Written by: Robel Habtamu Ababiya M.D, General Practitioner, Lecturer

Reviewed by: Fitsum T. Hailemariam M.D, Assistant Professor of Medicine, Division of Nephrology, Hypertension and Transplantation

 

በኢትዮጵያ የኩላሊት ህመም  ከፍተኛ የጤና ተግዳሮት ሲሆን ብዙ ግለሰቦችን ያጠቃል። በተጨማሪም የጤና ስርዓቱ ላይ ከባድ ሸክም እየፈጠረ ነው። በመጨረሻ ደረጃ የኩላሊት በሽታ ለሚሰቃዩ የኩላሊት ንቅለ-ተከላ  በጣም ውጤታማ የሕክምና አማራጭ ነው። የኩላሊት እጥበት የኩላሊትን ተግባራት በመፈጸም ህይወትን ማቆየት ቢችልም እንደኩላሊት ንቅለ ተከላ ጥሩ ኑሮ ወይም ረጅም የህይወት ዘመን አይሰጥም። የኩላሊት እጥበት  ብዙ ጊዜ ሆስፒታል መመላለስን ስለሚስከስት ለታካሚዎች አካላዊ እና ስሜታዊ ጉዳት ያመጣል። በአንፃሩ የተሳካ የኩላሊት ንቅለ ተከላ የኩላሊት መደበኛ ስራን ወደነበረበት እንዲመለስ በማድረግ ታካሚዎች ጤናማ እና ጥሩ ህይወት እንዲመሩ ያስችላቸዋል።

በህይወት እያሉ ኩላሊት መለገስ የተቀባዩን ህይወት በእጅጉ ከማሻሻል በተጨማሪ ህይወቱን ያድኑታል ። ይህ ጽሁፍ የኩላሊት ለጋሽ የመሆን ሂደትን ከመጀመሪያ ምርመራ ጀምሮ እስከ ድህረ ልገሳ ድረስ ለማብራራት ያለመ ነው። ይህንን  በማቅረብ፣ ብዙ ግለሰቦች በህይወት እያሉ የኩላሊት ለጋሾች በመሆን ሊያመጡ የሚችሉትን ከፍተኛ ተጽዕኖ እንዲያስቡ ያበረታታል።

 

          ኩላሊት መለገስ ያለው ጠቀሜታ

በህይወት እያሉ ኩላሊት ለመለገስ መምረጥ በርካታ ጥቅሞችን ይሰጣል፡-

  • ለተቀባዩ የተሻለ ጤና: በህይወት ካሉ ለጋሾች የሚመጡ ኩላሊቶች ብዙ ጊዜ ይቆያሉ እና ከተተከሉ በኋላ ወዲያውኑ ሥራ ይጀምራሉ።
  • የጥበቃ ጊዜ መቀነስ፡ በኢትዮጵያ የኩላሊት ንቅለ ተከላ የሚከናወነው በህይወት ባሉ ለጋሾች ለምሳሌ በቤተሰብ አባላት መካከል ነው። ለሚወዱት ሰው ኩላሊትን መለገስ በህይወት የሚቆይበትን ጊዜ በእጅጉ ያጨምራል።
  • የተሻለ ህይወት መምራት፡ ከለጋሽ ኩላሊትን መቀበል ተቀባዩ ኩላሊት እጥበትን እንዲያቆም እና የበፊት አቅማቸውን መልሰው እንዲያገኙ ያስችለዋል፣ ይህም እጅግ የተሻለ ህይወት እንዲኖራቸው ያደርጋል።
  • ህይወት ማዳን ኩላሊት በመለገስ የአንድን ሰው ህይወት ማዳን ያስችሎታል።

 

የኩላሊት ልገሳ ምንን ያካትታል?

ተስማሚ ለጋሽ መሆንዎን ለማረጋገጥ ከምርመራ ጀምሮ  በርካታ ደረጃዎችን ያካትታል። እነዚህም፡-

 

ደረጃ 1፡ የመጀመሪያ ምርመራ

የመጀመሪያ እርምጃዎ የንቅለ ተከላ ማእከልን ማነጋገር ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ጊዜ ይህ የሚሆነው የቤተሰብ አባል ወይም የሚወዱት ሰው ኩላሊት ሲፈልግ ነው። የንቅለ ተከላ ቡድኑ እርስዎ ለመለገስ ጤናማ መሆንዎን ለማረጋገጥ የህክምና ታሪክዎን ወስዶ አንዳንድ መሰረታዊ ምርመራዎችን ያደርጋል።

ደረጃ 2፡ የህክምና ምርመራዎች

የመጀመርያው ምርመራ እርስዎ ለኩላሊት ልገሳ ብቁ ሊሆኑ እንደሚችሉ የሚያመለክት ከሆነ፣ የእርስዎን ጤና እና ከተቀባዩ ጋር ያለውን ተስማሚነት ለማረጋገጥ ተከታታይ ተጨማሪ ዝርዝር ምርመራዎችን ያደርጋሉ።

የደም ምርመራዎች

የደም አይነትዎን እና ሌሎች ምርመራን በመጠቀም ከተቀባዩ ጋር ያለውን ተስማሚነት ለመወሰን ይረዳል።

የኩላሊት ተግባር ምርመራዎች

የኩላሊቶቻችሁን ጤና እና ተግባር ለመገምገም ይረዳል። ውጤቶቹም ኩላሊቶችዎ ለመለገስ በደንብ እየሰሩ መሆናቸውን ለማወቅ ይረዳሉ።

የምስል ምርመራዎች

የምስል ምርመራዎች የኩላሊቶቻችሁን አወቃቀሮች ለማየት ያስችላል።  እንደ አልትራሳውንድ፣ ሲቲ ስካን ወይም ኤምአርአይ የመሳሰሉ ምርመራዎች የኩላሊትዎን ዝርዝር ምስሎች ለማግኘት ይጠቅማሉ። እነዚህ ምስሎች ዶክተሮች የኩላሊቶቻችሁን መጠን፣ ቅርፅ እና ቦታ እንዲገመግሙ ያግዛሉ፤ እና በልገሳ ሂደት ላይ ተጽእኖ ሊያሳድሩ የሚችሉ ነገሮችን መኖር አለመኖራቸውን ይፈትሹ።

አጠቃላይ የጤና ምርመራ

አጠቃላይ የጤና ምርመራ ጤናዎን ለመገምገም እና ቀዶ ጥገናን ሊያወሳስቡ የሚችሉ ማናቸውንም ሁኔታዎችን ለመለየት ያግዛል። ይህም እንደ የደም ግፊት፣ የስኳር በሽታ፣ የልብ ሕመም እና ሌሎች የጤና ጉዳዮችን መመርመርን ያካትታል። የአካል ምርመራ፣ የህክምና ታሪክ ግምገማ እና እንደኢሲጂ፣ ሰትረስ ቴስት ያሉ ተጨማሪ ምርመራዎችን ሊያካትት ይችላል። ግቡ ጤነኛ መሆንዎን በማረጋገጥ ቀዶ ጥገና ለማድረግ እና ያለ ምንም ችግር እንደሚያገግሙ ለማረጋገጥ ነው።

ደረጃ 3፡ ለጋሽ ለመሆን ፍቃድ ማግኘት

ሁሉም አስፈላጊ ምርመራዎች ከተጠናቀቁ እና ከተገመገሙ በኋላ፡ የንቅለ ተከላ ቡድኑ እርስዎ ተስማሚ ለጋሽ መሆንዎን ይወስናል። ይህ እርምጃ ለጋሹም ሆነ ተቀባዩ ለሂደቱ ጥሩ ጤንነት ላይ መሆናቸውን ስለሚያረጋግጥ ወሳኝ ነው። በተጨማሪም የንቅለ ተከላ ቡድኑ የልገሳ ሂደቱን አጠቃላይ መግለጫ ይሰጣል። የቀዶ ጥገናውን ሂደት፣ የማገገም ግዜውን እና ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን ሁሉ ይብራራሉ። ቡድኑ እርስዎ ሊኖሩዎት የሚችሉትን ማንኛውንም ጥያቄዎች ወይም ስጋቶች ይመልስልዎታል።

ከዚህም በተጨማሪ የንቅለ ተከላ ቡድኑ የበጎ ፈቃድ ልገሳን አስፈላጊነት ያብራራል። ያዛ ያለምንም ውጫዊ ጫና እና ማስገደድ ይህንን ውሳኔ በነጻነት እየወሰኑ መሆኑን ያረጋግጣሉ። ቡድኑ የአኗኗር ለውጦችን ወይም አስፈላጊ የሆኑትን የህክምና ክትትልን ጨምሮ ይወያያል። የዚህ ጥልቅ ግምገማ እና ውይይት ዓላማ ለጋሽ ለመሆን በወሰኑት ውሳኔ ሙሉ በሙሉ ዝግጁ መሆንዎን እና በራስ መተማመንዎን ለማረጋገጥ ነው።

የኩላሊት ለጋሽ የመሆን ችግሮች

ኩላሊትን መለገስ ልክ እንደ ማንኛውም የቀዶ ጥገና ከተወሰኑ ችግሮች ጋር አብሮ ይመጣል። ከአንድ ኩላሊት ጋር መኖር በአጠቃላይ ይሄ ነው የሚባል አደጋዎች ባይኖሩትም፣ ሊከሰቱ የሚችሉ አንድአንድ ችግሮች የሚከተሉትን ያካትታሉ፡-

  • የቀዶ ጥገና ችግሮች፡ ከቀዶ ጥገና በኋላ ህመም፣ ኢንፌክሽን ወይም ደም መፍሰስ አንአንዴ ሊከሰት ይችላል።
  • የኩላሊት ተግባር ለውጦች፡ የቀረው ኩላሊት የተለገሰውን ኩላሊት ስራ ለማካካስ መጠኑ የተወሰነ ይጨምራል።
  • የረዥም ጊዜ ችግሮች፡ አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በቀጠይ ህይወታቸው ለደም ግፊት ወይም ለኩላሊት ህመም የመጋለጥ እድላቸው በመጠኑ ይጨምራል፤ ምንም እንኳን አብዛኛዎቹ ለጋሾች ረጅም እና ጤናማ ህይወት ቢቀጥሉም።

የንቅለ ተከላ ቡድኑ እነዚህን ችግሮች መከሰት አለመከሳቸውን በቀጠይ ይከታተላል።

ከኩላሊት ልገሳ በኋላ ምን ይደረጋል?

ከቀዶ ጥገና በኋላ፡ አብዛኛዎቹ የኩላሊት ለጋሾች በሆስፒታል ውስጥ ከ2-5 ቀናት ውስጥ ይቆያሉ። ሙሉ ለሙሉ ለማገገም ከ6-8 ሳምንታት ሊወስድ ይችላል ፤በዚህ ጊዜ ከባድ ማንሳት እና ከባድ እንቅስቃሴዎችን ባያደርጉ ይመከራል። ሐኪምዎ ህመሞን ለመቀነስ እና ወደ መደበኛ ህይወት እንዴት እንደሚመለሱ ምክር ይሰጣል።

ለጋሾች በአንድ ኩላሊት ብቻ ጤናማ ህይወት መኖር ይችላሉ። ከቀዶ ጥገናው በኋላ የኩላሊት ስራዎን እና አጠቃላይ ጤናዎን ለመከታተል ከጤና ባለሞያዎ ጋር በቅርበት ክትትል ማድረግ አስፈላጊ ነው። ከልገሱ በኋላ ጤናዎን ለመጠበቅ የተመጣጠነ አመጋገብ፣ መደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እና ውሀ በደንብ መጠጣት አስፈላጊ ናቸው።

 

ከኩላሊት ልገሳ በኋላ የሚደረግ የህክምና ክትትል

 

  • 2 ሳምንታት ከቀዶ ጥገና በኋላ፡ በንቅለ ተከላ ማእከል በአካል ተገኝቶ ተገቢውን ህክምና እና አጠቃላይ ጤናዎን ለመከታተል የሚደረግ ነው። በግዜው የደም እና/ወይም የሽንት ናሙናዎች ሊወሰዱ ይችላሉ።
  • 3 ወር እና 6 ወር ከቀዶ ጥገና በኋላ፡ የኩላሊት ተግባርን በደም እና በሽንት ምርመራዎች ለመከታተል ይደረጋል።
  • በየ 6 ወሩ 2 ዓመታት የሚደረግ ከቀዶ ጥገና 1 አመት እና 2 አመት በኋላ በድጋሚ የኩላሊት ስራን በደም እና በሽንት ምርመራዎች ለመከታተል ይደረጋል።
  • አመታዊ ምርመራዎች እድሜ ልክ የሚደረጉ፡ ከ 2 አመት በኋላ፡ የኩላሊት ስራን፣ የደም ግፊትን እና አጠቃላይ ጤናን ለመከታተል የሚደረግ ነው።

 

 ከለገሱ በኋላ ጤናዎን መጠበቅ

  1. የሰውነት ክብደትን መቆጣመር፡

የተመጣጠነ ምግብ መመገብ ማለትም በፍራፍሬ፣ አትክልት እና ፕሮቲኖች የበለፀገ ምግብ መመገብ ያስፈልጋል።

በተጨማሪም ከፍተኛ ስብ እና የስኳር ይዘት ያላቸውን ምግቦች ያስወግዱ።

  1. መደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ

አካላዊ እንቅስቃሴ፡ እንደ መራመድ፣ መዋኘት ወይም ብስክሌት መንዳት ባሉ መደበኛ የአካል እንቅስቃሴዎች ውስጥ ይሳተፉ። በሳምንት ቢያንስ 150 ደቂቃ መጠነኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያድርጉ። ከባድ  እቃ ማንሳት ግን የለቦትም።

  1. ኩላሊት የሚጎዱ መድሃኒቶችን ያስወግዱ

ማንኛውንም አዲስ መድሃኒት ከመውሰድዎ በፊት ሁል ጊዜ የጤና ባለሞያዎን ያማክሩ፤ይህም ያለ መዳኒት ማዘዣ የሚገዙትንም ይጨምራል።

  1. ውሀ በደንብ መጠጣት

ኩላሊቶቻችሁ በተገቢው መልኩ እንዲሰሩ ለማገዝ በቀን ቢያንስ 8 ብርጭቆ ውሃ ይጠጡ።

  1. የደም ግፊቶን ይከታተሉ፡

ከፍተኛ የደም ግፊት የቀረውን ኩላሊትዎን ሊጎዳ ስለሚችል በየጊዜው በአቅራቢው ባለው የጤና ማእከል በመሄድ ይለኩ።

በኢትዮጵያ የኩላሊት ልገሳ

በኢትዮጵያ በቤተሰብ አባላት መካከል የሚደረግ የኩላሊት ንቅለ ተከላ በጣም የተስፋፋው የኩላሊት ልገሳ አይነት ነው። ይህ አሰራር በጠንካራ የቤተሰብ ትስስር እና ዘመዶቻቸውን ለመርዳት ባላቸው ፍላጎት ተነሳሽነት የሚደረግ ነው። ይሁን እንጂ በሀገሪቱ ውስጥ የንቅለ ተከላ አገልግሎት አቅርቦት በጣም ውስን ነው። በውጤቱም: ብዙ ታካሚዎች ወደ ውጭ አገር የሕክምና እርዳታ ለመፈለግ ይገደዳሉ፤ ብዙውን ጊዜ እንደ ህንድ ወይም ቱርክ ባሉ አገሮች አስፈላጊውን የቀዶ ጥገና ሕክምና ለማድረግ ይጓዛሉ። ይህ በታካሚዎች እና በቤተሰቦቻቸው ላይ ከፍተኛ የገንዘብ ጫና ያሳድራል።

በኢትዮጵያ ውስጥ የኩላሊት ለጋሽ በመሆን ለተቸገረ ሰው የህይወት አድን ስራ በመስራት ወሳኝ ሚና መጫወት ይችላሉ። ለመለገስ መወሰን ለታካሚዎች ወደ ውጭ አገር የመሄድ ጫናን በማቃለል ተጓዳኝ ወጪዎችን እና የሎጂስቲክስ ተግዳሮቶችን መቀነስ ያስችላል። ከዚህም በተጨማሪ የሀገር ውስጡን የንቅለ ተከላ አገልግሎት አዋጭነት እና አስፈላጊነት በማሳየት የጤናን ሥርዓት ለማጠናከር አስተዋፅኦ ያደርጋሉ። ይህ የልግስና ተግባር ህይወትን ማዳን ብቻ ሳይሆን የማህበረሰብን ቀጠይ የድጋፍ ስሜት ያጎለብታል፤ ሌሎች ኩላሊት መለገስን እንዲያስቡ ያደርጋል።

ለመለገስ ካሰቡ በምን ይጀምሩ?

 

የኩላሊት ለጋሽ ለመሆን እያሰቡ ከሆነ፣ የመጀመሪያው እርምጃ  የንቅለ ተከላ ማእከልን( እንደ ፓውሎስ ሆስፒታልን) ያነጋግሩ። እነዚህ ተቋማት ስለ ልገሳ ሂደት አጠቃላይ መረጃ የሚያቀርቡልዎ ልዩ ቡድኖች አሏቸው። እርስዎ ተስማሚ እጩ መሆንዎን ለማረጋገጥ እና ከመጀመሪያ ምክክር ጀምሮ እስከ ከልገሳ በኋላ ያሉትን ነገሮች እንዲመራዎት የሚያስችል ጥልቅ የህክምና ግምገማ ያካሂዳሉ። ከህክምና ቡድኑ ጋር ስለጤናዎ፣ ስለሚያስጨንቁዎት ማናቸውም ጉዳዮች፣ እና ሊኖሩ ስለሚችሉ ስጋቶች እና ጥቅሞች ከህክምና ቡድኑ ጋር ግልጽ እና ታማኝ ውይይት ማድረግ በጣም አስፈላጊ ነው። ይህ በውሳኔዎ ሙሉ መረጃ እና ምቾት እንዲኖርዎት ያስችላል።

ኩላሊትን መለገስ የተቀባዩን ህይወት በእጅጉ ያሻሽላል። ለመለገስ መምረጥ ለታመመ ሰው ተስፋ እና ሁለተኛ እድል ይሰጣል። በመጨረሻም ይህ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ተግባር የተቀባዩን ቤተሰብ እና ማህበረሰብ ላይ በጎ ተጽዕኖ ያሳድራል።