Prepared by: Eyoel  Ameha Sebsibe  (C2 medical student)

Reviewed and edited by: Dr. Seyfe Bekele Tilahun (Assistant Professor of Urology at Addis Ababa University, College of Health Sciences, Department of Surgery, urology Division)

የኩላሊት ጠጠር ምንድን ነው?

የኩላሊት ጠጠር በዓለም ዙሪያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያጠቃ ህመም ነው፡፡ በትክክል ካልተያዘና በጊዜ ህክምና ካልተደረገለት፡ ከባድ ህመም እና ውስብስብ ችግሮችን ሊያስከትል ይችላል፡፡ ይህ ጽሑፍ የኩላሊት ጠጠር መንስኤዎች እና ምልክቶችን በጥልቀት በመመርመር አጠቃላይ ግንዛቤን ለመስጠት ያለመ ነው፡፡

የኩላሊት ጠጠሮች ከሰውነታችን በሽንት መልክ እንዲወገዱ በኩላሊት የተጣሩ ማዕድናት፣ጨዎች እና ንጥረ ነገሮች መሟሟት ከሚቸሉበት መጠን በላይ ሲሆኑ የሚፈጠሩ ጠንካራ ክምችቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ጠጠሮች በመጠን እና ቅርፅ የተለያዩ ሲሆኑ ከትንንሽ የአሸዋ መጠን ከሚያክሉ እስከ የጎልፍ ኳስ የሚያህል መጠን ሊኖራቸው ይችላል፡፡ የኩላሊት ጠጠር በተለያዩ ዓይነቶች የሚከፋፈሉ ሲሆን እነዚህም ካልሲየም ኦክሳሌት (Calcium oxalate)፣ ካልሲየም ፎስፌት (Calcium phosphate)፣ ዩሪክ አሲድ (Uric acid)፣ ስትሩቫይት (Struvite) እና ሲስቲን (Cystine) ጠጠሮችን ያጠቃልላል፡

ከ10-15% የሚሆነው የአለም ህዝብ በህይወት ዘመናቸው በተወሰነ ጊዜ የኩላሊት ጠጠር እንደሚገጥማቸው ይገመታል፡፡ በ ጥቁር አንበሳ ሆሰፒታል የተሰራ ጥናት እንዳመለከተው ከ 2010 እስከ 2015 (እ.ኤ.አ) ለቀዶ ህክምና አልጋ ከያዙት ጠቅላላ ታኪሚዎች ውስጥ 12 በመቶ የሚሆኑት ለኩላሊት ጠጠር ህክምና የገቡ ናቸው፡፡  የኩላሊት ጠጠር ህመም በማህበረሰብ ጤና እና ኢኮኖሚ ላይ የሚያደርሰው ተፅእኖ ከፍተኛ ነው፡፡ የኩላሊት ጠጠርን ከመመርመር፣ ከህክምና እና ክትትል ጋር የተያያዙ የጤና አጠባበቅ ወጪዎች ከፍተኛ መሆናቸው ትልቅ የማህበረሰብ ጤና ጉዳይ ያደርገዋል፡፡ ከዚህም በላይ የኩላሊት ጠጠር በፍጥነት ካልታከመ እንደ የሽንት ቱቦ ኢንፌክሽን፣ የሽንት ፍሰት መዘጋት እና ሥር የሰደደ የኩላሊት በሽታ የመሳሰሉ ችግሮችን ሊያስከትል ይችላል፡፡

                                                         

 የኩላሊት ጠጠር መንስኤዎች ምንድን ናቸው?

የኩላሊት ጠጠር የሚፈጠረው የውሃ፣ ጨው፣ ማዕድናት እና ሌሎች በሽንት ውስጥ ያሉ ንጥረ ነገሮች ሚዛን ሲስተጓጎል ነው፡፡ ለዚህ አለመመጣጠን በርካታ ምክንያቶች አስተዋፅኦ የሚያደርጉ ሲሆን ቀጥለው የተዘረዘሩት ለኩላሊት ጠጠር መፈጠር ዋና ዋና ምክንያቶች ናቸው፡፡

  1. በቂ ፈሳሽ አለመውሰድ ፡ ማዕድናት በቀላሉ በሽንት ውስጥ እንዳይሟሙ እና እንዲደድሩ( ክሪስታላይዝ እንዲያደርጉ) እና ጠጠር እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡
  2. ሞቃታማ እና ደረቅ የአየር ንብረት ያላቸው አካባቢዎች ፡ በእነዚህ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ለ ኩላሊት ጠጠር ተጋላጭነታቸው ከፍተኛ ነው፡፡ በ ሀገራችን ኢትዮጵያ የ ድሬዳዋ፤ ጅጅጋ ፤ ሀረር፤ ሶማሌ እና አፋር አካባቢዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡
  3. የስራ ሁኔታ፡- የስራ አካባቢያቸው ለከፍተኛ ሙቀት ተጋላጭ የሚያደርጋቸው ሰዎች ለ ኩላሊት ጠጠር ህመም ተጋላጭነታቸው ከፍተኛ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል የ ምግብ ማብሰል ባለሙያዎች፤በ ማዕድን ቁፋሮ እና በ ብረታብረት ስራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
  4. ወንዶች ከሴቶች በበለጠ በብዛት ይጠቃሉ፡፡
  5. አመጋገብ፡-

የሚከተሉት አይነት ምግቦች ለ ኩላሊት ጠጠር አጋላጭ ናቸው

ሀ. የኦክሳሌት (oxalate) መጠናቸው ከፍተኛ የሆኑ ምግቦች፡ ለምሳሌ፡ ስፒናች፤ ለውዝ ፤ ቸኮሌት ፤ሻይ ፤ ድንች ፤ወዘተ፡፡

ለ. ከመጠን በላይ ጨው ያላቸው ምግቦች

ሐ. ከፍተኛ የፕሮቲን መጠን ያላቸው ምግቦች

መ. የሰው ሰራሽ ጣፋጭ መጠጦች ፡ ለምሳሌ የሶዳ መጠጦች (carbonated beverages)

በብዛት መውሰድ የጠጠር መፈጠር እድልን ይጨምራል፡፡

  1. ተደጋጋሚ የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን፡ በዋናነት ስትሩቫይት ለሚባለው የ ጠጠር አይነት መፈጠር ምክንያት ይሆናል፡፡
  2.  ጄኔቲክስ፡ አንዳንድ የኩላሊት መንስኤዎች በዘር የሚተላለፉ ናቸው፡፡
  3. ተጓዳኝ ህመሞች፡ እንደ ሃይፐርፓራታይሮዲዝም፤ ሪህ እና  የአንጀት በሽታዎች ያሉ ህመሞች የኩላሊት ጠጠር የመፈጠር እድልን ይጨምራሉ፡፡
  4. ከልክ ለፈ ውፍረት (obesity): ከፍ ያለ የሰውነት ክብደት በሽንት ውስጥ ያለውን ኬሚካላዊ ሚዛን ሊለውጥ ይችላል፤ ይህም የጠጠር መፈጠርን ያበረታታል፡፡

 

የኩላሊት ጠጠር ምልክቶች ምንድን ናቸው?

የኩላሊት ጠጠር በኩላሊት ውስጥ መንቀሳቀስ እስኪጀምር ወይም ወደ ሽንት ቱቦ ውስጥ እስኪገባ ድረስ ምንም አይነት ምልክቶችን ላያመጣ ይችላል፡፡ ምልክቶቹ በሚከሰቱበት ጊዜ ግን በጣም ከባድ ሊሆኑ የሚችሉ ሲሆን የሚከተሉትን ያካትታሉ:

 

  1. ከባድ ህመም: የኩላሊት ኮሊክ በመባል የሚታወቀው ይህ አይነት ህመም የሽንት መተላለፊያ የኩላሊት ክፍሎች ወይም ሽንት ቱቦ በ ከፊል ወይም በሙሉ ሲዘጋ የሚመጣ ሲሆን ብዙውን ጊዜ ኃይለኛ ተብሎ ይገለጻል፡፡ ይህ ህመም በጀርባ፤ በጎን፤ በታችኛው የሆድ ክፍል ወይም ብሽሽት ላይ ሊከሰት ይችላል.  በጥንካሬው ሊለዋወጥ የሚችል ፤ ሄድ መለስ የሚል እና ሲመጣ ከ 20-30 ደቂቃ የሚቆይ የመጠዝጠዝ እና የመውጋት ስሜት ያለው ነው፡፡ ከ ህመሙ በተጨማሪ የማቅለሽለሽ እና የማስታወክ ስሜት ሊኖር ይችላል፡፡

ይህ አይነት ህመም ብዙውን ጊዜ አንድ ሰው ሊቋቋመው ከሚችለው በላይ በጣም የሚያሠቃይ ሲሆን ታማሚዎች ወደ ድንገተኛ ክፍል እንዲሄዱ ያደርጋል፡፡

 

  1.  ደም የቀላቀለ ሽንት፡ ሽንቱ ሮዝ ፤ ቀይ ወይም ቡናማ ሊመስል ይችላል.
  2. ተደጋጋሚ ሽንት የመሽናት ፍላጎት መጨመር፡ ብዙውን ጊዜ በሽንት ጊዜ ምቾት ማጣት፤ የመጠዝጠዝና ማቃጠል ስሜት ሊከሰት ይችላል.
  3. የሽንት ቦንቦ ኢንፌክሽን በተጨማሪ ካለ፡ ትኩሳት እና ብርድ ብርድ ማለት ከሌሎቹ ምልክቶች ጋር አብሮ ሊኖር ይችላል፡፡
  4.  የደፈረሰ ወይም መጥፎ ሽታ ያለው ሽንት፡ ይህ የሽንት ቱቦ ኢንፌክሽንን ሊያመለክት ይችላል፣ ይህም ከኩላሊት ጠጠር ጋር አብሮ ሊከሰት የሚችል ነው
  5. አንዳንድ ታካሚዎች ከሽንት ጋር ደቃቅ ጠጠሮች ሲወጡ ሊያስተውሉ ይችላሉ፡፡
  6. ለረጅም ጊዜ ችላ የተባለ የኩላሊት ጠጠር የሽንት መተላለፊያ ቱቦዎችን በመዝጋት፡ ኩላሊት እንዲጎዳና ፤ባስ ሲልም የኩላሊት ስራ ማቆምን ሊያስከትል ይችላል፡፡

 

ለኩላሊት ጠጠር የሚደረጉ ምርመራዎች የሚከተሉትን ያካትታሉ፡

  1.  የሽንት ምርመራ፡

የሽንት ምርመራ ጠጠር መኖሩን የሚያመለክቱ የኢንፌክሽን፣ የደም እና ክሪስታል ምልክቶችን ሊያሳይ ይችላል፡፡ ለጠጠር መፈጠር አስተዋጽኦ የሚያደርጉትን የተለያዩ ማዕድናት መጠን ለመለካት የ24 ሰዓት የሽንት ምርመራ ሊደረግ ይችላል፡፡

2. የደም ምርመራ፡

የደም ምርመራዎች እንደ ካልሲየም ወይም ዩሪክ አሲድ ያሉ የኩላሊት ጠጠር እንዲፈጠር የሚያደርጉ አንዳንድ ንጥረ ነገሮች በደም ውስጥ ያላቸውን መጠን ለመለየት ይረዳል፡፡ በተጨማሪም ከደም የሚሰራ የኩላሊት የማጣራት አቅም ምርመራ ማድረግ ይቻላል፡፡

  1. የ ኢሜጂንግ (በምስል የተደገፉ) ምርመራዎች፡ እነዚህ ምርመራዎች የኩላሊት ወይም የሽንት ቱቦ ጠጠር መኖሩን ፤ መጠኑን ብዛቱን እና ቦታውን ለማረጋገጥ የሚያግዙ ሲሆኑ በዋናነት የሚከተሉትን ያጠቃልላሉ፡

ሀ. የአልትራሳውንድ ምርመራ ፡ የኩላሊት ጠጠር መኖሩን፤ መጠኑን ፤ ቦታውን ለመለየት ያስችላል፡፡ እንደዚሁም የ ኩላሊት መጠኑን ለመለካት እና የሽንት መተላለፊያ መዘጋትን ለማየት ያስችላል፡፡ አንዳንድ የ ኩላሊት ጠጠሮች በ አልትራሳውንድ ላይታዩ ይችላሉ፡፡

ለ. የራጅ ምርመራ፡ በተመሳሳይ ጠጠር ለማየት የሚያሰችል ነው፡፡ የተወሰኑ የ ጠጠር አይነቶች በ ራጅ ላይገኙ ይችላሉ፡፡

ሐ. የሲ.ቲ ስካን () ምርመራ፡  ሁሉም አይነት የኩላሊት ጠጠሮችን በ ትክክል ሊያሳይ የሚችል የ ምርመራ ዐይነት ሲሆን ፤ ለ ኩላሊት ጠጠር ከሚደረጉ ህክምናዎች በፊት ቢሰራ ተመራጭ ነው፡፡

 

የኩላሊት ጠጠር የህክምና አማራጮች

 

የኩላሊት ጠጠርን የህክምና ስልቶች እንደ ጠጠሩ መጠን፣ አይነት እና ቦታ እንዲሁም የሕመም ምልክቶች እና ክብደት ይወሰናሉ፡፡

መጠናቸው ከ 7 ሚሊ ሜትር በታች የሆኑ እና ኩላሊት ላይ ጉዳት ያላደረሱ ጠጠሮች በራሳቸው ከሽንት ጋር ሊወጡ ይችላሉ ተብሎ ይታሰባል፡፡

የኩላሊት ጠጠር ህክምና የሚከተሉትን ያካትታል፡

 

  1. የህመም ማስታገሻ: የኩላሊት ጠጠር ህመም ኃይለኛ ሊሆን የሚችል ሲሆን እንደ ibuprofen ወይም acetaminophen ያሉ የህመም ማስታገሻዎች ብዙ ጊዜ ይመከራሉ፡፡ ለከባድ ህመም በሐኪም የሚታዘዙ የበለጠ ጠንካራ መድሃኒቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡

 

  1. 2. በቂ ፈሳሽ መጠጣት፡ ታካሚው የሚወስደውን የፈሳሽ መጠን መጨመር ትናንሽ ጠጠሮችን ከሽንት ጋር ለማስወገድ ይረዳል፡፡ ብዙውን ጊዜ ታካሚዎች ንጹህ ሽንት እስኪኖራቸው በቂ ውሃ እንዲጠጡ ይመከራሉ፡፡

 

  1. መድሃኒቶች: አንዳንድ መድሃኒቶች (ለምሳሌ ታምሱሎሲን ) ጠጠር በቱቦ ውስጥ በቀላሉ እንዲተላለፍ ለማመቻቸት ይረዳሉ፡፡ ሌሎች የመድሃኒት አይነቶች ደግሞ ወደፊት የጠጠር መፈጠርን ለመከላከል ሊታዘዙ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ ለካልሲየም ጠጠሮች ታይዛይድ ዳይሬቲክስ ሊታዘዝ ይችላል፡፡
  2. ጠጠር የመሰባበርና የማውጣት ህክምናዎች፡ ጠጠሮች በራሳቸው ለማለፍ የማይችሉ እና ትልቅ ከሆኑ ወይም ከፍተኛ ውስብስብ ችግሮች ካደረሱ እነዚሀ የሕክምና ሂደቶች ሊያስፈልጉ ይችላሉ:

ሀ. የድምጽ ሞገድ ህክምና (Extracorporeal Shock Wave Lithotripsy (ESWL))፡ ጠጠሩን በሽንት ውስጥ ሊተላለፉ ወደሚችሉ ትናንሽ ቁርጥራጮች ለመስበር የድምፅ ሞገዶችን የሚጠቀም የህክምና አይነት ሲሆን እስከ መካከለኛ መጠን ለሆኑ ጠጠሮች ያገለግላል፡፡ ይህ ህክምና በታካሚው ሰውነት ውስጥ ምንም አይነት መሳሪያ ሳይገባ ከውጭ የሚደረግ ነው፡፡

ለ. የ ሽንት ቱቦ እና ኩላሊት ኢንዶሰኮፒ (Ureterorenoscopy): በሽንት ቱቦ ውስጥ ወይም በኩላሊት ውስጥ ያሉ ጠጠሮችን ለማውጣት ወይም ለመስበር ቀጭን የኢንዶስኮፒ መሳሪያ በሽንት ቱቦ ውስጥ በማስገባት ጠጠሮችን በመሰባበር እና በማውጣት ያለ ምንም ጠባሳ የሚደረግ እጅግ ዘመናዊ የ ህክምና አማራጭ ነው፡፡

ሐ. በትንሽ ቀዳዳ የሚደረግ የኩላሊት ኢንዶሰኮፒ( percutaneous Nephrolithotomy (PCNL)): በጀርባ ላይ በትንሽ ቀዳዳ (1 ሴ.ሜ የሚያህል) አማካኝነት ትላልቅ ጠጠሮችን በቀጥታ ከኩላሊት ሰባብሮ ለማስወገድ የሚደረግ የቀዶ ጥገና ሂደት ነው፡፡

መ. ሆድ ተከፍቶ የሚደረግ ቀዶ ህክምና (Open surgery) : በጣም ትልልቅ ጠጠሮች በሚኖሩ ጊዜ እንደዚሁም ሌሎች ዘመናዊ አማራጮች በሌሉበት ጊዜ የሚደረግ የህክምና አማራጭ ነው፡፡

 

 

የኩላሊት ጠጠርን እንዴት መከላከል ይቻላል

 

የኩላሊት ጠጠርን መከላከል የአኗኗር ዘይቤን እና አጋላጭ መንስኤዎችን ለመቀነስ የታለሙ የአመጋገብ ለውጦችን ያካትታል፡፡ ዋና ዋና የመከላከያ እርምጃዎች የሚከተሉት ናቸው፡-

 

  1. ብዙ ፈሳሾችን በተለይም ውሃን መጠጣት በሽንት ውስጥ ጠጠር ሊፈጥሩ የሚችሉ ንጥረ ነገሮችን ለማሟሟት ይረዳል፡፡ በቀን ቢያንስ ከ8-10 ብርጭቆ ውሃ መጠጣት የሚመከር ሲሆን ሽንት ንጹህ ወይም ቀላል ቢጫ እስኪሆን ድረስ እንዲጠጡ ይመከራል፡፡ በውስጣቸው ከፍተኛ የሲትሬት መጠን ያላቸው ፈሳሾች (ለምሳሌ፡ ከ ሎሚ፤ ብርቱካን ፤ አፕል የሚሰሩ መጠጦች) ይመከራሉ፡፡

 

  1. የአመጋገብ ለውጦች፡ እንደ ጠጠሩ ዓይነት የተለያዩ የአመጋገብ ለውጦች ሊረዱ ይችላሉ:
  • ለካልሲየም ኦክሳሌት ጠጠሮች እንደ ስፒናች፣ ለውዝ እና ሻይ ያሉ በኦክሳሌቶች የበለፀጉ ምግቦችን ይቀንሱ፡፡
  • ጨው እና የእንስሳት ፕሮቲን ይቀንሱ: መካከለኛ ፕሮቲን እና ዝቅተኛ ጨው ያለው የተመጣጠነ አመጋገብ ይምረጡ፡፡
  • ሲትሬት ያላቸው ምግቦች (Citrate Intake): እንደ ሎሚ እና ብርቱካን ባሉ የሎሚ ፍራፍሬዎች ውስጥ የሚገኘው ሲትሬት፡ የጠጠር መፈጠርን ለመከላከል ስለሚረዳ እነዚህ አይነት ምግቦች ይመከራሉ፡፡

 

  1. መድሃኒቶች: ተደጋጋሚ የኩላሊት ጠጠር ታሪክ ላላቸው ግለሰቦች ፡ ዶክተሮች አዳዲስ ጠጠሮች እንዳይፈጠሩ ለመከላከል መድሃኒቶችን ሊያዝዙ ይችላሉ፡፡
  2. መደበኛ ክትትል፡ ወቅታዊ የሽንት እና የደም ምርመራዎች ለማድረግ፤ አጋላጭ መንስኤዎችን ለመከታተል እና በአመጋገብ እና በመድሃኒት ላይ አስፈላጊ ማስተካከያዎችን ለማድረግ ይረዳል፡፡

 

ማጠቃለያ

 

የኩላሊት ጠጠር ህመም ከፍተኛ እና ተደጋጋሚ ችግር ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን በተገቢው ምርመራ, ክትትል እና የመከላከያ እርምጃዎች ተጽእኖውን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ ይቻላል፡፡ ምልክቶቹን መረዳት እና ወቅታዊ የሕክምና ምክር መፈለግ ውጤታማ ህክምናን ለማግኘት ወሳኝ ነው፡፡ በመረጃ ላይ የተመሰረተ የአኗኗር ዘይቤን እና የአመጋገብ ለውጦችን በማድረግ፤ በቂ ፈሳሽ በመውሰድ እና የሕክምና ምክሮችን በማክበር ግለሰቦች የኩላሊት ጠጠር የመያዝ እድላቸውን በመቀነስ አጠቃላይ ጤናን ሊጠብቁ ይችላሉ፡፡ የኩላሊት ጠጠርን በተመለከተ ግንዛቤን ማሳደግ፡ ሰዎች የኩላሊት ጠጠርን ለመቆጣጠር እና ለመከላከል ንቁ እርምጃዎችን እንዲወስዱ ያስችላቸዋል፡፡

 

ዋቢ ምንጮች