ለልቱ መገርሳ (በአ.አ.ዩ ህ/ጤ/ሳ/ኮ የ 4ኛ አመት የህክምና ተማሪ) 

በአለም አቀፍ ደረጃ ከሚገኙ ሴቶች መካከል 52 በመቶ የሚሆኑት በየወሩ የወር አበባን ያያሉ፡፡ ነገር ግን ትክክለኛ የወር አበባ ንፅህና አጠባበቅ መረጃ ያላቸው ሴቶች ቁጥር በተለይ በታዳጊ ሀገራት አነስተኛ ነው። ዩኒሴፍ ዋሽ (UNICEF WASH) እኤአ ግንቦት 2017 በስድስት የኢትዮጵያ ክልሎች ባደረገው ሀገራዊ መሰረታዊ ጥናት መሰረት በጉርምስና ዕድሜ ላይ ከሚገኙ ልጃገረዶች መካከል የወር አበባ ንፅህና መጠበቂያ በ24 ሰዓታት ውስጥ  ከሶስት እስከ አራት ጊዜ መቀየር እንዳለበት የሚያውቁት 23.7%  ሴቶች ብቻ ናቸው። ከዚህም በተጨማሪ በኢትዮጵያ 11 በመቶ የሚሆኑ ልጃገረዶች የወር አበባ ንፅህና መጠበቂያ የሚቀይሩት በቀን አንድ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ይህም የዓለም ጤና ድርጅት ባወጣው የወር አበባ ንፅህና አጠባበቅ መስፈርት መሰረት በቂ የሚባል አይደለም:: 

የወር አበባ ጤና እና ንፅህና የወር አበባን ከጤና ፣ ከደህንነት ፣ ከፍትሃዊነት ፣ ከጾታ እኩልነት እና ከትምህርት ጋር የሚያገናኙትን ሰፋ ያሉ የስርዓተ-ፆታ ሁኔታዎችን ያጠቃልላል። የዓለም ጤና ድርጅት (ዩኒሴፍ የጋራ ክትትል ፕሮግራም) በቂ እና ትክክለኛ የወር አበባ ንፅህና አጠባበቅን እንደሚከተለው ገልጿል፡-  ‘ሴቶች እና ልጃገረዶች የወር አበባን ደም ለመያዝ የሚያገለግል ንፁህ የወር አበባ ንፅህና መጠበቂያ መጠቀም ፣ በአሻቸው ጊዜ ግላዊነቱ በተጠበቀ ቦታ መቀየር ፣ በወር አበባ ጊዜ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ሰውነትን ለማጠብ ሳሙና እና ውሃ መጠቀም ፣ ያገለገሉ የወር አበባ ንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን ለማስወገድ አስተማማኝ እና ምቹ መገልገያዎችን ማግኘት ፣ ከወር አበባ ዑደት ጋር የተቆራኙትን መሰረታዊ እውነታዎች መረዳት እና እንዴት በክብር ፣ በምቾት እና ያለፍራቻ የወር አበባ ንፅህናን መጠበቅ እንደሚቻል መገንዘብን ያካትታል።’

የወር አበባ ደም ለመያዝ የሚያገለግሉ የወር አበባ ቁሳቁሶች የንፅህና መጠበቂያ ፓድ፣ ጨርቆች፣ ታምፖኖች እና  የወር አበባ ካፕስን ያካትታሉ። የወር አበባ ንፅህና አጠባበቅን ከሚደግፉ እቃዎች መካከል የአካል እና የልብስ ማጠቢያ ሳሙና፣ የውስጥ ሱሪ ፣ የህመም ማስታገሻ መድሀኒቶች እና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ።

 

ትክክለኛ የወር አበባ ጤና እና የንጽህና አጠባበቅ ልምዶች የሚከተሉትን ይመስላሉ፡-

 

በቀን ቢያንስ ከ 3 እስከ 4 ጊዜ (በየ 4-6 ሰአታት) የወር አበባ ንፅህና መጠበቂያ መቀየር አለበት። የውስጥ ልብሶች በየጊዜው እንደየአስፈላጊነቱ መለወጥ አለባቸው።

አንድ የወር አበባ ንፅህና መጠበቂያ እርጥብ ከሆነ ወዲያውኑ መቀየር አለበት።

በወር አበባ ወቅት የቀረውን ደም ለማስወገድ ውጫዊው የብልት አካል መታጠብ አለበት።

ሴቶች የወር አበባ ንፅህና መጠበቂያ ከመቀየራቸው በፊት ሁልጊዜም እጃቸውን በሳሙና መታጠብ አለባቸው።

ብልታቸውን ከፊት ወደ ኋላ ብቻ በመታጠብ እና ፊንጢጣና ብልትን ባለማነካካት ከፊንጢጣ ወደ ብልት በሚመጣ ባክቴሪያ የሚፈጠር ኢንፌክሽንን መከላከል ይገባቸዋል።ብልትን በሚታጠቡ ጊዜ በጣም ጥሩው አማራጭ ውሃ ብቻ መጠቀም ነው።

ያስተውሉ!

በቂ እና ትክክለኛ ያልሆነ የወር አበባ ንፅህና አጠባበቅ እንደ የሽንት ቧንቧ ላሉ ኢንፌክሽኖች ተጋላጭ ያደርጋል። ይህም ወደፊት መካንነት እና ከወሊድ ጋር የተገናኙ ችግሮችን ሊያስከትል ይችላል።

ማጣቀሻ

  1. Guidance for monitoring menstrual health and hygiene (version 1) June 2020 UNICEF
  2. Menstrual hygiene Management Training module, UNICEF Maharashtra, 2014
  3. Menstrual Health Education Resource Second edition, 2013
  4. Menstrual Hygiene Management In Ethiopia National Baseline Report from Six Regions of Ethiopia UNICEF WASH May 2017