የጤና ወግ የእለቱ መልእክት ማርች 20 2020
በዶ/ር አዜብ አሳምነው አለሙ ፣ የአዕምሮ ህክምና ስፔሻሊስት
የኮሮና ቫይረስ በሽታ የኛን ሀገር ጨምሮ በተለያዩ መልክአ-ምድር በሚገኙ የተለያዩ ሀገራት ገብቷል።
- በሽታው ከየትኛውም #ዘር፣ #ብሔር ወይም #ዜግነት ጋር አይያያዝም። በበሽታው ለተያዙት ሁሉ ከየትም ቦታ ቢሆኑ ክብር አይለየን። ራሳችንን በነሱ ቦታ አድርገን፣ ‘የደረሰብን እኛ ብንሆንስ?’ ብለን እናስብ። በበሽታው የተያዙ ሰዎች ምንም ጥፋት የለባቸውም። እንደማንኛውም ሰው ክብር፣ ርህራሄ እና እርዳታ ያስፈልጋቸዋል።
- በበሽታው የተያዙ ሰዎችን ‘የበሽታው ኬዞች’ ፣’በበሽታው የተጠቁ’ ፣ ‘የበሽታው ቤተሰቦች’ ወይም ‘በሽተኞቹ’ በማለት አንጥራቸው። ‘በሽታው የተገኘባቸው’፣ ‘ከበሽታው እያገገሙ የሚገኙ’ ወይም ‘ለበሽታው ህክምና እያገኙ ያሉ’ በማለት እንግለጻቸው። ከበሽታው ካገገሙ በኋላ ህይወታቸው ከስራ፣ ከቤተሰብ እና ከወዳጅ ዘመድ ጋር ይቀጥላል። ስለዚህም በሽታውን ከግለሰቡ/ቧ ማንነት በመለየት ከአድሎ እና መገለል መከላከል ይኖርብናል።
- ጭንቀት እና መረበሽ የሚፈጥርብንን ዜና ከማዳመጥ፣ ከማየት፣ ከማንበብ እንቆጠብ። የምከታተላቸውን ዜናዎች ከታማኝ ምንጮች ብቻ እንጠቀም። እነዚህንም በዋናነት እራሳችንን እና ቤተሰባችንን ከበሽታው ለመከላከል እቅድ ለማውጣት እንጠቀምበት።
- ዜናዎችን ለመከታተል የሚመቸንን ሰአታት በመምረጥ በቀን አንድ ጊዜ ወይም ሁለት ጊዜ ብቻ እንከታተል። ስለወረርሽኙ የሚተላለፉ ድንገተኛ እና ተከታታይ የሆኑ ዜናዎችን መከታተል በማንኛውም ሰው ላይ ስጋት ይፈጥራል። ስለዚህም ለእውነታው ብቻ እንጂ ለሀሜቱ እና ለተዛነፈ ዜና ቦታ አንስጠው።
- መረጃዎችን በተወሰነ ሰአት ልዩነት ከአለም ጤና ድርጅት ድረገጽ ፣ ከፌደራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ወይም ከኢትዮጺያ ማህበረሰብ ጤና ኢኒስቲቲውት የሚወጡትን መረጃዎች በማየት እራሳችንን ከተዛነፈ ወይም ከሀሰት መረጃ እንጠብቅ። እውነታውን ማወቅ፣ የተጋነነ ፍርሃትን ለመቀነስ ያግዛል።
- ራሳችንን እንጠብቅ፣ ሌላውንም እናግዝ። የተቸገሩ ሰዎችን በመርዳት ሌላውን ሰው ከመጥቀም ባለፈ ለሁላችንም ይጠቅማል። ለምሳሌ፣ በስልክ ጎረቤቶችን እና ወዳጅ ዘመድ ወይም እርዳታ ሊያስፈልጋቸው የሚችሉ የማህበረሰቡ አባላትን መጠየቅ ይቻላል። የማህበረሰብ ተቀናጅቶ መስራት እንደኮሮና ቫይረስ ያሉ ወረርሽኞችን ለመቆጣጠር ይጠቅማል።
- ከኮሮና በሽታ ጋር የተያያዙ ተስፋ ሰጪ የሆኑ ዜናዎችን፣ ታሪኮችን እና ምስሎችን እናጋራ። ለምሳሌ፣ ከበሽታው ያገገሙ፣ በበሽታው ለተያዙ ሰዎች እንክብካቤ የሚሰጡ ሰዎችን ታሪክ ፈቃደኛ ከሆኑ ማጋራት።
- በኮሮና ቫይረስ በሽታ የተያዙ ሰዎችን ለሚንከባከቡ የጤና ባለሙያዎች እና አጋዥ ሰዎች ተገቢውን ክብር እንስጥ። የሰዎችን ህይወት ለማትረፍ እና የምንወዳቸውን ሰዎች ከበሽታው ለመከላከል በሚደረገው ትግል ውስጥ ያላቸውን ሚና በማስተዋል እናመስግናቸው።
*ይህ ጥቆማ የተዘጋጀው በአለም ጤና ድርጅት የአእምሮ ጤና ክፍል ሲሆን አላማው በዚህ ኮሮና ቫይረስ በሽታ ወረርሺኝ ወቅት የማህበረሰቡ የአዕምሮ ጤና እና ማህበረሰባዊ ግንኙነት ለማገዝ ነው። ለሃገራችን እንዲስማማ ተርጉሜዋለሁ።