የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን የሽንት ስርአት አካላትን ማለትም (ኩላሊትን ፣ የሽንት ፊኛን እና የላይኛውን (Ureter ) እና የታችኛውን (urethra ) የሽንት ማስተላለፊያ ቱቦዎች  የሚያጠቃ የኢንፌክሽን አይነት ነው። ብዙዎቹ ኢንፌክሽኖች የታችኛውን የሽንት ቧንቧዎች (Urethra ) እና የሽንት ፊኛንና (Urinary Bladder ) ያጠቃሉ። 

ሴቶች ከወንዶች ይልቅ ለበሽታው ይበልጥ ተጋላጭ ናቸው። ኢንፌክሽኖች ከ ሽንት ፊኛ አልፈው ወደ ኩላሊት ከተሻገሩ አሳሳቢ የጤና እክል ሊያስከትሉ ይችላሉ። 

ሃኪሞች የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽንን አንቲባዎቲክ (ፀረ ህዋስ) መድሃኒቶች በመስጠት ያክማሉ። ነገር ግን በሽታው ቀድሞ ሳይከሰት ራስን ከሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን መጠበቅ ከበሽታው ጋር ተያይዘው ሊመጡ የሚችሉ ጉዳቶችን ለመቀነስ ይጠቅማል ። 

የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ምልክቶች ምንድናቸው 

  • አንዳንዴ ምልክት ላያሳይ ይችላል ፤ ካሳዩ ግን ምልክቶቹ እነዚህን ይመስላሉ። 
  • በመጠን አነስተኛ ግን በተደጋጋሚ ሽንት መሽናት 
  • ደመናማ የመሰለ የሽንት ከለር
  • የሽንት ከለር መቀየር – ቀይ፣ ሮዝ ወይም ጠቆር ያለ ሽንት —ከሽንት ጋር የደም ምልክት
  • ያልተለመደ ጠንከር  ያለ የሽንት ሽታ
  • ማህፀን አካባቢ የሚሰማ የመጫን ህመም (ለሴቶች) ወይም ወንዶች ብልታቸው አከባቢ እና የሽንት ፊኛ አከባቢ የሚሰማ ህመም 

የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን አይነቶች 

የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን አይነቶችን ህመሙ በተከሰተበት ቦታ ከፍለን ማየት እንችላለን ። የበለጠ ለመረዳት ምስሉን ይመልከቱ 

የተጎዳው የ ሽንት ቧንቧ ክፍል የህመም ምልክቶች
ኩላሊት (acute pyelonephritis) የጎንና የጀርባ ህመም
ሃይለኛ ትኩሳት
መንቀጥቀጥ እና ብርድ ብርድ ማለት
የማቅለሽለሽ ስሜት እና ማስመለስ 
ፊኛ (cystitis) ማህፀን አካባቢ የሚሰማ የመጫን ህመም (ለሴቶች) ወይም ወንዶች ብልታቸው አከባቢ እና የሽንት ፊኛ አከባቢ የሚሰማ ህመም ሆዳችን ወደታች አካባቢ የሚሰማ ጥሩ ያልሆነ ስሜት
በተከታታይ ህመም ያለበት ሽንት መሽናት
ደም የተቀላቀለበት ሽንት
የታችኛው የሽንት ቧንቧ  Urethra (urethritis) ሽንት በሚሸናበት ጊዜ የማቃጠል ስሜት
ፈሳሽ መኖር

እነዚህ ምልክቶች ከታዩብዎ ሃኪምዎን ያማክሩ። አስፈላጊውን ምርመራ እና ሕክምና ያገኛሉ።

የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን መንሰኤዎች 

የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን የሚከሰተው ባክቴሪያ ወደ ሽንት ቧንቧ ገብቶ በሚራባበት ጊዜ ነው። የሽንት ስርአታችን በተፈጥሮ ባክቴሪያዎችን እንዲያስወግድ የተሰራ ቢሆንም አንዳንዴ ተፈጥሮአዊው መከላከያ መንገድ አሰራሩን በማሽነፍ ባክቴሪያዎች ወደሰውነታችን ገብተው በሽታ ሊያመጡ ይችላሉ።  

በተፈጥሮ የብልቶቻችን አቀማመጥ የተነሳ ሴቶች ከወንዶች የበለጠ ለሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን የበለጠ የተጋለጡ ናቸው ። 

የግብረ ስጋ ግንኙነት ለ ሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ሴቶችን በተለይ የበለጠ ተጋላጭ ሊያደርግ ይችላል። 

ሴቶች በተለይ ባላቸው የሰውነት አቀማመጥ (Female anatomy) ምክንያት  በግብረ ስጋ ግንኙነት ወቅት ፣  በማህፀን ውስጥ በሚቀመጡ አንዳንድ የወሊድ መከላከያዎች እንዲሁም የሴቶች ማረጥ (Menopause) ጊዜ  የበለጠ  ለሽንት ቧንቧ እንፌክሽን ከፍተኛ ተጋላጭ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል። 

ከነዚህ በተጨማሪ የሚከተሉት ሁኔታዎች ሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ተጋላጭነትን ይጨምራሉ።

  • ጤናማ ያልሆነ የሽንት ቧንቧ ኖሯቸው የሚወለዱ ህጻናት
  • የሽንት ቧንቧ መደፈን፦ ይህም በኩላሊት ጠጠር ምክንያት ወይም መጠኑ ከፍ ያለ prostate ምክንያት ሊመጣ ይችላል። 
  • የበሽታ መከላከያ ስርአት መጎዳት፦ ለምሳሌ በስኳር በሽታ ምክንያት – ተፈጥሮአዊው በሽታ መከላከያ ብቃት እንዲቀንስና ጀርሞችን እንዳንከላከል በማድረግ ለኢንፌክሽኑ ተጋላጭ እንድንሆን ያደርጋል። 
  • አርቴፊሻል የሽንት ቱቦ (ካቴተር )የሚጠቀሙ ህመምተኖች
  • የሽንት ፊኛ ፣ ፕሮስቴት ወይም የኩላሊት ቀዶ ጥገና ያደረጉ ሰዎች ለ ሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን የበለጠ ተጋላጭ ናቸው 

የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ከበረታ ምን አይነት ችግር ሊያመጣ ይችላል ? የከፋ ችግር (complications)

የታችኛው የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን በአግባቡና በጊዜ ከታከመ ለክፉ አይሰጥም። ካልታከመ ግን ከባድ የጤና ችግር ሊያስከትል ይችላል። እነዚህም

  • ተደጋጋሚ ኢንፌክሽኖች
  • ከፍተኛ የሆነ የኩላሊት ኢንፌክሽን እና መዳከም 
  • ነፍሰጡሮች ላይ ከተከሰተ ደግሞ  የሚወለደው ህጻን መጠኑ ከሚገባው ያነሰ ወይም ያለጊዜው ሊወለድ ይችላል።
  • Sepsis, ለህይወት አስጊ የሆነ እስከ ሞት ሊያደርስ የሚችል ኢንፌክሽን ነው፤ በተለይ ወደ ኩላሊት የሚዛመት ከሆነ። 

ታድያ የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን መከላከያ መንገዶች ምንድናቸው 

  • በቂ ውሃ መጠጣት። ውሃ መጠጣት ሽንትን ይበርዛል፤ እንዲሁም ቶሎ ቶሎ እንድንሸና በማድረግ ባክቴሪያው ኢንፌክሽን ሳያመጣ  ከሽንት ቧንቧ እንዲወርድ ያረጋል።
  • ሽንት ከሸናን በኋላ ከፊት ወደ ኋላ መጠረግ፦ ከተጸዳዳን በሁላ ከፊት ወደ ኋላ መጥረግ ባክቴሪያዎች ከመቀመጫ አካባቢ ወደ ብልት እንዳይሄድ ያደርጋል።
  • ከግብረ ስጋ ግንኙነት በኋላ የሽንት ቧንቧ አከባቢን ማጽዳት፤ እንዲሁም አንድ ብርጭቆ ውሃ በመጠጣት ባክቴሪያው እንዲወገድ ማድረግ 
  • የሴቶች የተለያዩ  የብልት ማጽጃዎች እንደ ዴወደራንት ፓውደር እና douches አለመጠቀም። እነዚህ አይነት ማፅጃዎች ባክቴሪያ ወደ ሽንት ቧንቧ እንዲገባ እድል ይፈጥራሉ
  • የወሊድ መከላከያ መንገዶችን መቀየር ካለብዎት ከ ሐኪምዎ ጋር ይማከሩ ፣ በተለይ ተደጋጋሚ የሽንት ቧንቧ  ኢንፌክሽን የሚያጠቃዎት ከሆነ። እንደ ዲያፍራም (Diaphragm) ወይም spermicide-treated ኮንደሞች ለባክቴሪያ እድገት አስተዋጾ አላቸው። 
  • በጊዜ ሐኪምዎን ያማክሩ ፣ መድሃኒት ከታዘዘሎት በአግባቡ ይውሰዱ ።

 ምንጭ  Mayo Clinic 

የጤና ወግ

በመረጃ የተመሰረተ ሕክምና ብቻ ።  

………………………………………………………………………………………………………………………..

ይህ የጤና ወግ ድረ ገፅ ነው።
ስለ ጤንነታችሁ ማወቅ የምትፈልጉትን መረጃ የምታገኙበት ፣ በህክምና ባለሙያዎች የሚዘጋጅ የመረጃ ምንጭ ነው።
ሁልግዜም ከሀኪማችሁ ተማከሩ፣ ተጨማሪ መረጃ ከፈለጋችሁ የኛን ድረ ገፅ ጎብኙ።

በጥናት የተደገፈ መረጃ ብቻ እናቀርባለን።

የህክምና ባለሙያዎች ለህሙማኖቻችሁ የሚሆን የሚነበብ መረጃ ከፈለጋችሁ ይህን ግፅ ጠቁሟቸው። ህሙማኖቻችሁ እንዲያውቁት የምትፈልጉትን ነገር መረጃ ጠቅሳችሁ ፃፉልን፣ ስምችሁን ጠቅሰን እናወጣለን። የህክምና ተማሪዎች እንዲጽፉ እናበረታታለን።

በተጨማሪም በጤና ወግ ፖድካስት፣  በ ዩትዩብ ፣በ ትዊተር ፣ በ ፌስቡክ ፣ በቴሌግራም የተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ ገፆቻችን ታገኙናላችሁ