By. Elsa Wolde ( Medical Student- Clinical year three-AAU)
ከእርግዝና ጋር ተያይዞ የሚመጣ የደም ግፊት መጨመር ወይም በእንግሊዘኛው ፕሪኤክላምሲያ በእርግዝና እና በወሊድ ወቅት ለሚከሰቱ የእናቶች እና የልጆች ስቃይ እንዲሁም ሞት ዋና ምክንያቶች ከሆኑት መካከል የሚጠቀስ ነው።
ፕሪኤክላምሲያ ማለት እርግዝናው ቢያንስ ሀያ ሳምንት ከሞላው በኋላ የሚመጣ የደም ግፊት መጨመር እና በሽንት ውስጥ ያለው የፕሮቲን መጠን ከበፊቱ ከፍ ሲል ማለት ነው።
በሽታው በማንኛውም እርግዝና ላይ ሊከሰት የሚችል ሲሆን ተጋላጭነትን ከሚጨምሩት መካከል:-
– እድሜ – ከ 20 አመት በታች ወይም ከ35 አመት በላይ
– የመጀመሪያ ጊዜ እርግዝና
– ሁለት ወይም ከዚያ በላይ ልጆችን በአንድ ጊዜ ማርገዝ
– አዲስ የግብረ ስጋ ግንኙነት ጋደኛ አጋር
– ከዚህ በፊት የተጓዳኝ በሽታዎች መኖር: የስኳር በሽታ፣ የኩላሊት በሽታ፣ ከመጠን በላይ የሆነ ውፍረት፣ የደም ግፊት
– ከዚህ በፊት በሽታው የተጠቃ ሰው በቤተሰብ መሀል መኖር
–ከዚህ በፊት በበሽታው መያዝ
– ከዚህ በፊት ያልተሳካ እርግዝና መኖር ዋነኞቹ ናቸው።
ይህ በሽታ እንደ ልብ፣ ሳንባ፣ ኩላሊት፣ አእምሮ እና አይንን ሊያጠቃ ይችላል።
ምልክቶቹም
የበሽታው ደረጃ ቀላል ከሆነ ምንም አይነት ምልክቶች ላይታዩ ይችላሉ። ነገር ግን በሽታው በቀላሉ ሊባባስ የሚችል እና የእናት እና የልጅን ጤና ሊያስተጓጉል ባስ ካለም ለሞት ሊዳርግ የሚችል ነው።
ዋና ዋና ምልክቶቹም:
– ቋሚ የሆነ ወይም ከሌላ ጊዜው የባሰ የራስ ምታት
– እይታ ላይ ብዥ ማለት፣ ጊዜያዊ የሆነ የእይታ መጋረድ ወይም ብርሀን መጥላት
– የላይኛው በቀኝ በኩል ያለው የሆድ ክፍል ህመም፣
– ግራ የመጋባት ስሜት
– አዲስ የሆነ የትንፋሽ ማጠር ዋነኞቹ ናቸው።
በህክምና ማእከል ተገቢውን የእርግዝና ክትትል ማድረግ በሽታው በቀላሉ እንዲታወቅና ተገቢው እርምጃ በቀላሉ እንዲወሰድ ለማድረግ ወሳኝ ሚና ይጫወታል።
በተጨማሪም ደግሞ ከላይ የተጠቀሱትን ምልክቶች ሲታዩ የበሽታውን መባባስ የሚጠቁሙ በመሆናቸው በአፋጣኝ ወደ የህክምና ማእከል በመሄድ እርዳታ ማግኘት አስፈላጊ ነው።
ምንጮች:
- https://www.uptodate.com/contents/preeclampsia-clinical-features-and-diagnosis
- Current Diagnosis & Treatment Obstetrics & Gynecology, 11th Edition
ይሄ አስተማሪ የህክምና ፅሁፍ የቀረበው የጤና ወግ እና የ ኢትዮጵያ ሕክምና ተማሪዎች ማህበር ባዘጋጁት የህክምና ተማሪዎችን የመረጃ አስበሰብ እና ህብረተሰቡን የማስተማር አቅማቸውን ለማዳበር ለታለመ የበጎ ፍቃድ ውድድር ነው። እያንዳንዱ ፅሁፍ በዘርፉ ባለሙያ ስፔሺያሊስት ሀኪም የታየ እና እርማት ተደርጎበት የቀረበ ነው ።