መንግስት አላስፈላጊ ስብሰባዎችን ሰልፎችን፣የሃይማኖት ቦታዎችን እና ትምህርት ቤቶችን እንዲዘጋ እንጠይቅ!

ማርች 15 2020

የኮሮና ቫይረስ መስፋፋትን ተከትሎ አውሮፓና አሜረካ ትምህርት ቤቶችንና የተለያዩ ህዝብ መአከላትን እየዘጉ ይገኛሉ። እዚሁ ቅርብ ጎረበቶቻችን ኬንያና ሩዋንዳም ትምህርት ቤቶችን ዘግተዋል ህዝባዊ ስብሰባዎች(የእምነት ተቋማትን ጨሞሮ) ላይም እገዳ አድርገዋል።  በአጠቃላይ ሰዎች በተቻለ መጠን ማህበራዊ ግንኙነታቸውን በሚገባ እንዲቀንሱ አስፈላጊውን እርምጃ እየወሰዱ ይገኛሉ። ለዚህ ዋንኛ አካሄድ የህክምና ባለሞያዎች በእንግሊዘኛው flattening the curve ብለው ይገልጹታል። ሃሳቡ ወደ አማርኛው ሲወስድ የሰዎችን እንቅስቃሴና ማህበራዊ ግንኙነቶችን በመቀነስ የቫይረሱን የመስፋፋት ሂደት በመቀነስ ብዙ ሰዎች በአንድ ላይ እንዳይታመሙ ማድረግ ነው።ለዚህ ነው የህክምና ባለሞያዎች በዚህ ግዜ ከአስፈላጊ ነገሮች ውጪ ቤት ውስጥ መቀመጥን የሚመክሩት። በየቦታው ከተንቀሳቀስን ቫይረሱን በቀላሉ እናስተላልፋለን፤ እኛ ላይም በቀላሉ ይተላለፋል። ይህ ቫይረሱን ለማጥፋት ሳይሆን በአንድ ግዜ የሚታመመውን ሰው ብዛት ለመቀነስ ነው። አስር ሰው አንድ ታሞ ሃኪም ቤት ከሚሄድ በተለያያ ቀን እየታመመ ቢሄድ እንደማለት ነው። ለግሩም ሰእላዊ ማብራሪያ ይሄን የዋሺንግተን ፖስት ዘገባ ይመልከቱ።

እስኪ በምሳሌ እንየው። አንድ ከተማ በምናባችሁ አስቡ። በከተማው አንድ ሺህ ነዋሪዎች አሉ ከዚህ ውስጥ ሁለቱ የህክምና ባለሞያዎች ናቸው እንበል። (ይህ ከኢትዮጵያ የሃኪም ታካሚ ረሽዎ በብዙ ሺ እጥፍ ይበልጣል)። ከነዚ ሰዎች መሃል አንደኛው (አበበ እንበለው) በኮሮና ቫይረስ ተይዟል ግን ምልክት ስላላሳየ ማንም አላውቅም። አበበ ወንደላጤ ነው፤ በጠዋት ተነሳና እንደተለመደው ወደ ስራ ሄደ፤ ከአለቃውን እና ከሴክረተሪው ጋር የቀርብ ንክኪ አድርጓል። ተጨማሪ ሁለት ሰው ታመመ ማለት ነው። ሴክረተሪው ቤቷ ገብታ ባለቤቷንና አንድ ልጇን እቅፍ አድርጋ ሳመች እራታቸውን በሉ። የአበበ አለቃ ደግሞ እድሜያቸው የገፋ እናትና ሰራተኛው ጋር የቅርብ ንክኪ ነበረው። በነጋታው የሴክረተሪው ባለቤት 70 ሰዎች የተገኙበት የገቢ ማሰባሰቢያ ላይ ተገኘ፤ ልጃቸው ወደ ትምህርት ቤት ሄደ። በሌላ በኩል እድሜ ባለጸጋዋ እናት ቤተክርስትያን ሄደው ቅዳሴ አስቀድሰዋል። 

ይህ እንግዲህ ምንም አይነት የሰብሰባ እገዳ ከሌለ ትምህርት ቤት ከተገኙት ውስጥ በትንሹ 5 ሰው ቢያዝ እንዚህ ሰባት ሰዎች በትንሹ ሌላ 7 ሰው ቢያሲዙ ብላችሁ አስቡ የገቢ ማሰባሰቢያ ላይ የተገኘው ሰው በትንሹ 3 ሰው ለቫይረሱ ቢያጋልጥ ሴትየዋ ክአንድ ሰው ጋር በተክርስትያን ቢሳሳሙ በአጠቃላይ በአንድ ቀን ወደ ሃያ ሰዎች ቫይረሱ ያዛቸው ማለት ነው። ይሄ ቁጥር በጥቂት ቀናት ስንት እንደሚደርስ ማሰብ ይቻላል። ይህ ማለት ለከተማው ሁለት ሃኪሞች ከቁጥጥር ውጭ ሆኗል ማለት ነው። ይህ እንግዲህ ለኮሮና ታካሚዎች ብቻ ነው፤ ለሎች ህመምተኞችን፣ነፍሰጡሮችን፣ያልተጠበቁ ድንገትኛ አደጋዎችን አስቡ። እነዚህ ህክምና ይፈልጋሉ፤ አንዳንዶች ተኝቶ መታከም ይኖርባቸዋል። ይህን ሁሉ ለማድረግ በቂ የህክምና ሃይል አይኖርም። በጣልያን የተከሰተው ይህ ነው። ሃኪሞች የታካሚው ብዛት ከአቅም በላይ ስለሆነባቸው በእድሜ የገፉትን እንዲሞቱ ትተዋቸዋል ኒሞንያ መሰል ህመም ያለባቸውን ህክምና ቢያስፈልጋቸውም ወደ ቤታቸው ልከዋቸዋል።

በእዚች በትንሽ ምሳሌ የተለያዩ ስብሰባና ሰልፎች ካልተዘጉ ቫይረሱ ምን ያህል ሰው በቀላሉ ሊያዝ እንደሚቻል መገመት በጣም ቀላል ነው። የስብሰባ ቦታዎችና ትምህርት ቤቶች ቢዘጉ ስብሰባው ላይ የተገኙት ሰዎች የመያዝ እድል አይኖራቸውም፤ ተማሪዎችም እንዲሁ። ይህ ማለት በዚህ ከተማ ውስጥ የተያዙት የመጀመሪያዎቹ በሽተኞች ለሌሎች የሚያስተላልፉበት መንገድ በእጅጉ ቀነሰ ማለት ነው። ይህም በከተማዎ ላሉት 2 ሃኪሞች ህክምና ለመስጠት አይቸግራቸውም። ይህ ነው የህክምና ባለሞያዎች flattening the curve ብለው የሚገልጹት። በሽታውን ሙሉ ለሙሉ ማጥፋት ሳይሆን በሽታውን የሚያዘውን ሰው በእጅጉ መቀነስና ሃኪሞች ተገቢውን ህክምና እንዲሰጡ ማድረግ። እነ ርዋንዳና ኬንያ እያንዳንዳቸው አንድ የተረጋገጠ የቫይረሱ በሽተኛ እያለባቸው ፐብሊክ ቦታዎችን የዘጉት በዚህ ምክንያት ነው፤ ቅድመ ጥንቃቄ።

ሃገራችን ከዚህ ምን ትማራለች? በተቻለን መጠን ማህበራዊ ግንኙነት እንቀንስ። መንግስት አላስፈላጊ ስብሰባዎችን ሰልፎችን፣የሃይማኖት ቦታዎችን ትምህርት ቤቶችን እንዲዘጋ እንጠይቅ። ችግሩ ከደረሰ ማቆም ስለማይቻል ገና ካሁን ሁላችንም እንጠይቅ፤ በዛው ልክ ውይም ካዛም በላይ ከኛ የሚጠበቀውን የህክምና ተቋማት በሰጡት መመሪያ መሰረት ከፍተኛ ጥንቃቄ እናድርግ።ሃኪሞችና የህክምና ጣቢያዎች በበቂ ሁኔታ በሌሉበት ሃገር ይሄን ችግር ማሰብ እጅጉን ያስፈራል። የቻልነውን ሳይረፍድ እናድርግ።