ዶ/ር ትንሳኤ አለማየሁ ; የህፃናት ህክምና ስፔሻሊስት እና የህፃናት ተላላፊ በሽታዎች ህክምና ሰብ-ስፔሻሊስት
ከቀናት በፊት የተላለፈ “ቢ.ሲ.ጂ. የተባለው የቲቢ ክትባትን መውሰድ ከኮቪድ19 በሽታ ይከላከላል” የሚል መረጃን የሰማ ጓደኛዬ ልጁ ሲወለድ ባጋጣሚ ክትባቱን ባለመውሰዱ ተጋላጭ ይሆን የሚል ጥያቄ ያነሳል:: ከጥያቄው ተነስቼ ስለ ክትባቱ ተፈጥሮ በአጭሩ ላስረዳ እሞክራለሁ::
በላይኛው ክንዳችን ልክ እንደተወለድን የምንወስደው የቲቢ ክትባት (ቢ.ሲ.ጂ.) ከ99 አመት በፊት (እ.ኤ.አ. 1921) የተገኘ ነባር ክትባት ነው:: ይህን የቲቢ ክትባት ባብዛኛው በምእራብ አውሮፓ እና ሰሜን አሜሪካ ከሚገኙ 29 ሀገራት ውጪ በመላው አለም በሙሉ ወይም በከፊል የሚሰጥ የቲቢ ህመምን በአማካይ በግማሽ (50%) የሚቀንስ መከላከያ ነው:: ኢትዮጵያን ጨምሮ በየአመቱ ከ 100 ሚልዮን በላይ ህፃናት ክትባቱን ይወስዳሉ::
የቲቢ ክትባት ስራውን የሚሰራው አቅሙ የተዳከመን የቲቢ ባክቴርያን ለሰውነታችን በማስተዋወቅ ከዛም የበሽታ የመከላከል መዋቅራችን ደካማ ጠላት ገጥሞ አሸንፎ በሙሉ አቅም ለሚያጠቃው የቲቢ ባክቴርያ ዝግጁ ማድረግ ነው:: ኮቪድ19 ወረርሽኝ ከመነሳቱ በፊት ኢንዶኔዥያ፣ ስፔን እና ጊኒ ቢሳው ባሉ ሀገራት የተሰሩ ጥናቶች እንደሚያሳዩን የቲቢ ክትባት የቲቢ ህመምን ለመከላከል ሰውነትን ከማዘጋጀት በተጨማሪ ሌሎች የመተንፈሻ አካላት ተላላፊ ህመሞች የመከላከል አቅምን በሁሉም እድሜ ባሉ ሰዎች ላይ (አረጋውያንን ጨምሮ) ከፍ ያደርጋል:: ህፃናትም በተለያዩ የመተንፈሻ አካላት የቫይረስ እና የባክቴርያ በሽታዎች የመያዝ እድላቸውን በ40% ይቀንሳል::
እስካሁን ባለ እውቀት የቲቢ ክትባት ከኮቪድ19 በሽታ እንደሚጠብቅ መላምት እንጂ መረጃ የለም:: የቲቢ ክትባት (ቢ.ሲ.ጂ.) ውጤታማነት ጥያቄ ውስጥ የሚከቱ ሌሎች እውነታዎችም አሉ:: ክትባቱ ህፃናት ልክ እንደተወለዱ ከተሰጠ በኃላ በአማካይ ለ15 አመት ብቻ መከላከያ የሚሰጥ ነው:: ይህንንም ጥቅሙን ከላይ እንደጠቀስኩት 50% ለሚሆኑት ተከታቢዎች ብቻ ይሰጣል:: በክትባት አለም 50% የመከላከል አቅም ከሌሎች ክትባቶች አንፃር አናሳ ነው:: አብዛኞቹ በኢትዮጵያ ለህፃናት የሚሰጡ ክትባቶች ከ80% እስከ 95% የመከላከል ስራን ለተወሰኑ አመታት ይሰራሉ:: ስለዚህም የራሱ የመከላከል አቅም ሳይሆን እንዴት ከኮቪድ19 ቫይረስ ይጠብቃል የሚለው ተገቢ ጥያቄ ነው::
በቲቢ ክትባት ላይ የሚሰሩ የዜና ዘገባዎች በቂ የህክምና ጥናት (Clinical trials) ያልተደረገባቸው ናቸው፡፡ ክፍተቱን ለመሙላት በኔዘርላንድስ እና በአውስትራልያ የተጀመሩ የቲቢ ክትባት ከኮቪድ19 በሽታ ጋር ያለውን ግንኙነት የሚያጠኑ ምርምሮች ከብዙ ወራት በኃላ ሲታተሙ ተጨማሪ መልሶች ይገኛሉ፡፡ ተመሳሳይ የመረጃ ክፍተት በሌሎች ጥቅማቸው ገና ባልተረጋገጡ መድሀኒቶችም ስለሚታይ በቂ መልስ ሳይኖር ለጥቅም እንዲውሉ አይመከርም፡፡
የጤና ወግ
በመረጃ የተመሰረተ ሕክምና ብቻ ።
………………………………………………………………………………………………………………………..
ይህ የጤና ወግ ድረ ገፅ ነው።
ስለ ጤንነታችሁ ማወቅ የምትፈልጉትን መረጃ የምታገኙበት ፣ በህክምና ባለሙያዎች የሚዘጋጅ የመረጃ ምንጭ ነው።
ሁልግዜም ከሀኪማችሁ ተማከሩ፣ ተጨማሪ መረጃ ከፈለጋችሁ የኛን ድረ ገፅ ጎብኙ።
በጥናት የተደገፈ መረጃ ብቻ እናቀርባለን።
የህክምና ባለሙያዎች ለህሙማኖቻችሁ የሚሆን የሚነበብ መረጃ ከፈለጋችሁ ይህን ግፅ ጠቁሟቸው። ህሙማኖቻችሁ እንዲያውቁት የምትፈልጉትን ነገር መረጃ ጠቅሳችሁ ፃፉልን፣ ስምችሁን ጠቅሰን እናወጣለን። የህክምና ተማሪዎች እንዲጽፉ እናበረታታለን።
በተጨማሪም በጤና ወግ ፖድካስት፣ በ ዩትዩብ ፣በ ትዊተር ፣ በ ፌስቡክ ፣ በቴሌግራም የተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ ገፆቻችን ታገኙናላችሁ