በዶ/ር ትንሳኤ አለማየሁ

የአለም የጤና ድርጅት ባወጣው እለታዊ ሪፖርት መሰረት የኮሮና ቫይረስ ሀገራችንን ጨምሮ 123 ሀገራት ውስጥ ተሰራጭቷል፡፡ በሀገራችን ተመርምሮ የታወቀው ጃፓናዊ ዜጋ በስራ አጋጣሚም ሆነ በሌሎች ግንኙነቶች የቅርብ ንክኪ የነበራቸው 117 ሰዎች ተለይተው የቅርብ ክትትልና ምርመራ እየተደረገላቸው ነው።

ከዚህ ቀደም ያጋጠሙንን ወረርሽኞች ለመከላከል ካሁኑ ጊዜ በተለየ መንገድ የመረጃ ማስተላለፍያ መንገዶች እጥረት ስለነበረ፣ የጤና ባለሙያዎችን ወደ ዋና ዋና ከተሞች በመጥራት ስልጠናዎች  የፊት ለፊት (face to face training) ይደረጉና ዝግጁነት እንዲኖራቸው ይደረግ ነበር፡፡ እነዚህ ስልጠናዎች ባለሙያዎችን በማገናኘት ልምድ በማለዋወጥ አስፈላጊ የመሆናቸውን ያህል ለትራንስፖርት፣ ለምግብ፣ ለማደሪ ቦታ ያ እና ለቀን አበል ብዙ ወጪ ያስወጡ ነበር፡፡ በነዚህ መንገዶችም መድረስ የሚቻለው ጥቂት ባለሙያዎችን ነበር፡፡ 

ባሁኑ ጊዜ ግን ባለው የሶሻል ሚድያ መስፋፋት እና የስማርት ስልክ ባለቤትነት በተገቢው መንገድ ከተጠቀምንበት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ማስተማር ይቻላል፡ይህን አሁን የምታነቡትን ጽሁፍ ባሁኑ ሰአት ብዙ የጤና ባለሙያዎች እና የጤና ተቋማት አስተዳደሮች ያነቡታል፡፡ ስለዚህ ይኸኛውን ወረርሽኝ ለመከላከል ለየት ያለ አካሄድ ያስፈልጋል፡፡ አብዛኛው ወጪ የእጅ መታጠቢያ ሳንታይዘር ወይም አልኮሆል ለህዝቡ ለማዳረስ ፣ ለጤና ባለሙያዎች የሚዘጋጁ ለየት ያሉ ማስኮች፣ የኮሮና ቫይረስ መመርመርያዎችን እንዲሁም በጣም ለተጎዱት የመተንፈሻ መሳርያዎች (Ventilators) አና የመሳሰሉትን ነገርፕች ለማሟት መዋል አለበት፡፡ በአዲስ አበባ ያሉ የመንግስት እና የግል ሆስፒታሎች ያሉት የመተንፈሻ መሳርያዎች (Ventilators) ከ100 በላይ አይሆኑም፡፡ ለጤና ባለሙያዎች የሚዘጋጁ ስልጠናዎች ባለው ነባራዊ ሁኔታ በሌላ ማስተማርያ መንገድ ሊተኩ የሚችሉ ወጪያቸውም ለህይወት አድን ምርመራዎች እና ህክምናዎች ማዋል ያስፈልጋል።