Tweet
ከስኳር ህመም እና ከ ደም ግፊት ቀጥሎ ለመጨረሻ ደረጃ የኩላሊት ህመም አልፎም ለ ዲያሊሲስ ከ ከሚያጋልጡ ምክንያቶች አንደኛው የትናንሾቹ የኩላሊት ማጣሪያዎች መቆጣት ወይም በእንግሊዘኛው (Glomerulonehritis) የምንለው በሽታ ነው። ምንጭ
በተለይ በልጆች ላይ እና በወጣትነት እድሜ የሚከሰት የኩላሊት ድክመት ከዚህ በሽታ ጋር ይያያዛል።
ኢትዮጲያ ውስጥ የተሰሩ ጥናቶች ባይኖሩም ወደ ሆስፒታል በአጣዳፊ የኩላሊት መድከም ህመም ከሚመጡት ውስጥ የኩላሊት ማጣሪያዎች መቆጣት ወይም (Glomerulonehritis) በብዛት ይታያል።
አጣዳፊ የኩላሊት ማጣርያዎች መቆጣት ህመሞች የሚታወቅ መንስኤ ሊኖራቸውም ላይኖራቸውም ይችላል፡፡ ይህ በሽታ ቀላል የቆዳና የጉሮሮ ህመምን ተከትሎ ሊመጣ ይችላል። ሌሎች እንደ ሄፓታይቲስ ያሉ የጉበት በሽታዎች ፣ የሰውነት የ በሽታ መከላከያ መንገዶች ስረአት መዛባት (Auto Immune disease like Lupus..) በተጨማሪ ለዚህ ህመም ሊዳርጉ ይችላሉ።
የኩላሊት ማጣርያዎች በሚቆጡ ሰአት ኩላሊቶቻችን መወገድ ያለባቸውን የሰውነት ቆሻሻዎችን ማጣራት ያቅታቸዋል፡፡ ህመሙ ሳይታከም ከቀጠለ ደግሞ ከናካቴው ስራቸውን ያቆማሉ፡፡
ሁለት አይነት የኩላሊት ማጣርያዎች መቆጣት ህመሞች አሉ – አጣዳፊ እና የሰነበተ የኩላሊት ማጣርያዎች መቆጣት ህመም ይባላሉ፡፡
የአጣዳፊ ህመም ሲጀምር የሚታዩ ምልክቶች ውስጥ የፊት ማበጥ ፣ ከሽንት ጋር ደም መቀላቀል (ወይም ቡናማ መምሰል) እና የሽንት መጠን መቀነስ ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በሳንባችን ውስጥ በሚጠራቀም መወገድ በነበረበት ፈሳሽ ምክንያት የትንፋሽ ማጠር እንዲሁም የደም ግፊት ሊታይ ይችላል፡፡ ህመሞቹ ሲጀምሩ ሳይውል ሳያድር መመርመር እና መታከም ያስፈልጋል፡፡
የሰነበተ የኩላሊት ማጣርያዎች መቆጣት ህመም ምንም ምልክት ሳያሳይ አመታት ቆየቶ የማጣራትን ችሎታ ሙሉ ለሙሉ ሊገታ ይችላል፡፡ የዚህ አይነት ህመም ከሽንት ጋር ደም ወይም ፕሮቲን መቀላቀል ፣ የደም ግፊት ፣ የቁርጭምጭሚት ወያም የፊት ማበጥ ፣ የደፈረሰ ሽንት እና በምሽት ቶሎ ቶሎ መሽናት ሊያመጣ ይችላል፡፡ አለፍ አለፍ እያለ ህመሙ በዘር ሊተላለፍ ይችላል፡፡ በዘር የተላለፈ የሰነበተ የኩላሊት ማጣርያዎች መቆጣት ህመም ያላቸው የተወሰኑ ወጣት ወንዶች የእይታ እና የመስማት ችግሮች ሊያሳዩ ይችላሉ፡፡ አብዛኞቹ መሰል ህመሞች ግን መንስኤያቸው በውል አይታወቅም፡፡
የኩላሊት ማጣርያዎች መቆጣት ወደ ሙሉ ስራ ማቆም ሲያመራ የምግብ ፍላጎት መዝጋት ፣ ማቅለሽለሽ ፣ ማስታወክ ፣ ድካም ፣ የአንቅልፍ ማጣት ፣ የቆዳ ድርቀት ወይም ማሳከክ እንዲሁም በምሽት የሚታይ የጡንቻ መሸማቀቅ ሊያመጣ ይችላል፡፡
የኩላሊት ማጣርያዎች መቆጣት ህመም መኖሩ እንዴት ሊረጋገጥ ይችላል ?
ሀኪምዎት የህመም ምልክቶችዎን እና በሽንት ውስጥ የሚታዩትን ፕሮቲን እና የቀይ ደም ሴሎች በመመርመር የትኛውን አይነት እና ደረጃ ላይ ያለ ህመም እንዳለዎት ሊታወቅ ይችላል፡፡ አንዳንዴም ከኩላሊትዎ ላይ በተለየ መርፌ ከሚወሰድ እና በማይክሮስኮፕ በሚመረመር ናሙና (Kidney Biopsy ) ለርስዎ የሚስማማ ህክምና ሊዘጋጅ ይችላል፡፡
የኩላሊት ማጣርያዎች መቆጣት ህመምን መከላከል ይቻላል ?
እስካሁን ባለው የህክምና እውቀት የግልን ንጽህና በመጠበቅ ፣ ጥንቃቄ በተሞላበት የግብረ-ስጋ ግንኙነት ፣ እና በደም ስር የሚሰጡን አደንዛዥ እጾች ባለመጠቀም በ ኤች – አይ – ቪ ፣ በሄፓታይቲስ ቫይረሶች ፣ በመሳሰሉት የቫይረስ ህመሞች የሚከሰቱት የኩላሊት ማጣርያዎች መቆጣት ህመሞችን መከላከል ይቻላል፡፡ የተቀሩትን አይነት ህመሞች ግን ምክንያታቸው ሳይታወቅ መከላከል አይቻልም፡፡ የሰነበተ የኩላሊት ማጣርያዎች መቆጣት ህመም ከተከሰተ በኋላ የጉዳት ፍጥነቱን ለመቀነስ የደም ግፊት ካለ መቆጣጠር እንዲሁም የፕሮቲን ይዘታቸው ከፍተኛ የሆኑ ምግቦችን መቀነስ ይረዳሉ፡፡
የኩላሊት ማጣርያዎች መቆጣት ህመምን እንዴት ማከም ይቻላል ?
ባንዳንድ ወቅቶች የአጣዳፊ የኩላሊት ማጣርያዎች መቆጣት ህመም ያለህክምና ሲድን ይታያል፡፡ አንዳንዴ ደግሞ መድሀኒቶችን መውሰድ ወይም በጊዜያዊነት ሰውነት ውስጥ የሚጠራቀውን ያልተጣራ ፈሳሽ ለማስወገድ እና የሚከተለውን የደም ግፊት ማስተካከል በዳያሊሲስ ማሽን መታገዝ ሊያስፈልግ ይችላል፡፡ ያለብዎት የኩላሊት ማጣርያዎች መቆጣት ህመም ከፍተኛ ከሆነ የበሽታ መከላከል አቅምን የመቀነስ የጎንዮሽ ጉዳት ያላቸውን መድሀኒቶች ሊታዘዝልዎት ይችላል፡፡ በተወሰኑ አጋጣሚዎች ደግሞ ፕላስማፌሬሲስ በሚባል ያልተጣሩ ቆሻሻዎች ከደም በሚያስወግድ ህክምና ሊጠቀሙ ይችላል፡፡
ለሰነበተ የኩላሊት ማጣርያዎች መቆጣት ህመም ቀጥተኛ ህክምና የለም፡፡ ሆኖም ከሀኪምዎ የሚከተሉትን ምክሮች ሊለገስዎት ይችላል፡፡
- የፕሮቲን ፣ የጨው እና የፖታሲየም ይዘታቸው ከፍተኛ የሆኑ ምግቦችን መቀነስ
- የደም ግፊት ካለ መቆጣጠር
- የሰውነት እብጠትን የሚቀንሱ መድሀኒቶች መውሰድ
- የካልሲየም እንክብሎችን መውሰድ
Source : The National Kidney Foundation