በርካታ ሰዎች ከቤታቸው በሚወጡ ሰአት በCOVID19 ህመም ላለመያዝ ሲሉ ጓንት ያጠልቃሉ፡፡ ይህ ድርጊት በሚድያ ባለሙያዎች እና በባለስልጣናት ጭምር በየቀኑ በሚተላለፉ የSocial media ፣ የ FM እና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ይታያል፡፡
ስለዚህ ጓንት ማድረግ እና የCOVID19 ህመም ያላቸውን ግንኙነት በዚህ ጽሁፍ እንድንመረምር አነሳስቶናል፡፡
የCOVID19 አምጪ ቫይረስ (SARS-CoV-2) ወደ ሰውነታችን የሚገባው በእጃችን አይደለም፡፡ እንዳውም ቆዳችን በተፈጥሮ ካሉን የበሽታ መከላከያዎች አንዱ በመሆን ከጓንት እኩል ከተለያዩ የባክቴርያ፣ የቫይረስ እና የፈንገስ ተላላፊ ህመሞች ይከላከልልናል፡፡ የCOVID19 አምጪ ቫይረስ (SARS-CoV-2) ወደ ሰውነታችን የሚገባው ከታማሚ ትንፋሽ በሚወጡ ቫይረሱን በያዙ ፍንጣቂዎች ነው፡፡ እነዚህ ፍንጣቂዎች (droplets) አይናችን፣ አፍንጫችን እና አፋችን ሲደርሱ ወደ ሰውነታችን ገብተው ህመሙ ይከሰታል፡፡
ትልቁ ችግር በአማካይ አንድ ሰው በአንድ ሰአት ውስጥ 20 ጊዜ ፊቱን መንካቱ ነው፡፡ ስለዚህም ከCOVID19 ታማሚ የወጡ ቫይረሱን የያዙ ፍንጣቂዎች አካባቢያችን ባሉ የተለያዩ እቃዎች ላይ አርፈው ከዛም በእጃችን ነክተው ወደፊታችን በመጠጋት ወደ ሰውነታችን ሊገቡ ይችላሉ፡፡
ጓንት ማድረጋችን ፊታችንን የምንነካካበትን ፀባይ አይቀይርም፡፡ ጓንት አድርገን በዛው እጃችን ስራ እንሰራለን፣ ፊታችንን እንነካለን፣ መኪና እንነዳለን፣ ብር እንቆጥራለን፣ … ኧረ ምግብም ስንበላ ታይቷል፡፡ የኮሮና ቫይረስ ካረፈበት እቃ ጋር ንክኪ ያደረገ ጓንት ቫይረሱ እንደተጣበቀበት ብዙ ጊዜ ይቆያል፡፡ ባዶ እጅ ላይ ቆሻሻ ሲታይ ቶሎ የመፀዳት እድሉ ከፍተኛ ነው፡፡ ስለዚህም ጓንት እንዳውም ከባዶ እጅ የበለጠ አስተላላፊ ሊሆን ይችላል፡፡ ጓንት ያጠለቁ ሰዎች ላይ “ጓንት በማጥለቄ የኮሮና ቫይረስ አይዘኝም” የሚል በራስ የመተማመን ፀባይ ይታያል፡፡ እንደዛም ስለሆነ ባዶ እጃቸውን ቢሆኑ የማይነካኩትን እቃ ጭምር ለመያዝ ሲደፍሩ ይታያል፡፡
ታድያ ለምን ሀኪሞች ያደርጉታል ልትሉ ትችላላችሁ፡፡ ሆስፒታሎች ውስጥ ታካሚዎችን ስንመረምር አንድ ጓንት ለአንድ ታማሚ ነው፡፡ በስራ ላይ አንድ አዲስ ጓንት ለህክምና ከተጠለቀ የሚቆየው ደቂቃዎችን ነው፡፡ ከዛም ወደ ቀጣይ ታካሚ ከመሄዳችን በፊት ወይ እጃችንን እንታጠባለን ወይ በአልኮሆል እንጠርጋለን፡፡ እንጂ በማህበረሰቡ ውስጥ እየታየ እንዳለው ለሰአታት አንድን ጓንት (ያውም ጊዜ ባለፈ ቁጥር እየቆሸሸ የሚሄድን) አናደርግም፡፡
የአለም የጤና ድርጅትም ይህንን አይነት የጓንት አጠቃቀም አይመክርም (ለጤና ባለሙያዎች እና ለአንባቢዎች የአለም የጤና ድርጅት የጓንት አጠቃቀም መመርያ ላይ ተጨማሪ ለማንበብ ይህንን ሊንክ ይጫኑ )፡፡ የአለም የጤና ድርጅት ጓንቶችን ለጤና ባለሙያዎች ወይ በቤታቸው የCOVID19 ታማሚን እየተንከባከቡ ላሉ የቤተሰብ አባላት ብቻ ይሁን ይላል፡፡
የCOVID19 ወረርሽኝ ሳይከሰት ራሱ የጓንት አቅርቦት እጥረት ነበር፡፡ ወረርሽኙ ከተከሰተ በኋላ በሚታይ ፍራቻ እና ትክክለኛ የህክምና ምክር ወደ ህብረተሰቡ ባለመድረሱ ምክንያት ህይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው የሚሰሩ የህክምና ባለሙያዎች የበለጠ የጓንት እጥረት እንዲያጋጥማቸው ሆኗል፡፡
ስለዚህ ጓንቱን ለሚያስፈልጋቸው እንተው፡፡ ባለማወቅ ለሰአታት ጓንት በማጥለቅ ለCOVID19 ህመም ራሳችንን አናጋልጥ፡፡ ዋናዎቹ መከላከያዎችን እንፈጽም፡፡ ማህበረሰባዊ መራራቅን እንተግብር፣ አስገዳጅ ወዳልሆኑ ሰዎች የተሰበሰቡባቸው ቦታዎች አንሂድ፣ የእጃችንን ንጽህና እንጠብቅ እና በተቻለ አቅም ፊታችንን አንነካካ፡፡
ባለንበት ራሳችንን እንጠብቅ፡፡
የጤና ወግ
በመረጃ የተመሰረተ ሕክምና ብቻ ።
………………………………………………………………………………………………………………………..
ይህ የጤና ወግ ድረ ገፅ ነው።
ስለ ጤንነታችሁ ማወቅ የምትፈልጉትን መረጃ የምታገኙበት ፣ በህክምና ባለሙያዎች የሚዘጋጅ የመረጃ ምንጭ ነው።
ሁልግዜም ከሀኪማችሁ ተማከሩ፣ ተጨማሪ መረጃ ከፈለጋችሁ የኛን ድረ ገፅ ጎብኙ።
በጥናት የተደገፈ መረጃ ብቻ እናቀርባለን።
የህክምና ባለሙያዎች ለህሙማኖቻችሁ የሚሆን የሚነበብ መረጃ ከፈለጋችሁ ይህን ግፅ ጠቁሟቸው። ህሙማኖቻችሁ እንዲያውቁት የምትፈልጉትን ነገር መረጃ ጠቅሳችሁ ፃፉልን፣ ስምችሁን ጠቅሰን እናወጣለን። የህክምና ተማሪዎች እንዲጽፉ እናበረታታለን።
በተጨማሪም በጤና ወግ ፖድካስት፣ በ ዩትዩብ ፣በ ትዊተር ፣ በ ፌስቡክ ፣ በቴሌግራም የተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ ገፆቻችን ታገኙናላችሁ ።