በአላዛር አምላኩ (አ.አ.ዩ ህ/ጤ/ሳ/ኮ የህክምና ተማሪ-C2)
መግቢያ
ብዙዎቻችን ተወልደን ባደግንባት አገራችን ኢትዮጵያ ውፍረት በጥሩ መልኩ ይታያል። ለብዙ ዘመናት አገራችን በድህነት አዙሪት ውስጥ ስትሽከረከር እንደመኖሯ የዜጎቿ የኑሮ ሁኔታ በእጅጉ የተጎዳ ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ ውፍረት እንደመልካም ነገር ይቆጠራል። አብዛኛው ሰው ስለአመጋገቡ ጤናማነትና ስለሰውነት ክብደቱ መጨመር አይጨነቅም። በነዚህና ሌሎች ምክንያቶች ከልክ ያለፈ ውፍረት በኢትዮጵያ ትልቅ የጤና ችግር እየሆነ ይገኛል።
ከልክ ያለፈ ውፍረት ምንድነው?
ከልክ ያለፈ ውፍረት (obesity) ክብደታችን ለቁመታችን ካሬ ተካፍሎ በሚሰጠን መመዘኛ መሰረት ከ30ኪግ በ ካሬሜትር በላይ ሲሆን ነው። ከልክ ያለፈ ውፍረት ሦስት ደረጃዎች ያሉት ሲሆን እነሱም ደረጃ 1 ከ30-34.9 ኪግ በካሬሜትር፣ ደረጃ 2 ከ35-39.9 ኪግ በካሬሜትር እና ደረጃ 3 ከ40 ኪግ በካሬሜትር በላይ ናቸው። ደረጃው በጨመረ ቁጥር አደገኛነቱም በዛው ልክ ይጨምራል።
ከልክ ያለፈ ውፍረት በአለም፣ በአፍሪካ እና በኢትዮጵያ
እንደ የአለም ጤና ድርጅት ጥናት መሠረት በአለምአቀፍ ደረጃ ከልክ ያለፈ ውፍረት ከፈረንጆቹ 1975 ዓ.ም ወዲህ በ3 እጥፍ ጨምሯል። እ.ኤ.አ በ2016 ዓ.ም ይፋ በሆነው ጥናት መሠረት እድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ ከሆኑት ውስጥ 13 በመቶ የሚሆነው የሰውነት ውፍረቱ ከልክ ያለፈ ነበር። በጾታ ክፍፍል ስናየው ደግሞ 11 በመቶ ወንዶች እና 15 በመቶ ሴቶች እድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ ከሆኑት ውስጥ ከልክ ያለፈ ውፍረት ይታይባቸው ነበር።
በአፍሪካ አህጉር ከልክ ያለፈ ውፍረት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአሳሳቢ ሁኔታ እየጨመረ ይገኛል። በቅርብ ጊዜ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩን 18.4 በመቶ ሴቶች እና 7.8 በመቶ ወንዶች ከልክ ያለፈ ውፍረት ነበረባቸዉ። በኢትዮጵያ በችግሩ ዙሪያ የተደረጉ ጥናቶች ጥቂት ከመሆናቸውም በላይ ብዙዎቹ አብዛኛውን የማህበረሰብ ክፍል አያካትቱም። የተጠቀሱት ክፍተቶች እንዳሉ ሆነው በ2015 እ.ኤ.አ በተደረገ ጥናት እንደምናየው በሀገሪቱ ያለው ከልክ ያለፈ ውፍረት ምጣኔ ወደ 5 በመቶ ተገምቷል። የጥናቶቹ አናሳነትና ሌሎች እክሎች ቁጥሩን ከፍ ወይም ዝቅ አድርጎታል ተብሎም ይታሰባል።
ከልክ ያለፈ ውፍረት እንዴት ይከሰታል?
የሰው ልጅ ለመኖር ጉልበት ያስፈልገዋል ይህን ጉልበት ደግሞ የምናገኘው ከምግብ ነው። ከምግብ የምናገኘው ጉልበት በተለያየ መልኩ አገልግሎት በመስጠት ይቃጠላል። የምናገኘው ጉልበት ከሚቃጠለው በላይ መሆን ሲጀምር ጤናማ የሆነው ሚዛን መዛነፍ ይጀምራል ስለሆነም ሰውነታችን ትርፍ ጉልበት ይይዛል። ይህ ትርፍ ጉልበት ሲከማች በጊዜ ሂደት ውፍረትን ብሎም ከልክ ያለፈ ውፍረትን ያስከትላል።
የምናገኘው ጉልበት ከሚቃጠለው በላይ እንዲሆንና ውፍረት እንዲከሰት የሚሆንበት ምክንያቶች ሁለት ሲሆኑ እነሱም ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ እና በቂ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ ናቸው።
ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ ስንል ሰውነታችን ከሚያስፈልገው በላይ ብዙ ስንመገብ በተለይም በቅባት እና ስኳር የበለጸጉ ምግቦችን ስናዘወትር እንደማለት ሲሆን ይህም ጤናማ የጉልበት ሚዛንን በማዛባት ለአላስፈላጊ የጉልበት ክምችት ይዳርጋል። ሌላኛው ደግሞ በቂ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ ነው። የከተሞች መስፋፋት የሰዎችን የእንቅስቃሴ መጠን በእጅጉ እየቀነሰው ይገኛል። ባለንበት ዘመን እየጨመረ የመጣው እንቅስቃሴ አልባ ኑሮ የምናቃጥለውን ጉልበት በመቀነስ ከልክ ያለፈ ውፍረትና ተያያዥ ችግሮች ጎልተው እንዲወጡ ምክንያት እየሆነ ይገኛል።
ከልክ ያለፈ ውፍረት የሚያመጣቸው የጤና እክሎች
ከልክ ያለፈ ውፍረት (obesity) ከበርካታ የጤና ችግሮች ጋር ይያያዛል። ተላላፊ በሽታዎች (communicable diseases) በአለም ላይ መቀነስ ሲጀምሩ በተቃራኒው ደግሞ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች (non-communicable diseases) ምጣኔ በማሻቀብ ላይ ይገኛል። ለነዚህ ችግሮች መበራከት ደግሞ እንደዋነኛ ምክንያት ተደርጎ የሚወሰደው ከልክ ያለፈ ውፍረት ነው።
ከነዚህ የጤና እክሎች ውስጥ የስኳር በሽታ፣ የልብና የደም ዝውውር ስርዓት ችግሮች፣ የአተነፋፈስ ስርዓት ችግሮች፣ ከፍተኛ የሆነ የደም ግፊት፣ የአጥንት የጡንቻና የመገጣጠሚያ አካላት ችግሮች፣ ካንሰር፣ የሐሞት ጠጠር፣ የአእምሮ ችግሮች በተለይ ድብርት ከዋነኞቹ ተጠቃሾች ናቸው። በልጅነት የሚከሰት ከልክ ያለፈ ውፍረት ከላይ ለተጠቀሱት ችግሮች በእጅጉ ተጋላጭነትን ከመጨመሩም በተጨማሪ ከፍተኛ የሆነ የስነልቦና ችግር ያመጣል።
ከልክ ያለፈ ውፍረትን እንዴት እንከላከል?
ከልክ ያለፈ ውፍረትና ተጓዳኝ ችግሮቹ እንዳይከሰቱ ቀድመን መከላከል እንችላለን። ጤናማ የሆነ አመጋገብን ባህላችን እንዲሁም የአካል ብቃት እንቅስቃሴን የዘወትር ልማዳችን በማድረግ ይህን ችግር መቀነስ ይቻላል።
ይህን ችግር ለመቅረፍ በግለሰብ፣ በማህበረሰብ እና በመንግስት ደረጃ የተቀናጀ ስራ ያስፈልጋል። መንግስት በችግሩ ዙሪያ ፖሊሲዎችን ቀርጾ ተፈጻሚ እንዲሆኑ በማድረግ ማህበረሰቡን ማገዝ አለበት። በማህበረሰቡ ውስጥ ያለው እያንዳንዱ ግለሰብ ደግሞ ሀላፊነቱን በአግባቡ መወጣት ይኖርበታል።
ዋቢ
https://www.who.int/news-room/fact-sheets/detail/obesity-and-overweight
Prevalence of overweight/obesity among the adult population in Ethiopia: a systematic review and meta-analysis – PubMed (nih.gov)
https://www.uptodate.com/contents/obesity-in-adults-overview-of-management
https://www.devex.com/news/key-to-addressing-obesity-in-africa-lies-in-education-food-systems-99644
ይህ ፅሁፍ በዶ/ር ቃልኪዳን አላቸው (የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት/ኢንዶክሪኖሎጂስት) እና የጤና ወግ ኤዲተሮች የተገመገመ ነው።