ክብርት ፕሬዝዳትን ወ/ሮ ሳህለወርቅ ትናንት አዲስ አበባ ከተማን ዞር ዞር ብለው አይተው ለCOVID19 ያለን ግንዛቤ አሁንም አናሳ እንደሆነ በትዊተር ግጻቸው አመላክተዋል

https://twitter.com/SahleWorkZewde/status/1242945641690652672?s=20

ሌሎች ሃገራት ቫይረሱን ለመከላከል በማህበራዊ እንቅስቃሴ ላይ ብዙ እርምጃ እየተራመዱ ነው።ብዙ ሳንርቅ ጎረቤቶቻችንን ኬንያንና ሩዋንዳን ማየት ይቻላል። ቫይረሱን ለመከላከል ሃገራት ሊወስዱት የሚገባው የመጀመሪያው እርምጃ አካላዊ መራራቅን ተግባራዊ ማድረግ ነው። እኛ አሁንም ስለዚህ እያወራን ነው፤ አሁንም ስብሰባዎችንና ተጠጋግቶ መንቀሳቀስ ቫይረሱን እንደሚያስፋፉና መቆም እንዳለባቸው እያወራን ነው። መንገድ ላይ ሰዎች አሁንም ተቀራርበው ይሄዳሉ፤ ጓደኛሞች አሁንም እርስ በርስ ተቃቅፈው ይሄዳሉ፣ አብረው ይጫወታሉ፣ በየካፌው ይገናኛሉ፣ ስብሰባዎች አሁንም አልተቋረጡም፤ የ እምነት ተቋማት ስነ ስርአቶች አሁንም ይካሄዳሉ፤ የመሳሰሉት። ይሄ በአሳዛኝና ገና ብዙ መንገድ እንደሚጠብቀን አመላካች ነው። አንድ ቀን ማለት በመቶዎች የሚቆጠሩ ቫይረሱን እንዲያስፋፉ ወይም እንዳያስፋፉ አስተዋጾ አለው፤ የምናባክነው ጊዜ የለም። መንግስት በዚህ ጉዳይ አቅሙን ተጠቅሞ ማስፋጸም ካልቻለ ሌሎቹ ጥረቶቹ ድንጋይ ላይ ውሃ እንደማፍሰስ ይቆጠራሉ። 

የሰዎች ችላ ማለት አሁንም በተለያዩ ቦታዎች እየተጋፉ መሄድ ተገቢውን ርቀት አለመጠበቅ እና ባጠቃላይ የመከላከያ ጥንቃቄዎችን ችላ ማለት የተለያዩ ምክንያቶች ሊኖሩት ይችላሉ። ይሄ ምናልባት እንደ ማህበረሰብ ለህይወት የምንሰጠው ዋጋና አመለካከት ቫይረሱን ለመከላከል የምናደርገውን ጥንቃቄ ላይ አስተዋጾ ሊኖረው ይችላል። ይሄ ሰፊ ጥናት የሚጠይቅ በራሱ ትልቅ ርእስ ነው፤ መፍትሄውም እንዲህ በአጭር ጊዜና በቀላሉ ለገኝ አይችልም። በኢትዮጵያ መሰረታዊ ራስን ከአደጋ የመከላከል ዝንባሌ በጣም አናሳ ነው፤ ብዙዎች ለምሳሌ የመኪና ቀበቶ ስላላደረጉ ብቻ ለመኪና አደጋና ሞት በተደጋጋሚ ይዳረጋሉ፤ ቀበቶ ማሰር እንደውም በከተማ ቋንቋ እንደማካበድ ይቆጠራል። የመኪና አደጋ ብዙዎችን ይገላል። ነገር ግን ይህን ቫይረስ ከመኪና አደጋ ይበልጥ አደገኛ የሚያደርገው ቫይረሱ ተላላፊ ነው፤ በግዜ ካልተቆጣጠርነው ሁላችንም ቤት መግባቱ አይቀርም። የአንድ ሰው ቀበቶ አለማሰር ግለሰቡን ነው የሚጎዳው ፣ በዚህ ተላላፊ ቫይረስ ግን የ አንዱ ሰው ቸልተኝነት ሁላችንንም ነው ለበሽታ አልፎም ለሞት የሚያጋልጠው።

ቫይረሱን መመከላከል  አካላዊ ቅርርብን ከመግታት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው። ሌላ ሶስተኛ አማራጭ የለም! መንግስት ሰዎች እርስ በርስ ያላቸውን አካላዊ መቀራረብ ማቆም ካልቻለ ሌሎች እርምጃዎቹ ዋጋ አይኖራቸውም። ተማሪዎች ትምህርት አቁመው ውጭ ከጓደኞቻቸው ጋር ከተገናኙ ሰራተኞች ስራ አቁመው የተቀሩት ስብሰባ ላይ ከተገኙ መንግስት የደረሰበት ሃገራዊ የኢኮኖሚ ኪሳራ በከንቱ ባከነ ማለት ነው። ከቤት መውጣት ግዴታው ያልሆነ ሁሉ በጣም አስፈላጊ ከሆኑ ምክንያቶች ውጪ ከቤት መውጣት የለበትም። በተጨማሪም ከከተማ ወደ ሌላ ከተማ የሚደረገውም ጉዞ ላይ መንግስት ገና ካሁኑ በተቻለ መጠን ቁጥጥር ማድረግ አለበት። በተለይ በሌሎች ሃገራት እንደታየው እንደ አዲስ አበባ አይነት ብዙ ሰው የሚኖርበት ከተማ ለበሽታው ይበልጥ የተጋለጠ ሊሆን ስለሚችል መንግስት ይህን ጉዳይ ካሁን መከታተልና መፍትሄውን ማስቀመጥ ይኖርበታል። ባጠቃላይ ሰዎች ከቻሉ እቤታቸው እንዲቆዩ ማስገደድ ካልሆነም የሰዎችን አካላዊ ርቀትን እንዲጠብቁ ማድረግ መንግስት ከምንም በላይ አጽንኦት ሰጥቶ የከተማና የየክልሉ ፖሊስን እንዲሁም የፌደራሉን ሃይል ተጠቅሞ በሰፊው መንቀሳቀስ ይኖርበታል።

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የኢኮኖሚ አቅማቸው ደካማ የሆኑ የህብረተሰብ አባላትን ከቤት አትውጡ ማለት በረሃብ ሙቱ ማለት ይሆናል። ስለዚህ ይህን በተመለከተ እኒዚህን የማህበረሰብ አባላት የሚረዱበትን መንገድ ማመቻቸት ከመንግስትና ከተለያዩ መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት ይጠበቃል። በዚህ ረገድ የተለያዩ በጣም የሚበረታቱ ጅማሬዎች ከመንግስት እና ከተለያዩ ቡድኖች ባለሃብቶችና በጎፈቃደኞች ተጀምሯል። እንዚህን በጎ ጅማሬዎች እያደረጉ ለሚገኙ አካላት ሁሉ የጤናወግ ምስጋናዋን ታቀርባለች ። ጅማሬው ቀጣይነት ይኖረው ዘንድ እነዚህ አካላት አብረው በቅንጅት የሚሰሩበት መንገድ ቢመቻች ለውጤቱ መሳካትና ለክትትል ይረዳል። እነዚህ አካላት የመንግስትን እስከ ቀበሌ ድረስ የሚደርስ መዋቅር ተጠቅመው የቀበሌ አመራርና አባላት በእርዳታ መካተት አለባቸው የሚሏቸውን አባሎቻቸውን በቶሎ መመዝገብና ለበላይ የመንግስት አባላት ማስተላለፍ አለባቸው። የበላይ አባላትም የሚረዱትን የአባላት ቁጥር በጊዜ ካወቁና በቅንጅት ከእርዳታ አሰባሳቢዎች ጋር ቢሰሩ ብዙ ርቀት ለመጓዝ ይረዳል። ከዚህም በተጨማሪ አባላት በቅንጅት መሰባሰባቸው ለትጠያቂነትና ገንዘቡ በአግባቡ መዋሉን ለማረጋገጥ ይጠቅማል።

https://twitter.com/FMoHealth/status/1243162066187431937?s=20