ዛሬ በመግለጫው የተሰጠውን ስህተት ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ተገንዝቦ ህዝብ እንዳይደናገር ግልፅ በሆነ መልኩ እንደገና ማብራሪያ መስጠት አለበት፤ ለህዝቡም ግልጽ በሆነ ቋንቋ በአሁን ሰአት ኮሮና ቫይረስ ምንም አይነት መድሃኒት እንደሌለውና ጥንቃቄውን አጠናቅሮ እንዲቀጥል ማስገንዘብ አለበት።

በዛሬው እለት የፈጠራና ቴክኖሎጂ ሚንስትርና የጤና ጥበቃ ሚንስቴር ሃላፊዎች በጋራ ባወጡት የፕሬስ መግለጫ ኮሮናቫይረስን ለማከም የተሰራው መድሃኒት መሰረታዊ የምርምር ሂደት ማለፉን በተጨማሪም ተደጋጋሚ የቤተ ሙከራ ሂደቶችን በስኬት ማለፉን ገልጸዋል።

ይህ ተገኘ የትባለው መድሃኒት በቂ ማብራሪያ ያልተሰጠበት እና ብዙ ጥያቄዎችን ያጫረ ነው። አንድ መድሃኒት በህክምና መድሃኒትነቱ  የሚረጋግጥበት የራሱ አካሄድና ደረጃዎች አሉት። በመጀመሪያ የመድሃኒት ምርምሩ በላብራቶሪ ይጀምራል። ለምሳሌ ለኮሮና ቫይረስ የምርምር ሥራ ይደረግ ቢባል ይሄን አዲስ ቫይረስ ለይቶ ለመመርመር በጣም የተራቀቀ ላቦራቶሪ ይጠይቃል ፣ ከዛም ይሰራል የተባለው መድሃኒት በ ቫይረሱ ላይ ያለውን ወጤት ከሰውነት ውጭ ይጠናል፣ እንዳልነው ይሄ ደግሞ ከፍተኛ አቅም ይጠይቃል፣ ኢትዮጵያ ያንን ለማድረግ አቅሙና መሳርያው የላትም፤ በአሁን ሰአት ኮሮናቫይረስን ለመመርመር የሚያስፈልገው መሳርያ test kit እንኳን በእርዳታ ነው ያገኘችው።  መድሃኒቱን ለመስራት ከሰውነት ውጭ በሚደረግ ምርመራ ጥሩ ውጤት ከታየ በተለያዩ እንስሳት ላይ ይሞከራል፣ ያህም ጥሩ ውጤት ካሳየ በመቀጠል ሰዎች ላይ ይሞከራል። ከዛም በማስከተል በጣም ብዙ ሰዎች የሚካፈሉበት እና በሀክምናው የምርመራ ሂደቶች ወሳኝ የሚባለው መድሃኒቱን ከሌሎች መድኃኒቶች ጋር የማወዳደር ሥራ (Randomized Clinical Trial) ይከተላል። ሁሉም ሂደት ጊዜ ይፈልጋል። 

በኛ በኩል ጋሪው ከፈረሱ እየቀደመ  ነው የተቸገርነው፣ በተለይ በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚንስቴር በኩል። እነዚህን ሁሉ ነገሮች ሳናካሂድ መድሃኒቱን ወደ ማምረት ልንገባ እንደሆነ ሲነገረን በነዚህ ተቋማት ላይ ያለን እምነት ይሸረሸራል። በተለይ እንደዚህ አለማችን ከመቶ አመታት በላይ አይታ ማታውቀው ወረርሽኝ እያስተናገደች ባላችበት ጊዜ ህዝቡ የሚተማመንበት እና ይህንን ከፍተኛ ሃላፊተት ይወጣዋል ብለን የምናስበው ጠንካራ የጤና ጥበቃ ስርአት ያስፈገናል። 

ዛሬ በተሰጠው መግለጫ በኢትዮጵያ ተስፋ የተጣለበት መድሃኒት ተመራማሪዎች ከሃገር በቀል ተመራማሪዎች ጋር በመተባበር እየተሰራ እንዳለ ተነግሯል። የሚሰራው ስራ የሚበራታታ ነው፤ ትክክለኛውን መንገድ እና ጊዜውን እስከጠበቀ። ነገር ግን የዛሬው መግለጫ አስፈላጊ አልነበረም፤ ብዙ ውዥንብሮችንም አስከትሏል። ቫይረሱን በመከላከል በኩል የተጀመረውን ሥራ ወደ ኋላ ሊያስኬድ ይችላል። 

  • ሰዎች መድሃኒት አለ ብለው በሽታውን የመከላከል እርምጃዎችን ችላ ሊሉ ይችላሉ።
  • በዚህ አጋጣሚ ሌሎች ያልተጠኑ መድኃኒቶችን ለሕዝብ በመሸጥ ማትረፍ የሚፈልጉ ሰዎች ሕዝቡን ሐሰተኛ መረጃ ሊያሳስቱ ይችላሉ።
  • ህዝቡ በትክክለኛ ሕክምና ላይ እምነት እንዲያጣ ያረገዋል።
  • እንደ ሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ሚንስቴር ያሉ ተቁአማት ደግሞ የ ሳይንስን መርሆዎች (Scientific Methods ) ለሌሎች ማስተማር ነው ሚገባቸው፣ መግለጫቸውም ያንን ማንፀባረቅ አለበት። 

ስለዚህ አሁንም ይሄን ወረርሽኝ ለመቆጣጠር እየሞከርን ባላነበት ጊዜ  COVID 19 በተመለከት የህክምና ባለሙያዎች ብቻ መግለጫ ቢሰጡ ይመረጣል።

ዛሬ በመግለጫው የተሰጠውን ስህተት ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ተገንዝቦ ህዝብ እንዳይደናገር ግልፅ በሆነ መልኩ እንደገና ማብራሪያ መስጠት አለበት፤ ለህዝቡም ግልጽ በሆነ ቋንቋ በአሁን ሰአት ኮሮና ቫይረስ ምንም አይነት መድሃኒት እንደሌለውና ጥንቃቄውን አጠናቅሮ እንዲቀጥል ማስገንዘብ አለበት።

የጤና ወግ

በመረጃ የተመሰረተ ሕክምና ብቻ ።  

………………………………………………………………………………………………………………………..

ይህ የጤና ወግ ድረ ገፅ ነው።
ስለ ጤንነታችሁ ማወቅ የምትፈልጉትን መረጃ የምታገኙበት ፣ በህክምና ባለሙያዎች የሚዘጋጅ የመረጃ ምንጭ ነው።
ሁልግዜም ከሀኪማችሁ ተማከሩ፣ ተጨማሪ መረጃ ከፈለጋችሁ የኛን ድረ ገፅ ጎብኙ።

በጥናት የተደገፈ መረጃ ብቻ እናቀርባለን።

የህክምና ባለሙያዎች ለህሙማኖቻችሁ የሚሆን የሚነበብ መረጃ ከፈለጋችሁ ይህን ግፅ ጠቁሟቸው። ህሙማኖቻችሁ እንዲያውቁት የምትፈልጉትን ነገር መረጃ ጠቅሳችሁ ፃፉልን፣ ስምችሁን ጠቅሰን እናወጣለን። የህክምና ተማሪዎች እንዲጽፉ እናበረታታለን።

በተጨማሪም በጤና ወግ ፖድካስት በ ዩትዩብበ ትዊተርበ ፌስቡክ ፣ በቴሌግራም የተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ ገፆቻችን ታገኙናላችሁ ።