በዶ/ር ቃልኪዳን ጫላ (የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ሀኪም)
አልኮልን አብዝቶ መውሰድ ለተለያዩ የጤና ጉዳቶች እንደሚዳርግ ይታወቃል። ከነዚህም አንዱና ዋነኛው ከአልኮል ጋር የተያያዘ የጉበት ህመም የምንለው ነው። አልኮል ከሰውነታችን ውስጥ የሚወገደው በጉበት አማካኝነት ነው። ስለዚህም ለረጅም አመታት አልኮልን መጠጣት ወይንም አልፎ አልፎ ከመጠን ባለፈ መልኩ መውሰድ ለጉበት ህመም ይዳርጋል። የአልኮል ጉዳት ከመጠን ጋር የተያያዘ እንደሆነ ጥናቶች ያሳያሉ። በዚህም መሠረት አንድ ሰው አብዝቶ ተጠቀመ የምንለው በቀን ለወንድ ከ 3 እና ከዚያ በላይ መጠጥ (drink)፣ ለሴት ደግሞ ከ 2 እና ከዚያ በላይ መጠጥ (drink) የሚወስዱ ከሆነ ነው። የመጠጥ መጠን እንደ መጠጡ አይነትና በውስጡ እንዳለው የአልኮል መጠን ይለያያል ። ለምሳሌ 1 መጠጥ (drink) ማለት አንድ ቢራ (bottle of beer)፣ 1 ብርጭቆ ወይን (glass of wine)፣ እንዲሁም 1 መለኪያ ከባድ አልኮል (80% spirit) ማለት ሲሆን ሁሉም የመጠጥ አይነቶች በተመሳሳይ መልኩ 14 ግራም የአልኮል መጠን አላቸው።
አንዳንድ ሰዎች በየቀኑ አልኮል ባይወስዱም ከቆይታ በኋላ ከጒደኛ ጋር ለመጨዋወት በሚል ወይም በተለያዩ ማህበራዊ መስተጋብሮች ምክንያት አልኮልን አብዝተው ሊወስዱ ይችላሉ ። ይህ ማለት ወንዶች ከ 5 መጠጥ በላይ ፣ ሴቶች ደግሞ ከ 4 መጠጥ በላይ የአልኮል መጠንን በ 2 ሰአታት ጊዜ ውስጥ የሚወስዱ ከሆነ binge drinkers እንላቸዋለን ። ለዚህ Binge Drinking የአማርኛ አቻ ትርጉም ባናገኝለትም በጥቂት ሰአታት ውስጥ የሚወሰድን ከፍተኛ የአልኮል መጠጥ መጠንን ይወክላል። ይህ ከልክ ያለፈ ድርጊት አልኮልን ለረጅም ጊዜ ከወሰዱት ሰዎች በእኩል ደረጃ ለጉበት ህመም ተጋላጭ ያደርጋቸዋል።
አልኮል የጉበት ህመምን የሚያስከትልበት ምክንያት በዋናነት በጉበት ሴሎች ውስጥ ስለሚወገድ ነው። አልኮልን በማስወገድ ሂደት ውስጥ acetaldehyde የምንለው ኬሚካል ይፈጠራል ። ይህ ኬሚካል በጉበት ሴሎች ላይ በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ መንገድ ጉዳት ያደርሳል፤ በዋነኝነት በእነዚህ ሴሎች ውስጥ ከፍተኛ የስብ መጠን እንዲጠራቀም በማድረግ የጉበት ላይ የስብ ክምችትን (fatty liver) በመፍጠር ነው። በተጨማሪም በሰውነታችን ውስጥ ያለው የስብ መጠን በአልኮል ምክንያት ይጨምራል ። ይህም በጉበት ላይ ለሚጠራቀመው ስብ ተጨማሪ ምክንያት ይሆናል።
ከአልኮል ጋር የተያያዘ የጉበት ህመም እንዲፈጠር የሚያደርጉ አጋላጭ ሁኔታዎች
1. ከመጠን በላይ የአልኮል መጠጥን መውሰድ
2. ያለምግብ አልኮል መውሰድ
3. ሲጋራ ማጤስ
4. የታወቀ የጉበት ህመም
5. ከመጠን ያለፈ ውፍረት (obesity)
6. እንዲሁም ሴቶች በትንሽ የአልኮል መጠን የጉበት ላይ ስብ የማከማቸት አቅማቸው ከፍተኛ በመሆኑ ከወንዶች ይልቅ ተጋላጭ ናቸው።
የጉበት ህመም ምልክቶች
በአብዛኛው ጊዜ የጉበት ላይ ስብ ክምችት እንዲሁም የመጀመሪያው መጠነኛ የጉበት ጉዳት ምልክት አያሳይም። ስለዚህ የህመም ስሜት ሲመጣ ከፍተኛ የጉበት ጉዳት ደርሷል ማለት ይቻላል።
ምልክቶቹም: ከፍተኛ የድካም ስሜት ፣መክሳት እና ክብደት መቀነስ፣ የሆድ ህመም ፣የሆድ እብጠት፣ የእግር እብጠት፣የአይን ቢጫ መሆን ፣የእጅ መዳፍ መቅላት እንዲሁም የመዳፍ ጡንቻ መቀነስ፣ የፊት ገፅታ እና የቆዳ ቀለም መቀየር ፣ የጡት መጠን መጨመር (ለወንዶች)፣ የወር አበባ መዛባት (ለሴት) ፣ የወሲብ ፍላጎት መቀነስ እና የመራቢያ አካላት መጠን መቀነስ (ለወንድ) ፣የእንቅልፍ መዛባት፣ መርሳት ፣የእጅና የእግር መደንዘዝ ናቸው። እነዚህ ምልክቶች ሲታዩ በአፋጣኝ ወደ ሆስፒታል በመሄድ የጉበት ምርመራ ማድረግ ያስፈልጋል ።
አልኮል ካቆሙ በኃላ ሊከሰቱ የሚችሉ ምልክቶችን ማወቅ በቶሎ የህክምና እርዳታን ለማግኘት ይረዳሉ። ሰውነታችን ለረጅም ጊዜ የአልኮል ጥገኛ ሆኖ ከቆየ በኃላ በማቆም ሂደት ውስጥ አልኮል የማቆም ምልክቶች (withdrawal symptoms) የሆኑ የሚከተሉት ስሜቶች ሊስተዋሉ ይችላሉ። እነዚህም የልብ ምት መጨመር፣ የእጅ መንቀጥቀጥ ፣ የመጨናነቅ ስሜት ፣ ራስን መሳትና የመሳሰሉት ናቸው።
በአልኮል ምክንያት የመጣን የጉበት ህመም እንዴት ማከም ይቻላል?
1. ዋነኛው ህክምና አልኮል መጠጥ ማቆም ነው። ይህም በራስ ተነሳሽነትም ሆነ በስነአዕምሮ ህክምና ባለሞያዎች እርዳታ አማካኝነት መደረግ የሚኖርበት እጅግ በጣም አስፈላጊ ህክምና ነው።
– በዋናነት አልኮል ማቆም ከባድ ያልሆኑ የጉበት ጉዳቶችን በመቀነስ ጉበት እንዲያገግም እና ጤነኛ እንዲሆን ይረዳል ።
– ከዚህ ባለፈ በአሁኑ የሳይንስ እውቀት የሚታወቅ የጉበቱን ጉዳት የሚያስተካክል ህክምና ወይም መድኃኒት የለውም።
2. ለጤና ጠቃሚምግቦችንመመገብ።ሀይልሰጭምግቦች፣ቫይታሚን B1 supplement መውሰድ።
3. በአልኮል ምክንያት የመጣ የጉበት ህመም ከፍተኛ ደረጃ የደረሰ ከሆነ ጉዳቱ እንዳይባባስ ለማድረግ የተለያዩ ህክምናዎች ሊደረጉ ይችላሉ ።
– የሆድ እብጠት ለመቀነስ የሚሰጡና እብጠቱን ያመጣውን የፈሳሽ ክምችት በሽንት በኩል እንዲወገድ የሚያደርጉ መድኀኒቶች (diuretics) በኪኒን መልክም ሆነ በደም ስር ሊሰጥ ይችላል
– በሆድ አከባቢ በሚከማቸው ፈሳሽ ውስጥ ኢንፌክሽን ተፈጥሮ ከሆነ ፈሳሹን ማስመርመርና መድሃኒቶች መውሰድ ይገባል።
– የምግብ መተላለፊያ ቱቦ ላይ በህመሙ ምክንያት የሚያብጡ ደምስሮች መድማት እንዳይከሰት የኢንዶስኮፒ ምርመራ እና ህክምና ማድረግ
– የጉበት ካንሰር ምርመራ ማድረግ
–ከልክ በላይ ጉዳት የደረሰበት ጉበት የጉበት ንቅለ ተከላ ሊያስፈልገው ይችላል።
በመጨረሻም አልኮል ከጉበት ባሻገርም የሰውነታችን እያንዳንዱ አካል ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ከፍተኛ ጉዳት በመገንዘብ ጥንቃቄ ማድረግ አስፈላጊ ይሆናል። ሰላም!