ክቡር ስጦታ

በዶ/ር ነህሚያ አንዳርጋቸው (ጠቅላላ ሀኪም)

 

‘እገሌ እኮ ደም ተሰጠው’ ሲባል መቼስ ሰምተው ያውቃሉ። ይህ ግን ምን ማለት እንደሆነ በግርድፉ ቢረዱም ጠለቅ ብለው ጠይቀው ላያውቁ ይችላሉ። ነገሩ እንደዛ ከሆነ አብረውን የተወሰኑ ደቂቃዎች ይቆዩ። አንድ ቁም ነገር አካፍለንዎ ወደየመንገዳችን እንቀጥላለን።

‘እገሌ ደም ተሰጠው’ መባል የጀመረው እ.አ.አ በ1818 በሃገረ እንግሊዝ ነበር። ከወሊድ በኋላ ብዙ ደም ለፈሰሳት እናት ከባለቤቷ ክንድ ላይ ደም በመቅዳት በእርሷ ደም ስር ይሰደዳል። ይህ ሙከራም በተሳካ ሁኔታ ተጠናቆ ከታሪክ መዝገብ ላይ ለመስፈር በቅቷል። በዚያን ጊዜ የተጀመረው የደም መስጠት ሂደት ዛሬ እጅግ በጣም ዘምኖ እና ረቆ በአመት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት ይታደጋል።

ቆይ ግን፤ ብዙ ሳንርቅ፤ ደም ተሰጠኝ ማለት  ምን ማለት ነው?

ለዚህ ጥያቄ አንድ ቀላል፣ አንድ ደግሞ ጠለቅ ያለ መልስ መስጠት ይቻላል።

ቀላሉ እንዲሁም በጣም የተለመደው መልስ ይህ ነው። በአሁኑ ሰዓት ደም ተሰጠህ/ተሰጠሽ ማለት ከብሄራዊ ደም ባንክ አገልግሎት ፍሪጅ ውስጥ የመጣ፤ ለጤና ተስማሚነቱ ተመርምሮ የተረጋገጠ ደም ህክምና እያደረግ/ሽ ባለው የጤና ተቋም ላብራቶሪ ውስጥ ከአንተ/አንቺ ደም ጋር ተቀላቅሎ ቢዋሃድ ሊሰራ እንደሚችል ተረጋግጦ በደም ስር በኩል ሲሰጥ ነው። ከዚህ ቀላል መልስ ጠለቅ ስንል ከተፈጥሮ ክስተቶች ውስጥ አስደማሚ ከሆኑት ሚስጥሮች አንዱ የሆነውን ደምን እናገኛለን። ደም፣ ለሰውነት ስርዓቶቻችን ወሳኝ የሆኑትን ኦክሲጅን እና መሰረታዊ ንጥረ ነገሮችን የማዘዋወር ሚና አለው። በተጨማሪም ሰውነታችን በሚደማበትም ጊዜ መድማት እንዲቆም የሚሆነውም በዚሁ ደማችን ውስጥ በሚገኙ ሴሎች ምክንያት ነው። ተዋህዶ ስናየው ሃምራዊ ቀለም ያለው ደማችን ፕላስማ ከምንለው ፈሳሽ፣ ፕሌትሌት የሚባሉ ሴሎች (እንዳንደማ የሚያደርጉ)፣ ከነጭ የደም ሴሎች (በሽታን የሚከላከሉ) እንዲሁም ከቀይ የደም ሴሎች (ኦክሲጅን የሚሸከሙ) በተጨማሪም ከተለያዩ ንጥረ ነገሮች የተሰራ ነው። እንደምናየውም በብዛት በመገኘት ቀይ ቀለሙን የሚሰጡት ቀይ የደም ሴሎች ናቸው።

ሰዎች መቼ ነው ደም የሚሰጣቸው?

ሰዎች ደም የሚሰጣቸው በሰውነታቸው ውስጥ ያለው የደም መጠን ሲያንስ ነው። ማነሱ በላብራቶሪ ምርመራ በቀላሉ ይታወቃል። ይህ ምርመራ በደም ውስጥ ያለውን የቀይ የደም ሴል እንዲሁም የፕሌትሌት ቁጥር በግልጽ ያሳየናል። በዚህም ላይ ተመርኩዞ ባለሙያው ደም እንዲሰጥ ሊያዝ ይችላል። ለዚህ ሁኔታ ሊያጋልጡ ከሚችሉት ሁኔታዎች ውስጥ የሚከተሉት ይጠቀሳሉ።

  • ከባድ የደም መፍሰስ ( አደጋን ተከትሎ፣ ከወሊድ በኋላ ወዘተ…)፤ ከባድ የደም መፍሰስ በአካላችን ውስጥ የሚዘዋወረውን የጠቅላላ ደም እንዲሁም የቀይ የደም ሴል መጠን በአንዴ እንዲያሽቆለቁል ስለሚያደርግ የሚፈሰውን ደም ወዲያው እንዲያቆም ማድረግ እና በምትኩ ደም መስጠት በየአመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት ይታደጋል።
  • የካንሰር ህመም፤ የተለያዩ አይነት የካንሰር ህመሞች ሰውነታችን የሚያመርታቸውን የቀይ ደም ሴል ቁጥር እንዲቀንስ በማድረግ ለደም ማነስ ያጋልጡናል። በተጨማሪም ፕሌትሌት የተባሉትን የደም ሴሎች ቁጥር በመቀነስ ያለምንም በቂ ምክንያት እንድንደማ እንሆናለን። በዚህን ጊዜም ደም እንዲሁም ከደም ውጤቶች ውስጥ አንዱ የሆነውን ፕሌትሌት በመውሰድ ህይወታችን ሊድን ይችላል።
  • የኩላሊት ህመም፤ ዳያሊሲስ የሚያስፈልገው የረጅም ጊዜ የኩላሊት ህመም ሰውነታችን የሚያመርተውን የቀይ የደም ሴል ቁጥር በእጅጉ ይቀንሰዋል። ይህ ሊሆን የቻለውም ኩላሊት በቀይ የደም ሴል ምርት ውስጥ ባላት ወሳኝ ቦታ ነው። ስለዚህም ከዚህ ህመም ጋር በተያያዘ አልፎ አልፎ ደም መሰጠት ሊኖርበት ይችላል።

ደም እንዲሰጠን ሲወሰን ባለሙያዎች መጀመሪያ የደም አይነታችንን ይለያሉ። በመቀጠልም ከደም አይነታችን ጋር የሆነ ደም ይፈለጋል። በመቀጠልም ይህ የደም አይነት ከእኛ ደም ጋር የመዋሀድ አቅሙ በቀላል የላብራቶሪ ምርመራ ይጣራል። በመጨረሻም ደሙ በደምስራችን ይሰጠናል። ደሙ በሚሰጠን ወቅትም ምንም አይነት እንግዳ የሆነ ለውጥ የሚኖር ከሆነ በቶሎ ደሙን አቁሞ ተገቢውን ህክምና ተደራሽ ለማድረግ የቅርብ ክትትል ይደረግልናል። በዚህ ክትትል ወቅት ባለሙያዎች ከሚከታተሏቸው ምልክቶች ውስጥ የሙቀት መጠናችን እና በቆዳችን ላይ የሚታይ ሽፍታ ተጠቃሽ ናቸው።

በዚህ ጽሁፍ ውስጥ ተጠቃሽ መሆን ያለበት ነጥብ የብሄራዊ የደም ባንክ አገልግሎት ሚና ነው። የደም ባንክ አገልግሎት በበጎ ፈቃድ ደም የሚለግሱ ግለሰቦችን ደም በመሰብሰብ እና ለታካሚዎች ለመሰጠት ብቁ መሆኑን በማረጋገጥ ህይወት የሚታደግ አገልግሎትን ያለምንም ክፍያ ያቀርባል። ሩቅ ባልሆነ ጊዜ ይህንን አገልግሎት ለማግኘት አንድ ሰው በሚሰጠው ደም ምትክ ደም የሚሰጥ ቤተሰብ/ጓደኛ ያስፈልገው ነበር። ይህን አሰራር ቀይሮ አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ የበጎ ፈቃድ ደም ለጋሾችን ቁጥር መጨመር ወሳኝ ሚና ነበረው።

ታዲያ በበጎ ፈቃድ ደም ለመለገስ ምን አይነት ሁኔታዎችን ማሟላት አለብን?

  • ክብደት ሚዛኑ ቢያንስ 45 ኪሎ ግራም የሆነ፣
  • የደም ግፊት መጠኑ ያልወረደ
  • ነፍሰ ጡር ያልሆኑ
  • በጠቅላላው በደህና ሁኔታ ላይ መገኘት

ተጨማሪ ነጥቦች

  • በደም ተላላፊ የሆኑ ህመሞች ያሉባቸው ግለሰቦች ደም ለመስጠት ብቁ አይደሉም
  • እንደ ስኳር፣ ደም ግፊት ያሉ የማይተላለፉ የህመም አይነቶች ደም ከመለገስ አያግዱንም
  • ደም መለገስ በጤናችን ላይ የሚያስከትለው ምንም አይነት ጉዳት የለም።

እናም በጠቅላላው ደማችንን በመለገስ ውድ የሆነውን የሰውን ልጅ ህይወት እንታደግ።

እኛ ከሃያ ባነሱ ደቂቃዎች የለገስነው ደም ምናልባትም በሞት እና በህይወት መካከል ያለች እናትን፣ ሮጦ ያልጠገበ በካንሰር የታመመ ህጻን ልጅን ብሎም ለሃገሩ ብሎ ደሙን የሚያፈሰውን ወታደር ህይወትን ይታደግ ይሆናል። ይህ ደግሞ ትልቅ ክብር ነው።

ደሜን ለወገኔ!