የአልኮል ሱሰኝነት – Alcohol Use Disorder
በኤልያስ ታፈሰ (የአ.አ.ዩ. የህክምና ኢንተርን) የተዘጋጀ
መግቢያ
ጤና ይስጥልኝ አንባቢያን ሆይ! ይህ መረጃ-አዘል ፅሁፍ በዋናነት ስለ አልኮል ሱሰኝነት ከምንነቱ እስከ ህክምናው ለማስገንዘብ ታልሞ የተፃፈ ሲሆን፤ ከዚህ በተጨማሪም ስለ አልኮል ጉዳቶች ያትታል፡፡ አደገኛ የአልኮል አጠቃቀም በአንድ ጊዜ ብዙ አልኮል መጠጣትን፣ ልማዳዊ የሆነ የአልኮል አጠቃቀምን፣ በእርግዝና ወቅትና በልጅነት አልኮልን መጠጣትን እንዲሁም የአልኮል ሱሰኝነትን ያጠቃልላል፡፡
አደገኛ በሆነ መጠን አልኮልን መጠጣት ምን አካላዊና ስነ-ልቦናዊ ጉዳት አለው?
ጤናማ ያልሆነ የአልኮል አጠቃቀም በበርካታ መንገዶች የሰውነታችንን አካላትና ስር ት ያናጋል፡፡ በዚህም ምክንያት የሚመጡ አካላዊ የሆኑ የጤና እክሎች እነሆ በምስሉ ተቀምጠዋል፡፡
አልኮል እንደ አካላችን ሁሉ አዕምሮአችን ላይም ከፍተኛ ተፅዕኖ እንዳለው ይታወቃል፡፡ ብዙ ሰዎችም ለዚሁ ተፅዕኖው ብለው አልኮልን ይጠቀማሉ፡፡ አልኮል ከጠጡ በኋላ የሚመጣው የባህሪና ስነ-ልቦናዊ ለውጥ የአልኮል ስካር (Alcohol intoxication) ይባላል፡፡ ስካር ጊዜያዊ የሆነ የደስታና የመረጋጋት ስሜት ቢፈጥርም፣ የተሳሰረ ንግግር፣ መፍዘዝ፣ የጡንቻ አለመቀናጀት፣ መወላገድ፣ የትኩረት ወይም የማስታወስ ችሎታ መረበሽ፣ ራስን መሳት ፣ኮማ እንዲሁም ሞትን ሊያመጣ ይችላል፡፡ ስካር በሚያመጠው የባህሪና የአስተሳሰብ ለውጥ ምክንያትም የትራፊክ አደጋዎች፣ ፀብና የአካል ጉዳት እንዲሁም ልቅ የሆነ የግብረ-ሥጋ ግንኙነትና ተያያዥ የአባላዘር በሽታዎች ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡
በተጨማሪም በተደጋጋሚ አልኮልን የሚጠቀም ሰው እንደ ጭንቀት፣ ድባቴ፣ የእንቅልፍ መረበሽ፣ የመርሳት በሽታና ራስን ለማጥፋት መነሳሳትን የመሳሰሉት ችግሮች የመጠቃት እድሉ ከሌሎች ሰዎች የላቀ ነው፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን፣ አልኮል ሱስ ማስያዝ ከሚችሉ ንጥረ-ነገሮች አንዱ በመሆኑ ሰዎች ያለ አልኮል አካላቸውና አዕምሮአቸው በአግባቡ እንዳይሰራ በማድረግ በአልኮል ላይ ጥገኝነትን (ወይም ሱሰኝነትን) ማምጣት ይችላል፡፡
አንድ የአልኮል ተጠቃሚ የአልኮል ሱሰኛ ነው የሚባለው መቼ ?
አንድ ሰው የአልኮል ሱኝነት ተጠቂ ነው የሚባለው በአምስተኛው የአእምሮ ሕመሞች የምርመራና የስታቲስቲካዊ መመሪያ (DSM-5) ውስጥ ውስጥ ቢያንስ ሁለቱን ሲያሟላ ነው፡፡ መስፈርቶቹም አልኮል በብዛት ወይም ከታሰበው በላይ ረዘም ላለ ጊዜ መውሰድ፣ የአልኮል አጠቃቀምን ለመቀነስ ፍላጎት ቢኖርም ለመቀነስ አለመቻል፣ አልኮልን ለማግኘት/ለመጠቀም ብዙ ጊዜ ማሳለፍ፣ አልኮልን ለመጠቀም ከፍተኛ ፍላጎት መኖር፣ በተደጋጋሚ አልኮልን መጠጣት በስራ፣ በትምህርት ቤት ወይም በቤት ውስጥ ያሉ ሀላፊነቶችን አለመወጣትን ማስከተሉ፣ በአልኮል ተጽዕኖ ስር ሆነው ሳሉ የተከሰቱ ማህበራዊ ወይም ግለሰባዊ ችግሮች ቢኖሩም መጠጣትን መቀጠል፣ በአልኮል መጠጥ ምክንያት ጠቃሚ ማህበራዊ፣ሙያዊ ወይም የመዝናኛ እንቅስቃሴዎች መቀነስ፣ ለአካል አደገኛ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ በተደጋጋሚ አልኮልን መጠቀም. (ለምሳሌ መኪና የሚነዱ ቢሆንም መጠጣት)፣ በአልኮል ምክንያት ሊከሰት የሚችል የአካል ወይም የስነ-ልቦና ችግር እንዳለ ቢያውቁም መጠጣትን መቀጠል፣ ስካርን ለማግኘት ከፍተኛ መጠን ያለው አልኮል ማስፈለግ እነዲሁም አልኮልን ሳይወስዱ ሲቀሩ የጤና መታወክ መከሰት (ሰውነት አልኮልን በመልመዱ የተነሳ)
አንድ የአልኮል ሱሰሰኝነት ያለበት ሰው እንዴት ከሱሱ መላቀቅ ይችላል?
ከአልኮል ሱስ መላቀቅ የተለያዩ ሂደቶች ያሉት ሲሆን በመጀመሪያ አንድ የአልኮል ሱስ ያለበት ሰው ይህ ሱስ እነዳለበት መገንዘብና ሱሱን ለመተው መወሰን አለበት፡፡ ይህን መወሰንም በአብዛኛው ቀስ በቀስ የሚመጣና ጊዜ የሚፈጅ ሂደት ነው፡፡
አንድ በአልኮል ሱስ የተጠቃ ግለሰብ ሱሱን ለመተው ከቆረጠ በኋላ በአቅራባው ወደሚገኝ የአልኮል ሱስን ለማከም ወደተዘጋጀ የህክምና ተቋም በመሄድ ከጤና ባለሙያዎችጋር እንዲመካከር በእጅጉ ይመከራል፡፡ ይህም አስፈላጊ የሆነው ሠውነታችን አልኮልን ለረጅም ጊዜ ከለመደ በኋላ (በተለይም የከፋ ሱሰኝኘት ያለበት ሰው ላይ) የጤና ባለሙያዎች ባልተሳተፉበት ሁኔታ አልኮልን መጠጣት ማቆም እንደ ጭንቀት፣ እንቅልፍ ማጣት፣ መንቀጥቀጥ፣ ማላብ፣ የልብ ምት መጨመር፣ ራስ ምታት፣ ቅዠትና ግራ መጋባትን የመሳሰሉ የጤና መታወክ ምልክቶች ሊያመጣ ስለሚችል ነው፡፡ ከሱስ የመላቀቁ ሂደት የጤና ባለሙዎች የተሳተፉበት ከሆነ ግን እነዚህ ምልክቶች እንዳይመጡ ለማድረግ የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰድ ይቻላል (ለምሳሌ ምልክቶቹን የሚቀንሱ መድሀኒቶችን ለታካሚው በመስጠት)፡፡
የአልኮል ሱሰኝነትን ለማከም ተብለው የተዘጋጁ የህክምና ክፍሎች በተለያዩ የግልም ሆነ የመንግሰት የህክምና ተቋማት ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ በአዲስ አበባ ካሉ የመንግስት ተቋማት መካከል፣ አማኑኤል የአዕምሮ ህክምና ሆስፒታል፣ ዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል፣ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል እና የካቲት 12 ሆስፒታል ለአልኮልም ሆነ ለሌሎች የሱስ አይነቶች ህክምናን ይሰጣሉ፡፡ ከአዲስ አበባ ውጪ ደግሞ ገፈርሳ የእእምሮ ጤናና ማገገሚያ ማዕከል ይህንን ህክምና ይሰጣል፡፡ ከግል ተቋማት ደግሞ አዲስ ሕይወት የዕፅና የአልኮል ሱሰኝነት ማገገሚያ ማዕከል ተመሳሳይ ህክምና ይሰጣል፡፡
ዋቢ
- Clinical practice. Unhealthy alcohol use – PubMed [Internet]. [cited 2022 Dec 12]. Available from: https://pubmed.ncbi.nlm.nih.gov/15703424/
- Alcohol. WHO | Regional Office for Africa. 2018. Available from: https://www.afro.who.int/health-topics/alcohol
- Sadock BJ, Sadock VA, Ruiz P. Kaplan & Sadock’s comprehensive textbook of psychiatry. 10th ed. Philadelphia: Wolters Kluwer; 2017.
- American Psychiatric Association. Diagnostic and statistical manual of mental disorders. 5th ed. Arlington, VA: American Psychiatric Association; 2013.
- Edelman EJ, Fiellin DA. Alcohol Use. Annals of Internal Medicine. 2016 Jan 5;164(1):ITC1.
- Bouzyk-Szutkiewicz J, Waszkiewicz N, Szulc A. [Alcohol and psychiatric disorders]. Polski Merkuriusz Lekarski: Organ Polskiego Towarzystwa Lekarskiego [Internet]. 2012 Sep 1 [cited 2022 Dec 12];33(195):176–81. Available from: https://pubmed.ncbi.nlm.nih.gov/23157139/