ዶ/ር ብሩክ አለማየሁ (የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት)
.. በቫይረሱ እንደተያዙ ተጠርጥረው ምርመራቸው ግን ነጌቲቭ የሆኑና ከመለያ ማዕከል እንዲወጡ የሚደረጉ ታካሚዎች ከሃኪሞቻቸው ጋር ተማክረው ቢያንስ ለ14ቀን ራሳቸውን ቢለዩ ይመረጣል፡፡
Tweet
የPCR ምርመራ ከዚህ በፊት ስለተለያዩ የኮቪድ19 ምርመራዎች ባወጋንበት ፅሁፍ ላይ እንደጠቀስነው አሁንም ዋነኛ የኮቪድ19 መመርመሪያ ሆኖ ቀጥሏል፡፡
እንደ መነሻ መጠቀስ ያለበት ነገር ቢኖር የትኛውም አይነት የላቦራቶሪ ምርመራ የራሱ የሆነ በሽታውን የመለየት አቅም (Sensitivity) እና የትክክለኝነት አቅም (Specificity) እንዳለው ሊታወቅ ይገባለ፡፡
rRT-PCR የቫይረሱን ዘረ-መል በመለየት በቀጥተኝነት ስለሚመረምር ያለው የትክክለኝነት አቅም ከፍተኛ (ከ95% በላይ) ቢሆንም አንድን ታካሚ በሽታው የለበትም ወይም ውጤቱ ኔጌቲቭ ነው ሲለን ግን በምን መልኩ ነው ይህን መረዳት ያለብን የሚለው ጉዳይ አስፈላጊ ነው፡፡
የPCR ምርመራ በሽታውን የመለየት አቅሙ (Sensitivity) ምን ያህል ነው?
እስካሁን ይህን በተመለከተ የወጡ ጥቂት ጥናቶች አሉ፡፡ በተለይ በመጋቢት2/2012 ዓ.ም. “Detections of SARS-CoV-2 in Different Types of Clinical Specimens” በሚል ርዕስ በ JAMA ላይ የወጣ አንድ ጥናት ከተለያዩ ዓይነት ናሙናዎች አንፃር የምርመራውን የመለየት አቅም በጥሩ ሁኔታ አሳይቶናል፡፡
በዚህ ጥናት የተካከተቱት፡- ከታችኛው የአየር ቧንቧ የተወሰዱ ናሙናዎችን [ለምሳሌ፡ Bronchoalveolar lavage, Bronchoscopic brush biopsy, sputum (አክታ)]፣ ከላይኛው የአየር ቧንቧ የተወሰዱ ናሙናዎችን [ለምሳሌ፡ ከአፍንጫ እና ከጉሮሮ የሚወሰዱ ናሙናዎችን)፣ ሰገራ፣ ሽንት እና ደም ናቸው፡፡
በውጤቱም መሰረት ለአብዛኞቹ ታካሚዎቻችን የምንጠቀምባቸው የላይኛው አየር ቧንቧ ናሙናዎች ውጤት ከሚጠበቀው አንፃር ዝቅተኛ ሆኖ ተገኝቷል (አፍንጫ፡ 63% እና ጉሮሮ፡ 32%):: በተመሳሳይም ሰንጠረዡ ላይ እንደሚታየው rRT-PCR ከሽንት፣ ደም እና ሰገራ ናሙናዎች ቫይረሱን የማግኘት አቅሙ ዝቅተኛ ነው፡፡ በተቃራኒው ከፍተኛ የመለየት አቅም (93%) የታየው ከ Bronchoalveolar lavage (ብሮንኮስኮፒ ተሰርቶ ከሚገኝ ፈሳሽ ናሙና) እንደሆነ ታይቷል፡፡
በተመሳሳይም ሌሎች ጥናቶችም የ rRT-PCR ቫይረሱን የመለየት አቅም በግርድፉ በ59% እና 71% መሃከል እንደሆነ ያስቀምጡታል፡፡
የዚህ እንድምታው (Implication) ምንድን ነው?
ከላይ እንደተመለከትነው የ rRT-PCR የመለየት አቅም ከሚፈለገው በታች መሆኑ የራሱ እንድምታዎች አሉት፡፡ ለምሳሌ ቫይረሱን የማግኘት አቅሙ 63% ነው ሲባል ከ100 በቫይረሱ ከተጠቁ ታካሚዎች ውስጥ 63ቱን መለየት ሲችል 37ቱን ግን በሽታው የለባቸውም ወይም ኔጌቲቭ ናቸው ይላል ማለት ነው፡፡ ይህ አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡ ምርመራው ኔጌቲቭ የሚል ውጤት ሲሰጠን ትክክለኛ ኔጌቲቭ (True Negative) ነው ወይስ የተሳሳተ ኔጌቲቭ (False Negative) የሚለውን ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ይህንንስ እንዴት ማስታረቅ ይቻላል?
ይህ መታየት ያለበት ከምርመራው በፊት ባለሙያው ያ ታካሚ በቫይረሱ እንደተጠቃ በሚኖረው የጥርጣሬ መጠን/እድል (Pre-test probability) ላይ ይመሰረታል፡፡ ይህ ጥርጣሬ ደግሞ የሚመሰረተው በታካሚው የበሽታ ምልክቶች፣ በበሽታው ለመያዝ ባለው ተጋላጭነት እና በቫይረሱ እንደተጠቁ ከሚጠረጠሩ ወይም ከታወቁ ሰዎች ጋር በነበረው የንክኪ ታሪክ እና በመሳሰሉት ላይ ነው፡፡
እንደ ቀላል ምሳሌ ብንወስድ አንድ ሳልና ትኩሳት ያለውና ከውጪ ከመጣና የበሽታውን ምልክት ካሳየ ሰው ጋር ንክኪ የነበረው ግለሰብ የ rRT-PCR ምርመራው ኔጌቲቭ ቢሆን ይህ ኔጌቲቭ በጥርጣሬ መታየት ይኖርበታል ማለት ነው፡፡
የተሳሳተ ኔጌቲቭ (False Negative) የሚባሉትን እንዴት ልንለያቸው እንችላለን?
በተጠቀሰው ዓይነት አጠራጣሪ ሁኔታዎች ወቅት መጠቀም የምንችላቸው አማራጮች የሚከተሉት ናቸው፡፡
ሀ. ናሙናዎችን ከአንድ ቦታ ብቻ ሳይሆን ከ2 ወይም ከ3 ቦታዎች መውሰድ
ለ. ከ24 ሰዓት በኃላ ምርመራውን መድገም
ሐ. ሌሎች አጋዥ ምርመራዎችን መጠቀም፡- ከዚህ አንፃር የሳንባ ሲቲ ስካን (Chest CT Scan) ሚና ሳይጠቀስ አይታለፍም፡፡
ስለ ሳንባ ሲቲ ስካን
በተለይ ቻይና ላይ በተደረጉ ጥናቶች የሳንባ ሲቲ ስካን ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑ ታይቷል፡፡ እንደውም የተወሰኑ ጥናቶች የሳንባ ሲቲ ስካን በሽታውን የመለየት አቅም ከ rRT-PCR በላይ ሆኖ እንዳገኙትና (አንዳንድ ጥናቶች እስከ 98% ሪፖርት አድርገዋል) ለሁሉም ታካሚዎች እንደ መጀመሪያ ምርመራ ሲቲ ስካን መጠቀም በሽታውን ለመለየት በጣም አጋዥ እንደሆነ ሃሳብ ሰጥተዋል፡፡ ሆኖም ግን የሳንባ ሲቲ ስካን በሽታውን “አለ” ቢለንም ያለው የትክክለኝነት አቅም (Specificity) ዝቅተኛ (ባንዳንድ ጥናቶች 25% ብቻ) በመሆኑ ከላቦራቶሪ ምርመራዎቹ ጋር አብሮ ቢጣመር የተሻለ ነው፡፡
የመጨረሻ ሃሳብ
እንዚህን ሁሉ መንገዶች ተጠቅመን የተሳሳቱ ኔጌቲቮችን እንቀንሳለን እንጂ ሙሉ በሙሉ ማስወገድ አንችልም፡፡ ማለትም ተደጋጋሚ ምርመራ ተካሂዶ፣ ሲቲ ስካንም ተጠቅመን በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ሳይገኙ ሊቀሩ ይችላሉ፡፡
በተለይም ደግሞ እንደ ኢትየጵያ ባሉ ሀገራት ደጋግሞ መመርመርም ሆነ ሲቲ ስካንን ማግኘትና መጠቀም አስቸጋሪ ከመሆኑ አንፃር ነገሩን የበለጠ አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡ ብዙ በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎችም ሳይታወቁ ወይም ህመሙ ሳይገኝላቸው ሊቀር ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ ሳይታወቅ እነዚህ ሰዎች በሽታውን ለሌሎች ሰዎች ሊያስተላልፉና በሌሎች ጤና ላይም አደጋ ሊደርስ ይችላል፡፡
ስለዚህም በቫይረሱ እንደተያዙ ተጠርጥረው ምርመራቸው ግን ነጌቲቭ የሆኑና ከመለያ ማዕከል እንዲወጡ የሚደረጉ ታካሚዎች ከሃኪሞቻቸው ጋር ተማክረው ቢያንስ ለ14ቀን ራሳቸውን ቢለዩ ይመረጣል፡፡
ምንጮች