በዶ/ር ናታን ሙሉብርሃን (የድንገተኛና ፅኑ ህክምና ስፔሻሊስት)
ማንኛውም ወደ ሰውነታችን ገብቶ ጉዳት፣ ህመም ወይም ሞት ሊያስከትል የሚችል ንጥረ ነገር መርዝ ተብሎ ሊጠራ ይችላል። መመረዝ የምንለው ባዕድ ንጥረ ነገር (መርዝ) ወደ ሰውነታችን ውስጥ በተለያየ መልኩ ገብቶ ጤንነታችንን ሲያውከዉና ለጉዳት ሲያጋልጠው ነው። አንድ ሰው በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ሊመረዝ ይችላል። መርዝ በአፍ፣ በቆዳ፣ በትንፋሽ፣ በአይን፣ በመርፌ (በደም ስር፣ በጡንቻ፣ በስብ ስር) ወደ ሰውነታችን ሊገባ ይችላል።
ያልታዘዙ መድሃኒቶችን በመውሰድ ወይም የታዘዙትንም ቢሆን በተሳሳተ መጠን ከተወሰደ ሊመርዘን ይችላል። ከ5 ዓመት በታች ያሉ ህጻናት፣ የአእምሮ ህመም ያለባቸው፣ የማየት ችግር ያለባቸው በዋናነት ለመመረዝ የተጋለጡ ናቸው።
በቤት ውስጥ ለተለያዩ አላማዎች የምንገለገልባቸው ምርቶች ያለአግባብ ከተጠቀምንባቸው ሊመርዙን ይችላሉ። ከነዚህም መካከል፡ አልኮል (ሳኒታይዘር፣ ሽቶ፣ የአፍ ሳሙና)፣ መድሃኒቶችና ቫይታሚኖች፣ ማጽጃ ምርቶች፣ቀለምና ማጣበቂያ፣ ፀረ አረም፣ ፀረ ነፍሳት፣ የመኪና ዘይት፣ማለስለሻ፣ ሲጋራ፣ ብረቶች (ሊድ) ወዘተ…ተጠቃሽ ናቸው።
የመመረዝ ምልክቶች
በአፍ የተወሰደ መርዝ ምልክቶች፡ ማቅለሽለሽ፣ ትውከት፣ የሆድ ቁርጠት፣ ማንቀጥቀጥ፣ ፈጣን ወይም ደካማ የሆነ የልብ ምት፣ ራስን መሳት።
በማሽተት የተወሰደ መርዝ፡ በአፍንጫ በኩል ወደ ሰውነት የሚገባ ሲሆን መርዛማ ጭስ፣ ወይም ጋዝ በማሽተት ሊከሰት ይችላል። በማሽተት የገባ መርዛማ ነገር ምልክቶቹም የመተንፈስ ችግር፣ አየር ማጠር፣ የቆዳ መገርጣት፣ የቆዳችን ቀለም መጥቆር እና የመሳሰሉት ናቸው።
በንክኪ፣ በቆዳ ስር የገባ መመረዝ ምልክቶች ፡ የ ህመም ስሜት፣ መቅላት፣ ማሳከክ ፣
ወደ ዓይናን የተረጨ መርዝ ፡ የአይን ህመም፣ መቆጥቆጥ፣ የእይታ ችግር ፣ የአይን መቅላት፣ የአይን አካባቢ እብጠት ናቸው።
ያልታሰበ መመረዝን ለመከላከል
- መድሃኒቶችንና የቤት ውስጥ መገልገያ ምርቶችን ህጻናት በማይደርሱበት ቦታ ያስቀምጡ።
- መርዛማ የሆኑ ንጥረ ነገሮችን ቁልፍ ባለው ሳጥን ያስቀምጡ።
- ህጻናትና የአእምሮ ህመም ያለባቸው ሰዎችን በደንብ ይከታተሏቸው።
- መድሃኒቶችንና የቤት ውስጥ መገልገያ ምርቶችን በመጡበት እቃ ማስቀጥ እንዲሁም በግልፅ በሚታይ መልኩ ምንነታቸውን የሚገልፅ ፅሁፍ ያኑሩባቸው።
- የመርዝ ምልክቶችን እና አደገኝነታቸውን ለህጻናት ያስተምሩ።
- ለህጻናት መድሃኒት ሲሰጡ “ከረሜላ“ ነው እያሉ መስጠት መድሀኒቱን በድብቅ እንዲወስዱ ሊያደበረታታቸው ስለሚችል ሌሎች ማባበያ መጠቀሙ የተሻለ ነው።
- መድሀኒት ከመውሰድዎ በፊት በመሸፈኛው ላይ የተፃፈውን የአገልግሎት ማብቂያ ጊዜ (Expire date) እና የታዘዘ መጠን ትክክለኛ መሆኑን ያረጋግጡ። አብዛኞቹ መድሀኒት ተመሳሳይ መሸፈኛ ወይም ቀለም ነገር ግን የተለያየ መጠን እና አገልግሎት ሊኖራቸው ይችላል።
- አላስፈላጊ ወይም ጊዜ ያለፈባቸው መድሃኒቶችን በሚገባ ያስወግዱ ።
የመመረዝ የመጀመሪያ እርዳታ
- ተጠቂው የሚከተሉት ምልክቶች ካሉት ወደ 907 ይደውሉና እርዳታን ይጠይቁ።
- ራሱን ከሳተ፣
- ለመተንፈስ ከተቸገረ፣
- ካንቀጠቀጠው (እንደ የሚጥል በሽታ)፣
- ደም ካስመለስው/ካስቀመጠው፣
- ደረት ውጋት/ ህመም ካለው፣
- የማይተባበርና አደገኛ ጸባይ ካለው።
- የህክምና እርዳታ ተቋም እስኪደርሱ የመርዙን ምንጭ እርሶ ላይ አደጋ በማያደርስ መልኩ ያስወግዱ፤ እንደ ማላታይን፣ ዲዲቲ… ያሉ መርዞች በቀላሉ በትንፋሽና በንክኪ ሊመርዙን ስለሚችሉ ተጎጂውን ስንረዳ የራስ መከላከያ የፊት ጭንብል፣ ጓንት፣ ቡትስ ጫማ ማድረግ ይኖርብናል።
- ለተጠቂው የሚበላም ሆነ የሚጠጣ አይስጧቸው፤
- የተወሰደው መርዝ የሚያቃጥል ከሆነ በሚወሰድበት ጊዜ ከአፍ ጀምሮ እስከ ጨጓራ ያለውን የምግብ መተላለፊያ ስለሚያቃጥለው እንዲያስታውኩ ማድረግ ተገቢ አይደለም፤
- በረኪና ለወሰደ ሰው በተለምዶ እንደሚደረገው መርዙን እንዲያስታውከው ለማድረግ የሚደረጉ እንጥል አካባቢ መንካት፤ እንዲሁም ለማርከሻ ተብሎ የሚሰጥ ወተት መጠቀም አይመከርም።
- በንክኪ፣ በቆዳ ስር የገባ መመረዝ ከሆነ የተጎዳውን ሰው ልብስ በጥንቃቄ ከሰውነቱ ላይ ቆርጦ ማስወገድና፣ በርከት ያለ ውሃ ለ20 ደቂቃ ያህል በሰውነቱ ላይ ያፍስሱ። (ይሁንና አንዳንድ መርዞች ውሃ ሲነካቸው የበለጠ መርዛማ ሊሆኑ ይችላሉ)
በዶ/ር ናታን ሙሉብርሃን (የድንገተኛና ፅኑ ህክምና ስፔሻሊስት)