(በሰብለወንጌል አባተ በቅዱስ ጳውሎስ ሆ/ሚ/ሜ/ኮ የህክምና ተማሪ-C1)
ይህ የብዙዎቻችን ታሪክ ነው፡፡ በበዓል ወይም በሌላ አጋጣሚ ከጓደኞቻችን፣ ከቤተሰቦቻችን፣ ከዘመዶቻችን፣ ከጎረቤቶቻችን ወይም ከስራ ባልደረቦቻችን ጋር ተሰብስበን ባለንበት ድፎ ዳቦ (በተለይ የስንዴ) የማይመገብ አንድ ሰው አለ፡፡ ይህ ሰው ለምን እንደማይመገብ ስንጠይቀው የሚሰጠን የተለመደች መልስ “ስኳር አለችብኝ አይደል? ለዚያ ነው” የሚል ነው፡፡ በዚህ ምላሽ የማንረካ ብዙዎቻችን ግለሰቡን “ግድ የለህም ምንም አይልህም፣ ዛሬ ዓመት በዓልም አይደል?” ብለን ለማሳመን እንሞክራለን::
ለመሆኑ ስለ ስኳር በሽታ ምን ያህሎቻችን እናውቃለን?
የስኳር በሽታ አንድ ሰው በደሙ ውስጥ ያለው የስኳር (ግሉኮስ) መጠን እንዲበዛና እንደ ዓይን፣ ኩላሊት፣ ልብ፣ የደም ስርና ነርቭ ላይ ጉዳት እንዲያደርስ የሚያደርግ የበሽታ ዓይነት ነው፡፡ ለበሽታው እንደ ዋና መንስኤ የሚጠቀሱት በሰውነታችን የሚመረተው የኢንሱሊን መጠን በቂ አለመሆንና ሰውነታችን የተመረተውን ኢንሱሊን በአግባቡ መጠቀም አለመቻል ናቸው።
ኢንሱሊን ምን እንደሆነ በአጭሩ ለመግለፅ ያህል እንደ ስንዴ ዳቦ፣ ድንች፣ ስኳርነት ያላቸው መጠጦችንና ሌሎች ምግቦች በምንመገብበት ጊዜ ሰውነታችን ምግቡን ወደ ስኳር (ግሉኮስ) ይቀይረዋል፤ ይህ ስኳርም ወደ ደም ውስጥ በመግባት ወደተለያዩ የሰውነት ህዋሳት ለመድረስ ይዘጋጃል፡፡ በዚህ ጊዜ የሰውነታችን ቆሽት (pancreas) ኢንሱሊን የሚባለውን ንጥረ ነገር ያመነጫል፤ ይህ ኢንሱሊን የሰውነታችን ህዋሳት እንዲከፈቱ በመርዳት የተመረተው ግሉኮስ (ስኳር) ወደ ውስጥ እንዲገባ በማድረግ ለሀይል ምንጭ እንድንጠቀምበት ይረዳል።
ታዲያ የስኳር ታማሚዎች ከላይ በገለፅናቸው ከኢንሱሊን ጋር የተያያዙ ችግሮች በደማቸው ውስጥ ከመጠን በላይ ስኳር ይከማችና ሰውነታቸው ላይ ጉዳት ያደርሳል፡፡
የተለያዩ የስኳር በሽታ ዓይነቶች ሲኖሩ ዋነኞቹ
- አይነት አንድ
- አይነት ሁለት እና
- በእርግዝና ወቅት የሚከሰት የስኳር በሽታዎች ናቸው፡፡
አይነት አንድ የስኳር በሽታ የሚከሰተው ሰውነታችን በተለያዩ ምክንያቶች ቆሽታችንን በተለይም ኢንሱሊን የሚያመርቱ ቤታ የተሰሠኙ ህዋሳትን በሚያጠቃበት ጊዜ ነው። አብዛኛውን ጊዜ የሚከሰተው በሕጻንነትና በጉርምስና ጊዜ ሲሆን ሆኖም ግን በሌላ የእድሜ ክልል ውስጥ አይከሰትም ማለት አይደለም።
አይነት ሁለት የስኳር በሽታ በአብዛኛው የተለመደው የስኳር በሽታ አይነት ሲሆን ከቆሽት የሚመነጨው ኢንሱሊን ስራውን በሚገባ ሊሰራ ባለመቻሉ ወይም መጠኑ እጅግ በማነሱ የሚመጣ ህመም ነው፡፡
በእርግዝና ወቅት የሚከሰተው የስኳር በሽታ ደግሞ ከማርገዛቸው በፊት የስኳር በሽታ በሌለባቸው ነፍሰጡሮች ላይ የሚከሰት የስኳር በሽታ ዓይነት ነው፡፡ በእርግዝና ወቅት የሚከሰት የስኳር በሽታ ከሚያመጣቸው ችግሮች ውስጥ የተረገዘው ህፃን ኪሎ ከመጠን በላይ መሆን፣ ያለ ጊዜው መወለድና ለእናትየው ደግሞ ከእርግዝና በኋላ የአይነት ሁለት የስኳር በሽታ የመያዝ እድል መጨመር ይገኙበታል፡፡
የስኳር በሽታ ምልክቶች
የአይነት አንድና የአይነት ሁለት የስኳር በሽታ ምልክቶች በሁለቱም ላይ የሚታዩ ቢሆንም በብዛት በሚስተዋሉበት የስኳር በሽታ አይነት በሚከተለው መልኩ ሊከፈሉ ይችላሉ፡፡
የአይነት አንድ ስኳር በሽታ ምልክቶች
ቶሎ ቶሎ የውሃ ጥማት መሰማት
ቶሎ ቶሎ መራብ
ቶሎ ቶሎ መሽናት (በተለይ በማታ ጊዜ)
የክብደት መቀነስ
የድካም ስሜት ና ሌሎችም ሲሆኑ
የአይነት ሁለት ስኳር በሽታ ምልክቶች
የአፍና የቆዳ መድረቅ
የቁስል ቶሎ አለመዳን
እግርና እጅ የማቃጠልና የመደንዘዝ ስሜት ይገኙበታል፡፡
ለስኳር በሽታ አጋላጭ ሁኔታዎች
የአይነት አንድ የስኳር በሽታ በግልፅ የታወቁ አጋላጭ ሁኔታዎች ባይኖሩትም የልጅነት እድሜና በቤተሰብ የአይነት አንድ ስኳር በሽታ መኖር ለህመሙ የመጋለጥ እድልን ከፍ እንደሚያደርግ ይታመናል፡፡ የአይነት ሁለት ስኳር በሽታ አጋላጭ ሁኔታዎች የሚባሉት ደግሞ ከመጠን በላይ ውፍረት፣ የሰውነት እንቅስቃሴ አለማድረግ፣ 45 አመትና ከዚያ በላይ እድሜ እና በቤተሰብ የአይነት ሁለት ስኳር በሽታ መኖር ናቸው፡፡
ታዲያ ከላይ የጠቀስናቸውን አጋላጭ ሁኔታዎች በቀላሉ የአኗኗር ዘይቤ ለውጥ በማድረግ፣ የሰውነት ክብደትን በማስተካከልና እንቅስቃሴ በማድረግ በበሽታው የመያዝ እድላችንን መቀነስ ይቻላል፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ በበሽታው የተያዝን እንደሆነም በህክምና ባለሙያ ከታዘዙልን መድኃኒቶች በተጨማሪ የሰውነት ክብደትን በማስተካከል፣ አዘውትሮ የሰውነት እንቅስቃሴ በማድረግ፣ ትንባሆ እና አልኮል ነክ ነገሮችን ባለመጠቀም እንዲሁም እንደ መጀመሪያው ባለታሪካችን የስኳር መጠናቸው ከፍ ያሉ ምግቦችን በመቀነስና ጤናማ አመጋገብ በማዘውተር በሽታው ከሚያመጣብን አስከፊ ጉዳቶች ራስን መከላከል ይቻላል፡፡
References
https://www.who.int/health-topics/diabetes
https://www.cdc.gov/diabetes/basics/diabetes.html
https://www.cdc.gov/diabetes/basics/risk-factors.html
https://www.cdc.gov/diabetes/basics/symptoms.html
https://www.cdc.gov/diabetes/basics/what-is-type-1-diabetes.html
https://www.cdc.gov/diabetes/prevent-type-2/index.html
ይህ ፅሁፍ በዶ/ር ቃልኪዳን አላቸው (የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት/ኢንዶክሪኖሎጂስት) እና የጤና ወግ ኤዲተሮች የተገመገመ ነው።