በአያና አየለ (በጅማ ዩኒቨርሲቲ ህ/ጤ/ሳ/ኮ የህክምና ተማሪ-PC 1)
አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ፡ ስንቶቻችሁ በአዕምሮ ህመም ተሰቃይታችኋል ወይንም በአዕምሮ ህመም የሚሰቃይ ሰው ታውቁ ይሆን? እኔ እንደምገምተው ከሆነ ሁላችንም በአእምሮ ህመም ውስጥ ያለን ወይንም በዚህ ህመም ምክንያት የሚቸግር አንድን ሰው እናውቃለን።
ይህን ይህል ለመግቢያ አንዲሆን ከፃፍኩ አሁን ደግሞ የአእምሮ ህመም ምን ማለት አንደሆነ ላብራራው።
የአእምሮ ህመም የሚባለው በአብዛኛው ጊዜ የሚታወቁት ሁኔታዎች እንደ ጭንቀት ፣ድባቴ ፣ “ስኪዞፍሬኒያ”፣ “ባይፖላር” ወዘተ እንዲሁም የአስተሳሰብ መታወክ አና የአልኮልና የተለያዩ መድሃኒቶች ሱሰኝነት ያጠቃልላል። እነዚህ አሁን የተዘረዘሩት ህመሞች የሚጎዱት ተመሳሳይ የአእምሮ ክፍልን ነው። በተለያየ ደረጃ እና መጠን የአእምሮ የማሰብ፣ የማሰላሰል፣ የመገንዘብ እና ስሜትን የመግዛት ስራውን በትክክል እንዳይሰራ ያደርጋሉ። ይህ የቀን ተቀን ኑሯችንን የሚያውክ ችግር ነው።
የአለም ጤና ድርጅት እንደዳስቀመጠው 20% የአለም ህዝብ በህይወት ዘመኑ አንድ ጊዜ በአእምሮ ህመም አና ተያያዥ ጉዳዮች ይሰቃያል ይላል። ይህም ማለት ከ5 ሰዎች አንዱ ማለት ነው። ስለዚህ ሒሳቡን ብናሰላው እያንዳንዱ ሰው በአእምሮ ህመም የሚቸገር አንድን ሰው ሊያውቅ ይችላል ማለት ነው። በጥቅሉ ይህን ያህል ብዛት ያለው ሰው በአለም ዙሪያ በዚህ በሽታ ከተጠቃ በዚህ በሽታ ዙሪያ ብዙ ጥናት፣ ምርምር አና ጠለቅ ያለ ግንዛቤ መፈጠር ይኖርበታል ማለት ነው። ግን አሁን መሬት ላይ በተግባር የሚታየው በዚህ በሽታ ዙሪያ ብዙ ምርምሮች አና ተግባሮች እንደ በሽታው ክብደት፣ መጠን እና አስከፊነት እንዳልተሰሩ ነው።
የአእምሮ ህመም መገለል አና ያላግባብ ፍረጃ ያጠቃዋል። መገለል ማለት ክብር አለመስጠት፣ መናቅ፣ ማዋረድ፣ ማሸማቀቅ አና የመሳሰሉት ናቸው። ግን ለምንድነው የአእምሮ ህመምተኞች ለመገለል እና ያላግባብ ፍርጃ የሚጋለጡት?
በአእምሮ ህሙማን ላይ ያለውን መገለልና ትክክል ያልሆነ አመለካከት ለማሳየት አንድ ምሳሌ እንውሰድ።
ለምሳሌ፦ አንተ ወይንም አንቺ ለአለቃህ/ሽ 50ኛ ዓመት የልደት በአል መልካም ምኞታችሁን እንድትገልፁ እና ንግግር እንድታደርጉ በአክብሮት ተጠራችሁ እንበል ነገር ግን በልደት በአሉ እለት ታመማችሁ አና ቀጠሮውን መሰረዝ እንዳለባችሁ ተረዳችሁ። ስለዚህ ቀጠሮውን ለመሰረዝ አንዴት ብትሉ ትመርጣላችሁ? ይቅርታ ቀጠሮውን የሰረዝኩት እራስን እስከማጥፋት የሚያደርስ ክፉ ድብርት (ድባቴ) ይዞኝ ነው ወይንስ እግሬን በጣም ስላመመኝ መራመድና መቆም ከብዶኝ ነው ያልመጣሁት ትላላችሁ። የመጀመሪያውን ከሁለተኛው አስበልጣችሁ ከመረጣችሁ አትጠራጠሩ አናንተ ለመገለል እና አግባብ ላልሆነ ፍረጃ ትጋለጣላችሁ።
ዶክተር ጄኤፈሪ ሊበርማን ” አሁን እኔ በየቀኑ መገለል ያጋጥመኛል እንደ አንድ የአእምሮ ሀኪም፡ ይህ እራሴን የሰጠሁለት የህክምና ስፔሻሊቲ ሙያ ከሁሉም የህክምና ስፔሻሊቲዎች በጣም የተዋረደ እና ትንሽ ቦታ የሚሰጠው ሙያ ነው።”
እስቲ የአእምሮ ህመምን አንደ ልብ ህመም አርገን እንየው እና ከዚያም ምልክቶችን ለምሳሌ ጭንቀትን እንደ ደረት ህመም፣ “አንዛይቲን” እንደ ትንፍሽ መቆራረጥ ወይንም በቀላሉ ለመተንፈስ መቸገር እንዲሁም “ሳይኮሲስን” እንደ የልብ ምት መጨመር ብናየው የመጀመሪያዎቹ ህመምዎች የሚመነጩት ከአእምሮአችን ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከልብ ነው ነገር ግን አእምሮአችን ከየትኛውም አካላታችን በላይ በጣም የተወሳሰበ ነው። ልብ በመሠረታዊነት ብዙ የደም ስሮች እና 4 የደም መቀበያ ክፍሎች ያሉት 2ቢሊዮን መስል ሴሎች ያሉት የደም መርጪያ አካል ነው። በአንፃሩ ደግሞ አእምሮ 3 ፓውንድ የሚመዝን ከ100ቢሊዮን በላይ ኒውሮኖች የተገነባ እና 30 ትሪሊዮን በላይ ትስስሮች ያሉት ከመሰረታዊ እና ዋና ከሆነው ከአተነፋፈስ፣ የሰውነት ሙቀትን መቆጣጠር፣ አስከ የተቀናጀ እንቅስቃሴ መፍጠር እንዲሁም ማንነትና ባህሪን የሚያላብስ ነው። አእምሮ እራሳችንን እንድናውቅ አና አንድንነቃ እንዲሁም አዲስ ፈጠራ አንድንሰራ ትልቅ ሚና አለው። የአእምሮን ስራ በትክክል ለይቶ ለመረዳት እና ለማወቅ ከባህሪ እና ማንነት ጋር ያለውን ትስስር ለመረዳት በጣም ብዙ ጊዜ ይወሰዳል።
አሁን መገለልና አድሎ ለአእምሮ ህመም ብቻ የተሰጠ አይደለም። በሰው ልጆች ታራክ ውስጥ ብዙ በሽታዎች ታይተዋል እንደ ቲቢ፣ የስጋ ደዌ ፣ ካንሰር፣ እንዲሁም እስከ አሁን መድሀኒት ያልተገኘለት ኤችአይቪ ተጠቃሽ ናቸው።
ኤችአይቪ ኤድስ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲከሰት ብዙ ሰው ሞተ፡ የሟቾች ቁጥርም በብዙ በእጥፍ እየጨመረ ሄደ ። ነገር ግን ምክንያቱ በትክክል አይታወቅም ነበር። ብዙ ምርምሮች እና ጥናቶች ከተደረጉ በኃላ ምን እንደሆነ በምን መንገድ እንደሚተላለፍ ታወቀ። ከብዙ ጥረት በኃላም ኤችአይቪ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍበት መንገዶች በግልጽ ተለይተው ወጡ አንዳንድ ክትባቶችም ተገኙ ይህ ሁሉ ከሆነም በኋላም ህዝብ ግን በኤችአይቪ የተያዙትን ከማግለል አልተቆጠበም። ኤችአይቪ ኤድስ ታማሚዎችን ማግለል ምግብ ለይቶ ለብቻቸው መስጠት፣ ከነርሱ ጋር አለማውራት፣ አለመጫወት አና የመሳሰሉት። አሁን ግን ከብዙ ግንዛቤ መፈጠር በኃላ ህዝቡ ስለ ኤችአይቪ አና ስለ ኤችአይቪ ታማሚዎች ያለው አመለካከት በተወሰነ ደረጃ ተለውጧል። የኤችአይቪኤድስን መገለል እና ያለአግባብ ፍረጃን ከአእምሮ ህመም ጋር ስናስተያየው ብዙ የሚያመሳስሉት ነገሮች አሉ። ይህም ማለት መንግስት ትኩረት ቢሰጠው አና በጀት ተመድቦ ቢሰራበት ብዙ ለውጦች ሊመጡ ይችላሉ። ነገር ግን ለአእምሮ ጤና የተሰጠው ትኩረት በጣም አናሳ ነው። ብዙ ተጨማሪ ነገሮችን ከ ምስል እና ከአሃዝ ጋር አያይዤ ባሰፍር ደስ ባለኝ ነገር ግን ይህን ፅሁፍ የፃፍኩት ከድባቴ አና መሰል የአእምሮ ህመም ጋር እየታገልኩ ነው።
አሁንም ትኩረት ለአእምሮ ጤና
ያለ አእምሮ ጤና ጤና የለም!
ይህ ፅሁፍ በዶ/ር ሄርሞን አማረ (የስነ አዕምሮ ህክምና ስፔሻሊስት) እና የጤና ወግ ኤዲተሮች የተገመገመ ነው።