በዶ/ር ኤደን በላይ (በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የቀዶ ህክምና ስፔሻላይዜሽን ሬዝደንት)
አንድ ታካሚ የተሳካ ቀዶ ህክምና ካከናወነ በኃላ የሚደረግ የህክምና ክትትል እና ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮች በቀዶ ህክምናው እና በማደንዘዣው ዓይነት እንዲሁም ታካሚው እንዳለበት ተጓዳኝ የጤና ችግር ይለያያል::
ከቀዶ ህክምናዬ በኃላ ምን ሊሰማኝ ይችላል?
–የቁስል ህመም: ከቀዶ ህክምና በኃላ ለሚኖር ህመም እንደ ህመሙ ክብደት የማስታገሻ መድሃኒቶች በቋሚነት ይሰጣሉ ሆኖም በየመሀሉ የህመም ስሜት ሲኖር ለሃኪምዎ በመንገር ተጨማሪ መድሃኒት ማግኘት ይቻላል::
–ማቅለሽለሽና ማስመለስ: በአብዛኛው በሰመመን መድሃኒቶች ፣ አንዳንድ የፀረ ኢንፌክሽን እና የህመም ማስታገሻ መድሃኒቶች መንስኤነት የሚከሰት ሲሆን ከህክምናው አስቀድሞ ተመሳሳይ ምልክት ያላቸው እንዲሁም ሴት ታካሚዎች ይበልጥ ተጋላጭ ናቸው:: እነዚህ ምልክቶች በአብዛኛው በ 24ሰዓት ውስጥ ሊቀንሱ ይችላሉ:: ነገር ግን ተደጋጋሚ ወይም ሀሞት የቀላቀለ ማስመለስ ካለ አስፈላጊው ምርመራ ተደርጎ መታከም ይኖርበታል::
የራስ ምታት: በህብለ-ሰረሰር የሚሰጥ ማደንዘዣ (Spinal Anesthesia) የወሰዱ ታካሚዎች
ከቀዶ ህክምናዬ በኃላ ምን አይነት ችግር ሊያጋጥመኝ ይችላል?
በአጭር ጊዜ የሚያጋጥሙ ችግሮች፦
–መድማት: ይህ እንደ ቀዶ ህክምናው አይነት እና ክብደት የሚወሰን ይሆናል
–የቁስል ማመርቀዝ ወይም ኢንፌክሽን: ይህም የክብደቱ መጠን የሚለያይ ሲሆን የቁስሉ ስፌት ያለበትን የቆዳ ክፍል ብቻ የሚያጠቃና ስር ያልሰደደ እንደሆነ ስፌቱን በመፍታትና ቁስሉን በማጠብና ለተወሰነ ጊዜ ክፍት በመተው ይታከማል:: ነገር ግን ወደውስጠኛው የሰውነት ክፍል የዘለቀ ማመርቀዝ ተጨማሪ ቀዶ ህክምና ሊያስፈልገው ይችላል::
–የቁስል ስፌት መልቀቅ
-የቁስል ቶሎ አለመዳን: የስኳር ህመም፣ በተለያዩ ምክንያቶች በሽታን የመከላከል አቅም መቀነስ፣ የደም ማነስ እና የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ተጠቂ የሆኑ ታካሚዎች ቁስል የመዳን ሂደት ተመሳሳይ ችግሮች ከሌሉባቸው ታካሚዎች ጋር ሲነፃፀር ረዘም ያለ ጊዜ ከመውሰዱም ባሻገር ለቁስል ኢንፌክሽንና ስፌት መልቀቅ ይበልጥ ተጋላጭነት አላቸው::
–የሳንባ ኢንፌክሽን ፣ የሽንት ቱቦ ኢንፌክሽን
–የደም መርጋት ህመም: ለረዥም ሰዓታት መተኛት ወይም ሳይንቀሳቀሱ መቆየት በደም ስር ውስጥ ደም እንዲረጋ ብሎም የረጋው ደም ወደ ሳንባ የደም ዝውውር እንዲሰራጭ በማድረግ እና ጤናማ የደም ዝውውር ስርዓትን በማቃወስ ለድንገተኛ ሞት ሊዳርግ ይችላል::ስለዚህ ይህ ችግር እንዳያጋጥም በቶሎ መንቀሳቀስ እና መንቀሳቀስ ለማይችሉ እና ተጋላጭነት ላላቸው ታካሚዎች የደም ማቅጠኛ መድሃኒቶች ይሠጣሉ::
በረዥም ጊዜ የሚያጋጥሙ ችግሮች፦
እነዚህ ችግሮች እንደ ህመሙ ጠባይ፣ ቀዶ ህክምናው እንደተከናወነበት የአካል ክፍል እንዲሁም እንደህክምናው ውስብስብነት የሚለያዩ ሲሆን ቀዶ ህክምና ከተደረገ ከወራት አሊያም ከዓመታት በኃላ ሊከሰቱ ይችላሉ:: ታካሚው ከቀዶ ህክምናው በፊት የሚደረግለት ቀዶ ህክምና ሊኖረው ስለሚችለው ችግር ወይም ዘላቂ ጉዳት ከሃኪሙ ጋር መወያየት ያስፈልገዋል::
ከሆስፒታል ስወጣ ማድረግ ያለብኝ ጥንቃቄ
-በሃኪምዎ የታዘዘ ማንኛውም መድሃኒት በአግባቡ መውሰድ እንዲሁም ያልታዘዘን መድሃኒት አለመውሰድ
-የሳንባ መኮማተር እና የደም መርጋት ህመም ተጋላጭነትን ለመቀነስ ረዥም ሰዓት አለመተኛት እና ቀላል እንቅስቃሴ ማድረግ
-ከባድ እንቅስቃሴ ከማድረግዎ በፊት ሃኪምዎን ማማከር
-በቀጠሮ ለክትትል ወደ ሀኪም መቅረብ። ነገር ግን የሚከተሉት የጤና ችግሮች ካጋጠሙ በማንኛውም ሰዓት በአፋጣኝ ወደጤና ተቋም መሄድ ያስፈልጋል።
* ትኩሳት፣ ብርድ ብርድ ማለት
* የቁስል አካባቢ መቅላት እና ከቁስል የሚወጣ ፈሳሽ
* ከፍተኛ የህመም ስሜት
* ተደጋጋሚ ማስመለስ
* የእግር እብጠትና ህመም
-በቂ ፈሳሽ መውሰድ፣ በኘሮቲን የበለፀጉ ምግቦች ፣ አትክልትና ፍራፍሬ መጠቀም
-የአልኮል መጠጥና ሲጋራ ማቆም
ሰውነትን መታጠብ (Shower) መቼ መጀመር ይቻላል?
ቀዶ ህክምና ከተደረገ ከ 48 ሰዓት በሁኃላ ሻወር መውሰድ ለቁስል ኢንፌክሽን እንደማይዳርግ ጥናቶች ቢያመለክቱም አስቀድሞ ሃኪምዎን ማማከር ያስልጋል።
በአጠቃላይ የተሳካ የቀዶ ህክምና በቅድመ ቀዶ ህክምናው ዝግጅት ፣ በህክምናው በተገቢው መንገድ መከናወን እንዲሁም በድህረ ቀዶ ህክምናው ክትትል አጥጋቢነት የሚወሰን ይሆናል።