Written by- PINEAL ABEBE MITIKU(C-2)

Reviewed by Dr. Wuhib Zenebe

 

ክትባት ጠቃሚ እና ወጪ ቆጣቢ ከሆኑ የበሽታ መከላከያ ዘዴዎች አንዱ ነዉ ። ውጤታማ እና ደህንነታቸው በተጠበቁ ክትባት ግኝቶች ምክንያት የሰው ፈንጣጣ በሽታ ከዚህ ዓለም ማጥፋት ተችሏል።

ክትባት በአንድ የተወሰነ በሽታ ላይ የበሽታ መከላከያዎችን የማነሳሳት ሂደት ነው:: የክትባት ንጥረ ነገሮች የተገደሉ ወይም የተዳከሙ የቫይረስ ፣ ባክቴሪያ ወይም ኘሮቶዞአ ቁርጥራጮች ሊሆኑ ይችላሉ።

በክትባት መከላከል የሚቻሉ በሽታዎችን ለመቆጣጠር በ1974 የተስፋፋው የክትባት ፕሮግራም (expanded program of immunization) በአለም የጤና ድርጅት ተቋቁሟል።

 

የክትባት ጥቅሞች

በሽታን መከላከል ፡- ክትባቶች የበሽታ መከላከል ስርዓታችን እንደ ቫይረሶች እና ባክቴሪያ ያሉ በሽታ አምጪ ተዋስያንን እንዲያውቅ እና እንዲዋጋ ይረዳል።

በሽታን ማጥፋት ፡- ክትባቶች በአለም ላይ አንዳንድ በሽታዎችን ለማጥፋት ሚና ተጫውተዋል። ለምሳሌ የፈንጣጣ በሽታ በክትባት መስፋፋት አማካኝነት ማጥፋት ተችሏል። የፖሊዮ በሽታም በሰፊው የክትባት ዘመቻ ለመጥፋት ተቃርቦአል።

የበሽታ ስርጭትን መቀነስ ፡- ክትባቱን የተከተቡ ግለበቦችን ከመከላከል ባለፈ በማህበረሰቡ ውስጥ የበሽታዎችን ስርጭት ለመከላከል ይረዳል። ጉልህ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍል ሲከተብ “የመንጋ መከላከያ (Herd immunity)”ይፈጠራል። ይህም የወረርሽኙን የመስፋፋት እድል ይቀንሳል።

ወጪ ቆጣቢነት ፡- በሽታን ከማከም ጋር ተያይዞ የሚመጡ የጤና አጠባበቅ ወጪዎችን መቀነስ እና በህመም ምክንያት የምርታማነት ኪሳራን በማስወገድ ያግዛል።

 

በህፃናት ክትባት መከላከል የሚቻሉ በሽታች

1. የሳንባ ነቀርሳ ( ቲቢ ) 

ቲቢ በጣም ከባድ የሆነ በሽታ ሲሆን በህፃናት ላይ የማጅራት ገትር በሽታ ሊያመጣ ይችላል።

የቢሲጂ ክትባት የሳንባ ነቀርሳ (ቲቢ) የሚያስከትሉ ባክቴሪያዎች የተዳከመ ቅርፅ አለው። ክትባቱ ልጆች በሽታ መከላከያ እንዲያዳብሩ ይረዳል። የቢሲጂ ክትባት እንደ የማጅራት ገትር ካሉ ከባድ የቲቢ አይነቶች ለመከላከል ይረዳል።

ጥናቶች እንደ ሚያሳዩት የBCG ክትባት ከተወሰደ በኋላ እስከ 15 አመታት ድረስ ይከላከላል።

አዲስ ለተወለዱ ህፃናት በግራ ክንድ የላይኛው ክፍል ላይ የቢሲጂ ክትባት ይሰጣል።

 

2. ፖልዮ

ፖልዮ በቫይረስ የሚመጣ ተላላፊ በሽታ ነው። ቫይረሱ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፈው በዋናነት ከሰገራ ወደ በአፍ መንገድ፣ በተበከለ ውሀ ወይም ምግብ ነው።

የመጀመሪያዎቹ ምልክቶች ትኩሳት፣ ድካም ፣ ራስ ምታት ፣ ማስመለስ ፣ የአንት መገተር እና የእግሮች ላይ ህመም ናቸው። ፖልዮ የነርቭ ስርአትን የሚያጠቃ እና ወደመተንፈሻ አካላት ሽባነት ሊያመራ ይችላል።

ፓልዮ በሰፊው የክትባት ዘመቻዎች አማካኝነት በአለም አቀፍ ሊጠፋ የተቃረበ በሽታ ነው።

የፖልዮ ክትባት ለጨቅላ ህፃናት ሲሰጥ የመጀመሪያው ክትባት በመጀመርያዎቹ 6 ሳምንታት እድሜ ውስጥ፣ ሁለተኛው ክትባት በአስረኛው ሳምንት እድሜ፣ ሶስተኛው ክትባት በአስራ አራተኛው ሳምንት እድሜ ባጠቃላይ አራት ጊዜ ይሰጣል።

 

3. ዲፍቴሪያ (diphtheria)

ዲፍቴሪያ የላይኛውን የመተንፈሻ አካል በሚያጠቃ ባክቴሪያ የሚመጣ በሽታ ነው። በዋነኛነት ጉሮሮን እና አፍንጫን ይጎዳል። ከዚያም ወፍራም ግራጫ ሽፋን ይፈጥራል።

ይህ ሽፋን የአየር መተላለፍያ መንገዶችን ሊያደናቅፍ እና የመተንፈስ ችግር ሊያስከትል ይችላል።

ዲፍቴሪያ እንደ ልብ እና ነርቭ ስርአት ያሉ የሰውነት ክፍሎችን ሊጎዳ የሚችል መርዝን ማምረት የሚችል በሽታ ነው።

ይህ ክትባት ለህፃናት በስድስተኛ ሳምንት እድሜ የመጀመሪያው ክትባት ፣ በአስረኛው ሳምንት እድሜ ሁለተኛው ክትባት እና በአስራ አራተኛው ሳምንት እድሜ ሶስተኛው ክትባት ባጠቃላይ ሶስት ጊዜ ክትባቱ ይሰጣል።

 

4. ትክትክ ሳል (pertussis)

ትክትክ ሳል (pertussis) የሚከሰተው በባክቴሪያ ቦርዴቴላ ፐርቱሲስ ሲሆን ይህም በሽታው በተያዘው ሰው ሳል እና ማስነጠስ በቀላሉ ሊተላለፍ ይችላል። የመተንፈሻ አካላትን በተለይም አፍንጫን እና ጉሮሮን የሚጎዳ የባክሪያ ኢፊክሽን ነው።

የመጀመሪያ ምልክቶች ብዙውን ጊዜ ከጉንፋን ፣ ከአፍንጫ ንፍጥ ፣ ትኩሳት እና ቀላል ሳል ጋር ተመሳሳይ ናቸው። ከባድ የሆነ የማያቋርጥ ሀይለኛ ሳል ፣ ማስመለስ ፣ መተንፈስ መቸገር ያስከትላል።

የፐርቱሲስ ክትባት ለህፃናት በስድስተኛ ሳምንት እድሜ የመጀመሪያው ክትባት ፣ በአስረኛው ሳምንት እድሜ ሁለተኛው ክትባት እና በአስራ አራተኛው ሳምንት እድሜ ሶስተኛው ክትባት ባጠቃላይ ሶስት ጊዜ ክትባቱ ይሰጣል።

 

5. ቴታነስ (መንጋጋ ቆልፍ)

ቴታነስ ክሎስትሪደም ቲታኒ በተባለ ባክቴሪያ የሚመጣ ኢንፊክሽን ነው። እነዚህ ባክቴሪያዎች ወደ ሰው ሰውነት ሲገቡ የሚያሰቃይ የጡንቻ መኮማተርን የሚያስከትል መርዝ ያመነጫሉ። ሌላው የቴታነስ ስም “መንጋጋ ቆልፍ” ነው። ብዙውን ጊዜ የአንድ ሰው አንገት እና መንጋጋ ጡንቻዎች እንዲቆለፉ ያደርጋል ፤ ይህም አፍን ለመክፈት ወይም ለመዋጥ አስቸጋሪ ያደርገዋል።

የቴታነስ ባክቴሪያ በአፈር ፣ በአቧራ እና በየአካባቢ ውስጥ ይገኛል። በተቆረጠ ቆዳ አማካኝነት አካል ውስጥ ሊገባ ይችላል።

የመንጋጋ ቆልፍ ክትባት ለህፃናት በስድስተኛ ሳምንት እድሜ የመጀመሪያው ክትባት ፣ በአስረኛው ሳምንት እድሜ ሁለተኛው ክትባት እና በአስራ አራተኛው ሳምንት እድሜ ሶስተኛው ክትባት ባጠቃላይ ሶስት ጊዜ ክትባቱ ይሰጣል።

 

6. ሂፓታይቲስ ቢ ቫይረስ (hepatitis B virus)

ሄፓታይተስ ቢ በደም ውስጥ በሚሰራጭ ቫይረስ አማካኝነት የሚመጣ እና ከእናት ወደ ልጅ በወሊድ እና በእርግዝና ጊዜ የሚተላለፍ በሽታ ሲሆን ጉበትንም የሚያጠቃ ቫይረስ ነው።

የአይን ወይም የሰውነት ቢጫ መሆንና፣ ተቅማጥ ፣ ማስመለስ ፣ መደካከም የጡንቻዎች የመገጣጠሚያ ወይም ሆድ ህመም የሄፓታይተስ በሽታ በህፃናት ሲከሰት ከምናያቸው ምልክቶች ዋና ዋናዎቹ ናችው ።

ሄፓታይተስ ቢ ክትባት ለህፃናት በስድስተኛ ሳምንት እድሜ የመጀመሪያው ክትባት ፣ በአስረኛው ሳምንት እድሜ ሁለተኛው ክትባት እና በአስራ አራተኛው ሳምንት እድሜ ሶስተኛው ክትባት ባጠቃላይ ሶስት ጊዜ ክትባቱ ይሰጣል።

 

7. ሄሞፊሊያ ኢንፍሉዌዛ አይነት ቢ ( hib)

ሄሞፊሊያ ኢንፍሉዌዛ አይነት ቢ ( hib) ለህይወት አስጊ የሆነ ኢንፌክሽን የሚያመጣ ባክቴሪያ ሲሆን በተለይም በልጆች ላይ ወደ ከባድ ህመም ሊያመራ ይችላል።

እንደ ማጅራት ገትር፣ ኤፒግሎቲተስ (የንፋስ ቧንቧ የላይኛ ክፍል መቆጣት) እና የሳንባ ምች ያሉ ሁኔታዎች ያስከትላል።

በሄሞፊሊያ ኢንፍሉዌዛ ምክንያት የሚከሰተው በሽታ በዋናነት በሳል ወይም በማስነጠስ ወይም በበሽታው ከተያዘ ሰው አፍንጫ እና ጉሮሮ በሚወጣ ፈሳሽ ግንኙነት ይተላለፋል።

የዚህ በሽታ መከሰትን በመቀነስ ረገድ መደበኛ ክትባቶች በጣም ውጤታማ ናቸው።

ሄሞፊለስ ኢንፍሉዌዛ አይነት ቢ ( hib) ክትባት ለህፃናት በስድስተኛ ሳምንት እድሜ የመጀመሪያው ክትባት ፣ በአስረኛው ሳምንት እድሜ ሁለተኛው ክትባት እና በአስራ አራተኛው ሳምንት እድሜ ሶስተኛው ክትባት ባጠቃላይ ሶስት ጊዜ ክትባቱ ይሰጣል።

 

8. ኒውሞኮካል ባክቴሪያ (pneumococcal bacterial)

ኒውሞኮከስ በሽታ ከሰው ወደ ሰው በቅርብ ንክኪ የሚተላለፍ በባክቴሪያ የሚመጣ በሽታ ነው።

የኒውሞኮከስ ክትባት ከማጅራት ገትር ፣ ከሳንባ ምች በተጨማሪም ከጆሮ ኢንፌክሽን ለመከላከል ይረዳል።

የኒውሞኮከስ ክትባት ለህፃናት በስድስተኛ ሳምንት እድሜ የመጀመሪያው ክትባት ፣ በአስረኛው ሳምንት እድሜ ሁለተኛው ክትባት እና በአስራ አራተኛው ሳምንት እድሜ ሶስተኛው ክትባት ባጠቃላይ ሶስት ጊዜ ክትባቱ ይሰጣል።

 

9. ሮታ ቫይረስ በሽታ 

ሮታ ቫይረስ የሆድ እና አንጀት መቆጣት ተላላፊ ኢንፌክሽን ነው። ይህም በተለይ ልጆች ላይ ከባድ ተቅማጥና ትውከት ፣ ትኩሳት እና የሆድ ህመም ሊያስከትል ይችላል። ሮታ ቫይረስ ክትባት ከሮታ ቫይረስ ለመከላከል ይረዳል።

የሮታ ቨይረስ ክትባት ለህፃናት በስድስተኛ ሳምንት እድሜ የመጀመሪያው ክትባት እና በአስረኛው ሳምንት እድሜ ሁለተኛው ክትባት ባጠቃላይ ሁለት ጊዜ ይሰጣል።

 

10. ኩፍኝ (measles) 

ኩፍኝ በአየር ወለድ የሚተላለፍ በሽታ ሲሆን ከአንድ ሰው ወደ ሌላው በሳል እና በማስነጠስ እንዲሁም ከአፍንጫ ወይም ከአፍ ፈሳሽ ጋር በመነካካት ይተላለፋል።

ምልክቶቹም እንደ ከፍተኛ ትኩሳት ፣ሳል ፣ የአፍንጫ ፈሳሽ እና በመላው ሰውነት ላይ ሽፍታ ያስከትላል። የኩፍኝ በሽታ የመሃል ጆሮ ኢንፌክሽን፣ የሃንባ ምች እና ተቅማጥ ያመጣል። የኩፍኝ ክትባት በሽታውን ለመከላከል ይረዳል።

የኩፍኝ ክትባት ለህፃናት በዘጠነኛው ወር እድሜ የመጀመሪያው ክትባት እና በአስራ አምስተኛው ወር እድሜ ሁለተኛው ክትባት ባጠቃላይ ሁለት ጊዜ ክትባቱ ይሰጣል።