በቤቴልሄም መኮነን (በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ህ/ጤ/ሳ/ኮ የህክምና ተማሪ-C2)
አብዛኞቻችን ካንሰር የሚለውን ስም በሀገራችን መስማት ከጀመርን ሩቅ አይደለም፡፡ በተለይም በገጠሩ የሀገራችን ማህበረሰብ ዘንድ ገና በመታወቅ ላይ ያለ ህመም ነው፡፡ በዚህም የተነሳ መታከም እንደሚችል ከማሰብ ይልቅ የፈጣሪ ቁጣ እንደሆነ የሚያስቡም በርካቶች ናቸው፡፡
በሀገራችን በርካታ ጥናቶች ባይደረጉም፣ ካንሰር 5.8 ከመቶ አመታዊ የሞት ምጣኔ እንዳለው ይገመታል፡፡ በስፋት ተሰራጭተው ከሚገኙት መካከል የጡት ካንሰር 30.2ከመቶ የሚሆነውን ድርሻ ሲይዝ የማህፀን ጫፍ ካንሰር 13.4ከመቶ እንዲሁም የትልቁ አንጀት ካንሰር 6.3ከመቶ የሚሆነውን ድርሻ በመያዝ ተቀምጧል፡፡
የማህፀን ጫፍ ካንሰር በሴቶች ላይ ከሚከሰቱ ሌሎች ካንሰሮች በ4ኛ ደረጃ ላይ ይቀመጣል፡፡ እንደ የአለም ጤና ጥበቃ ድርጅት ጥናት መሰረት በ2020 በመላው ዓለም ከ604,000 በላይ ሴቶች በዚህ ካንሰር የተጠቁ ሲሆኑ ከ342,000 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ለሞት ተዳርገዋል፡፡ በኢትዮጵያም ከ6,294 የካንሰሩ ተጠቂዎች 4,884 የሞት ሰለባዎች ሆነዋል፡፡
በ2019 የተደረገው የጅማ ዩኒቨርሲቲ ጥናት እንደሚያሳየው ከሆነ አብዛኞቹ የካንሰሩ ተጠቂዎች ስለ ካንሰሩ ምንም እውቀት የሌላቸው ሲሆኑ ሲመረመሩም በስፋት ወደ ሰውነታቸው ከተሰራጨ በኋላ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የሚታየው የግንዛቤ ማነስ ትኩረት የሚሻ ነው፡፡
የማህፀን ጫፍ ካንሰር ምንድን ነው?
✓ መከላከል እንደሚቻል እንዲሁም ቢታከም መዳን እንደሚችል ያውቃሉ ?
✓ ይህ ካንሰር ማህፀን በር አካባቢ ያሉ ህዋሶቻችን ከመጠን በላይ ሲራቡ የሚፈጠር እጢ ነው፡፡
✓ ከሞላጎደል ሁሉም(99%) የማህፀን ጫፍ ካንሰሮች ሂውማን ፓፒሎማ ቫይረስ (Human Papilloma Virus) በተሰኘ የቫይረስ ኢንፌክሽን ምክንያት የሚከሰቱ ናቸው፡፡ ይህ ቫይረስ የግብረ-ስጋ ግንኙነት በማድረግ የሚተላለፍ ነው፡፡ አንዲት ሴት በዚህ ቫይረስ (HPV) ብትጠቃም፣ ቫይረሱ በራሱ ጊዜ የመዳን እድል አለው በተለይም ከ90ከመቶ በላይ በ2ዓመት ይድናል፡፡
በምን ምክንያት ወደ ካንሰር ሊለወጥ ይችላል?
➢ አንዲት ሴት ከ16 ዓመቷ በፊት ወሲብ መፈፀም ከጀመረች አልያም ደግሞ የወር አበባ ማየት በጀመረችበት ዓመት ወሲብ ከፈፀመች
➢ ከአንድ በላይ የወሲብ ጓደኞች ከነበሯት
➢ የሚዋጥ የወሊድ መቆጣጠሪያ የምትጠቀም ከሆነ በተለይም ለ5 ዓመትና ከዚያ በላይ ➢ ሲጋራ የምታጨስ ከሆነ
➢ የተዳከመ በሽታን የመቋቋም አቅም ካላት
➢ የምግብ ዕጥረት ለምሳሌ እንደ ቫይታሚን ቢ፣ሲ፣ኢ የመሳሰሉት
➢ በአባላዘር በሽታዎች ከተጠቃች
➢ የቅድመ የማህፀን ጫፍ ካንሰር ምርመራ አድርጋ የማታውቅ ከሆነ
➢ ዝቅተኛ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ
ምልክቶቹ ምንድናቸው?
ከሆነ በአስቸካይ በአቅራቢያዎ ወደሚገኝ የጤና ተቋም በመሄድ የሀኪም እርዳታ ማግኘት ያስፈልጋል፡፡
የመጀመሪያ ደረጃ ካንሰር ምንም ምልክት ላያሳይ ይችላል ወይም ደግሞ መጠነኛ ምልክቶች ብቻ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ስለሆነም መዘናጋት ተገቢ አይደለም፡፡
የማህፀን ጫፍ ካንሰርን እንዴት እንከላከል?
ቅድመ መከላከል
ለታዳጊ ሴቶች ማለትም ከ9-14ዓመት ለሆኑ
➢ የሂውማን ፓፒሎማ ቫይረስ(HPV) ክትባት መስጠት
➢ በሀገራችንም እ.ኤ.አ ከ2018 ጀምሮ ከ14 ዓመት በላይ ለሆኑ ታዳጊዎች በየትምህርት ቤቱ እንዲሁም በጤና ተቋማት የሂውማን ፓፒሎማ ቫይረስ(HPV) ክትባት መሰጠት ተጀምራል፡፡ይህ ተግባር ሁሉንም ዜጋ ተደራሽ በማድረግ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡
ለሴቶችና ለወንዶች
➢ እድሜና ባህልን መሰረት ያደረገ የጾታዊ ግንኙነት ትምህርት መስጠት
➢ ወሲብ መፈፀም ለጀመሩ ኮንዶምን እንዲጠቀሙ ማበረታታት
➢ የወንዶች ግርዛት
➢ ስለ ሲጋራ የጤና ጠንቆች ግንዛቤ መስጠት
2ኛ ደረጃ መከላከል
➢ 30ዓመትና ከዛ በላይ ለሆኑ ሴቶች የሚተገበር ሲሆን የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም የቅድመ ካንሰር ምርመራ ማድረግ ነው
3ኛ ደረጃ መከላከል
እንደአስፈላጊነቱ ለሁሉም ሴቶች ሲሆን በተለይም አደገኛ የሆኑትን የካንሰር ምልክቶች ማሳየት ለጀመሩ ሴቶች ተገቢውን ህክምና መስጠት ነው፡፡
አማራጮቹም ፡-
– የቀዶ ህክምና
– የጨረር ህክምና
– ኬሞቴራፒ
የአሜሪካ የካንሰር ማህበረሰብ፣ የማህፀን ጫፍ ካንሰር ቅድመ ምርመራን በተመለከተ መቼ መጀመር እንዳበትና መች እንደሚቋረጥ የሚከተለውን ያስቀምጣል ፡–
– አንዲት ሴት ወሲብ መፈፀም ከጀመረች ከ3ዓመት በኋላ፤ ከ21ዓመት ባይበልጥ ይመከራል
– እንደአስፈላጊነቱ በየ2 ወይም በ3 ዓመት ልዩነት መደገም አለበት፡፡ ይሁንእንጂ እንደ ኤች.አይ.ቪና ሌሎች በሽታን የመቋቋም አቅምን የሚያዳክሙ ሁኔታዎች ካሉ በየአመቱ መደገም እንዳለበት ተቀምጧል፡፡
– አንዲት ሴት ላለፉት 10ዓመታት ምንም አስጊ ሁኔታ ላይ ካልሆነች ከ70 ዓመቷ በኋላ የቅድመ ምርመራውን ማቋረጥ ትችላለች
ዋቢ
- Saleem A, Bekele A, Fitzpatrick MB, Mahmoud EA, Lin AW, Velasco HE, et al. Knowledge and awareness of cervical cancer in Southwestern Ethiopia is lacking: A descriptive analysis. PLoS One. 2019;14(11):e0215117.
- Begoihn M, Mathewos A, Aynalem A, Wondemagegnehu T, Moelle U, Gizaw M, et al. 2019. Cervical cancer in Ethiopia–predictors of advanced stage and prolonged time to diagnosis. Infectious agents and cancer, 14(1):1-7.
- world health organization.2021. Cervical cancer. https://www.who.int/health-topics/cervical cancer#tab=tab_1
- world health organization.2021. cervical cancer elimination initiatives. https://www.who.int/initiatives/cervical-cancer-elimination-initiative
ይህ ፅሁፍ በዶ/ር ዳዊት ወርቁ (የማህፀን እና ፅንስ ስፔሻሊስት/የማህፀን ካንሰር ልዩ ስፔሻሊስት) እና የጤና ወግ ኤዲተሮች የተገመገመ ነው።