ይህ ሳምንት አለምአቀፍ የክትባት ሳምንት በመባል ይከበራል፡፡ አጋጣሚውን በመጠቀም ክትባቶች ለጤናችን የሰጡትን ጥቅም እና ተያያዥ ጥያቄዎች ከታች እንመልሳለን፡፡
- በክትባት መኖር ከምድረ ገጽ የጠፉ ወይም የበሽታ የማስከተል አቅማቸው የተዳከሙ ህመሞች የትኞቹ ናቸው?
ተጋላጭ ለሆኑ ሰዎች የሚከተሉትን ክትባቶች በመከተብ፣
- (ከባክቴርያዎች) የኮሌራ፣ ዲፍቴርያ፣ በሶስት የተለያዩ ባክቴርያዎች የሚከሰቱን የማጅራት ገትር ህመሞች፣ ሳንባ ነቀርሳ (ቲቢ)፣ ትክትክ፣ ቴታነስ፣ ታይፎይድ ህመሞችን
- (ከቫይረሶች) – የዴንግ፣ በሶስት የተለያዩ ቫይረሶች የሚከሰቱን የጉበት ኢንፌክሽን (ሄፓታይቲስ) ህመሞችን፣ ኢንፍሉኤንዛ፣ ኢቦላ፣ በነፍሳት የሚተላለፉ ሁለት በተለያዩ ቫይረሶች የሚከሰቱን የማጅራት ገትር ህመሞች፣ ፖሊዮ፣ ኩፍኝ፣ የጆሮ ደግፍ፣ ሩቤላ፣ የእብድ ውሻ በሽታ፣ የማኅፀን ጫፍ ካንሰር አምጪ (HPV) የቫይረስ ህመምን፣ የሮታ ቫይረስ (በህፃናት የሆድ ህመም አምጪ)፣ ቢጫ ወባ፣ አልማዝ ባለጭራ እና የጉድፍ ህመሞች
የሚያስከትሉትን ህመም እና ሞት በብዙ እጥፍ መቀነስ ተችሏል፡፡
እነዚህ ክትባቶች በመኖራቸው ባሁኑ ሰአት ሀኪሞች በተለይ በተለይ የዲፍቴርያ፣ የማጅራት ገትር ህመሞች፣ ቴታነስ፣ ፖሊዮ፣ ኩፍኝ፣ የጆሮ ደግፍ፣ የእብድ ውሻ በሽታ ህመሞችን በሽተኞች ላይ ሳያዩ አመታት እንዲቆጠሩ እያስገደደ ነው፡፡ የተለያዩ እክሎች በማጋጠማቸው እስካሁን በክትባት ከምድረ ገጽ የጠፋ ብቸኛ በሽታ እ.ኤ.አ. በ1980 ፈንጣጣ (Small pox) ብቻ ነው፡፡ በክትባት ለመጥፋት በጣም የቀረበው የፖልዮ (የልጅነት ልምሻ) በሽታ በአለም ዙርያ በአመት ከ30 ያነሱ ሰዎች ላይ እየታየ ነው፡፡ ህመሞቹን እየዘነጋናቸው ሲመጡ ምን እንዳጠፋቸውም እየረሳን ነው፡፡ ውለታን እንደመርሳት ይቆጠራል፡፡
- ክትባቶች የህብረተሰብ ጤና በተለይም የህፃናት ጤና አጠባበቅን በተመለከተ እስካሁን ምን ያህል ሞት ተከላከሉ?
በ1974 የፀረ ስድስት ክትባቶችን (የሳንባ ነቀርሳ (ቲቢ)፣ ትክትክ፣ ቴታነስ፣ ዲፍቴርያ፣ ፖሊዮ እና ኩፍኝ) በአለም በሰፊው ለማዳረስ ስምምነት ከተደረገ በኋላ (ከዛ በኋላ የተመረቱትን እና የተካተቱትን ክትባቶች ሳይጨምር) ስድስቱ ክትባቶች በአመት ከሁለት ሚሊዮን በላይ የህፃናት ሞቶችን በአለም ይከላከላሉ፡፡ ይህ ቁጥር ባለፉት 4 ወራት የCOVID19 ህመም ካስከተላቸው ሞቶች በ10 እጥፍ ይበልጣል፡፡
- የማኅፀን ጫፍ ካንሰርን ለመከላከል ክትባቶች ምን አስተዋጽኦ አላቸው?
የማኅፀን ጫፍ ካንሰር ብዛት ያላቸውን ሴቶች በማጥቃት 4ኛ ደረጃ ላይ ይቀመጣል፡፡ በአመት በአለም 570,000 አዳዲስ ታማሚዎች ላይ ሲታይ ከነዚህም ከ90% በላይ የሚሆኑት በታዳጊ ሀገሮች ውስጥ ይከሰታሉ፡፡ በተመሳሳይ በአለም 311,000 ሴቶችን ለሞት ይዳርጋል፡፡ ለታዳጊ ሴቶች የሚሰጡት የማኅፀን ጫፍ ካንሰር ክትባቶች ከ95% በላይ የማኅፀን ጫፍ ካንሰሮችን የሚከላከሉ ሲሆን በአለም ዙርያ ከ100 ሀገራት በላይ ይሰጣሉ፡፡
- የማኅፀን ጫፍ ካንሰር ክትባቶች መሀንነትን እንደሚያስከትሉ የሚያሳዩ ትክክለኛ የምርምር መርህን የተከተሉ ጥናቶች የሉም፡፡
በተቃራኒው በአመት ሰባት ሺ አዳዲስ ሴቶች በማኅፀን ጫፍ ካንሰር ለሚያዙባት እና በአመት ከነባር እና አዲስ ታማሚዎች ውስጥ አምስት ሺ ሴቶችን በማኅፀን ጫፍ ካንሰር በሞት ለምታጣው ኢትዮጵያ በክትባት 95 ከመቶውን መከላከል በጣም አስፈላጊ ነው ፡፡ ከላይ የጠቀስኩት ቁጥር ህክምና ፍለጋ ሆስፒታል ከሚመጡት ውስጥ ነው፡፡ በአካባቢያቸው በቅርበት ህከምና ባለመኖር እና ህመማቸው ሳይታወቅ የሚያልፉት ሲጨመሩ ባልተከተቡት ላይ ጉዳቱ የበለጠ የከፋ እንደሆነ ማሰብ ይቻላል፡፡
- ክትባቶች ኦቲዝምን አያስከትሉም፡፡
ክትባቶች (በተለይ የኩፍኝ፣ የጆሮ ደግፍ እና የሩቤላ ክትባቶች) ኦቲዝምን አያስከትሉም፡፡ አለማስከተል ብቻ ሳይሆን ያልተከተቡ ልጆች ባለማችን አሁን ባሉ የተላላፊ በሽታዎች ነባራዊ ሁኔታ አማካይ እድሜያቸው በእጅጉ ይቀንሳል፡፡ የኩፍኝ ክትባቶች በሀገራችን በሁለት የእድሜ ክልል የሚሰጥ ሲሆን በብዙ የአለም ሀገራት የኩፍኝ፣ የጆሮ ደግፍ እና የሩቤላ ክትባቶችን በአንድ መርፌ ይሰጣሉ፡፡ ባለፉት 20 አመታት ይህ የ3 በአንድ ክትባትን ጨምሮ ሁሉም ክትባቶች በብዙ ህፃናቶች ላይ ተጠንተው በጭራሽ ኦቲዝምን እንደማያስከትሉ ተረጋግጧል፡፡ እነዚህን ጥናቶች ለማንበብ ከታች ያሉትን ሊንኮች ተጫኑ፡፡
- በዴንማርክ በ650000 ልጆች ላይ የተሰራ ጥናት
- በአውስትራልያ በአንድ ሚልዮን ልጆች ላይ የተሰራ ጥናት
- በእንግሊዝ ህፃናት ላይ የተሰሩ ጥናቶች
- በጃፓን ኦቲዝም ክትባቱ ባልተሰጠባቸው ጊዜያት ከተሰጠባቸው ጊዜያት በላይ መከሰቱን የሚያሳይ ጥናት
- በካሊፎርንያ ከ1980 – 1994 በተወለዱ ልጆች ላይ የተሰራ ጥናት
- ቁጥራቸው በጣም አነስተኛ የሆኑ (ከ0.1% በታች) ሰዎች ለክትባቶች አለርጂክ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን የአለርጂ ስሜቶች በህክምና ይታከማሉ፡፡ መጠነኛ ትኩሳት፣ የክትባት መርፌ የተወጉበት ቦታ ማበጥ፣ ለደቂቃዎች የሚታዩ ድንግዝግዝ ማለት በአንዳንድ ክትባቶች ሊታዩ የሚችሉ የጎንዮሽ ጉዳቶች ቢሆኑም ለአጭር ሰአታት የሚቆዩ እና ክትባቶቹ ከሚሰጡት ከፍተኛ ጥቅም ጋር የማይነፃፀሩ ናቸው፡፡ ይህንን ያላመዛዘኑ የሚድያ ሪፖርቶች አንዳንዴ ይታያሉ፡፡ ስለዚህም ስሜቶቹ እንዴት መጡ – ክትባቱን ከወሰዱ ሰዎች ስንቱ ላይ ታዩ – በምን ይታከማሉ የሚለው ሚዛን ውስጥ ገብቶ ለህብረተሰቡ መዘገብ አለበት፡፡
የጤና ወግ
በመረጃ የተመሰረተ ሕክምና ብቻ ።
………………………………………………………………………………………………………………………..
ይህ የጤና ወግ ድረ ገፅ ነው።
ስለ ጤንነታችሁ ማወቅ የምትፈልጉትን መረጃ የምታገኙበት ፣ በህክምና ባለሙያዎች የሚዘጋጅ የመረጃ ምንጭ ነው።
ሁልግዜም ከሀኪማችሁ ተማከሩ፣ ተጨማሪ መረጃ ከፈለጋችሁ የኛን ድረ ገፅ ጎብኙ።
በጥናት የተደገፈ መረጃ ብቻ እናቀርባለን።
የህክምና ባለሙያዎች ለህሙማኖቻችሁ የሚሆን የሚነበብ መረጃ ከፈለጋችሁ ይህን ግፅ ጠቁሟቸው። ህሙማኖቻችሁ እንዲያውቁት የምትፈልጉትን ነገር መረጃ ጠቅሳችሁ ፃፉልን፣ ስምችሁን ጠቅሰን እናወጣለን። የህክምና ተማሪዎች እንዲጽፉ እናበረታታለን።
በተጨማሪም በጤና ወግ ፖድካስት፣ በ ዩትዩብ ፣በ ትዊተር ፣ በ ፌስቡክ ፣ በቴሌግራም የተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ ገፆቻችን ታገኙናላችሁ