ በመከታተል ፅንሱ የእድገት ዉስንነት አለዉ ወይስ የለዉም የሚሉትን ነገሮች ማየት ያስፈልጋል፡፡

 

በምጥ ወቅት የሚደረጉ ጥንቃቄዎች

  • ምጥ በሚጀምርበት ግዜ በቶሎ ወደ ጤና ተቋም መሄድ
  • ተደጋጋሚ የማህፀን ምርመራ አለማድረግ
  • የፅንስን ውሀ ከማፍሰስ መቆጠብ

 

ኤችአይቪ ቫይረስ በደማቸው ውስጥ ያለ እናቶች ላይ በድህረወሊድ ጊዜ ምን ይጠበቃል?

ማንኛዉም በቫይረሱ የተያዙ እናቶች ለቫይረሱ የጀመሩትን መድሃኒቶች ሳያቋርጡ ከወሊድ በኋላም መቀጠል ይኖርባቸዋል፡፡ በድህረወሊድ ጊዜ የተወለዱት ህፃናት ጡት ማጥባት ወይስ የፎርሙላ ወተት (በተለምዶ የጣሳ ወተት) ይጠቀሙ ለሚለዉ የጤና ባለሙያዎች ጋር በመማከር የትኛዉ  ተቀባይነት አለው፣ ተመጣጣኝ፣ ዘላቂ፣ አዋጭ እና አስተማማኝ ነዉ የሚለዉን በማመዛዘን የሚወሰን ይሆናል፡፡

 

 በተደጋጋሚ የሚጠየቁ ጥያቄዎች

  • በቫይረሱ የተያዘች ሴት ከቫይረሱ ነፃ የሆነ ልጅ መዉለድ ትችላለች?

አዎ፣ ትችላለች፡፡ ቫይረሱ ከእናት ወደ ልጅ መተላለፍ የሚችልበት ትልቅ አቅም ቢኖረውም የቫይረሱን መኖር ቅድሚያ በማወቅ በሚደረጉ መከላከያ መንገዶች ልጁ በቫይረሱ የሚያዝበትን አቅም መቀነስ ይቻላል፡፡

  • በቫይረሱ የተያዘች ሴት ጡት ማጥባት ትችላለች?

አብዛኛዉ አገራት በቫይረሱ የተያዙ እናቶች ጡት እንዲያጠቡ አይመክሩም፡፡ ነገር ግን ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረዉ ከጤና ባለሙያዎች ጋር በመማከር የሚወሰን ነዉ፡፡ የአለም ጤና ድርጅት እ.ኤ.አ በ2010 ወቅት ላይ እንደጠቀሰዉ በቫይረሱ የተያዙ እናቶች እስከ 6 ወር ድረስ በእናት ጡት ብቻ እንዲቆዩ ይመክራል፡፡ ለረጅም ጊዜ (ከ 2 አመት በላይ) ጡት ማጥባት አይመከርም፡፡ 

  • ቫይረሱ ፅንሱ ላይ የሚያመጣዉ ተፅዕኖ አለ?

ፅንሱ ያለጊዜዉ መወለድ፣ የፅንስ ዉርጃ ወይም በማህፀን ዉስጥ መሞት፣ ፅንሱ ከሚጠበቅበት ክብደት አንሶ መወለድ እና የፅንስ እድገት ቅንጭርነት ብዙ ጊዜ ከሚጠቀሱ ተፅዕኖዎች ዉስጥ ዋነኞቹ ናቸዉ፡፡

  • ፅንሱ በቫይረሱ ላይ የሚያመጣዉ ተፅዕኖ አለ?

እርግዝና በቫይረሱ ላይ የሚያመጣዉ ምንም አይነት ተፅዕኖ የለም፡፡ የቫይረሱን ስርጭት አያብሰዉም ወይንም አይቀንሰዉም፡፡

 

  • የትኛዉ የመዋለጃ ሂደት ይመረጣል፣ በምጥ ወይስ ኦፕራሲዮን?

ብዙ ፅሁፎች እንደሚያሳዩት የቫይረሱ መጠን ጥቂት ከሆነ እና እናትዬዉ መድሃኒቶቿን በአግባቡ እየተከታተለች ከነበረ በምጥ መዉለድ ጥሩ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ አንዳንድ ፅሁፎች በወሊድ ወቅት ሊኖር የሚችልን ንክኪ ለመቀነስ ኦፕራሲዮን የተሻለ እንደሆነ ይጠቅሳሉ፡፡ በምጥ ወይስ ኦፕራሲዮን ለሚለዉ ጥያቄ የቫይረሱ መጠን ታይቶ የሚወሰን ይሆናል።

 

የጤና ወግ 

ጠቃሚ እና የተረጋገጠ መረጃ ለጤናዎ ።

የጤና ወግን በነዚህ ሊንኮች መከታትል ይችላሉ ።

https://linktr.ee/Yetena_Weg