በ ፍስሀ ሙሉጌታ (2nd Year Medical Student- Myungsung Medical College)

1.1 መግብያ 

ዕጢ(Tumor) ማለት የሕዋሳት ስብስብ ማለት ነው ፡፡ ይህ ማለት ጤናማ ያልሆነ (በአጠቃላይ ጉዳት 

የሌለው) ወይም አደገኛ (ካንሰር) እድገትን ሊያመለክት የሚችል አጠቃላይ ቃል ነው ፡፡ 

የጡት ካንሰር ማለት በጡት ሕብረ ሕዋሳት ውስጥ የህዋሳት ቁጥር በማያስፈልግ መጠን እና ሁኔታ 

መራባት ነው ፡፡ ባደጉት ሀገራት ውስጥ ከ 2/3 ኛ በላይ የጡት ካንሰር ከ50 እና ከዚያ በላይ ዕድሜ የሆኑ ሴቶችን  ይጠቃል ። በተቃራኒው ኢትዮጵያ ውስጥ በተሰ ራ ጥናት ከ 70% በላይ የሚሆኑት የጡት ካንሰር ታማሚዎች ዕድሜያቸው ከ 50 ዓመት በታች መሆኑን በጥናት ታይቷል  ፡፡ የሱዳን (74%) ፣ ሊቢያ (71%) ፣ እና ጋና (54.2%) ከ50 አመት በታች ነው። 

የጡት ካንሰር በዓለም ዙሪያ ላሉ ሴቶች ለእጅግ በጣም ብዙ ህመም እና  ሞት ምክንያት ነው፡፡ የተለያዩ ሰዎች የተለያዩ የጡት ካንሰር ምልክቶች ያሳያሉ፡፡ አንዳንድ ሰዎች በሽታው እስኪፋፋ ድረስ  በጭራሽ ምንም ምልክቶች ላያሳዩ ይችላሉ  ፡፡  

በጡት ካንሰር ብዙ ጊዜ ሴቶች ቢጠቁም ወንዶችም አንዳንድ ጊዜ በበሽታው ሊያዙ ይችላሉ። 

1.2 የጡት ካንሰር ምልክቶች 

• በጡት ውስጥ ወይም ብብት ስር እብጠት፡፡ 

• የጡት የተወሰነ ክፍል ውፍረት ወይም እብጠት። 

• በጡት ጫፍ አካባቢ ህመም ፡፡ 

• በእርግዝና እና በማጥባት ወቅት ካልሆነ በስተቀር ከ ጡት ጫፍ የሚታይ ፍሳሽ (ደምን ጨምሮ) ።

• በአንዱ ወይም በሁለቱም የጡት ጫፎች መልክ (ቅርፅ) ለውጦች ፡፡ 

• የ ጡት ቀለም  መለወጥ፡፡ 

• በአጭር ጊዜ ውስጥ የጡት መጠን ወይም ቅርፅ መጨመር 

• የጡት ጫፍ ቆዳ መጎጥጎጥ  ወይም ወደ ውስጥ መግባት 

• የጡት ቆዳ መቅላት ወይም መላጥ (ልክ እንደ ብርቱካን ቆዳ) 

እንደነዚህ ያሉትን ምልክቶች ካዩ በአቅራቢያዎ ወደሚገኝ ሆስፒታል ይጎብኙ፡፡ 

1.3 በጡት ካንሰር የመያዝ መንስኤ (Risk factors) 

የሚከተሉት የጡት ካንሰርን የመያዝ እድልን ይጨምራሉ፡- 

•ሴቶች- የጡት ካንስር በአብዛኛውን ጊዜ ሴቶችን ያጠቃል።  ግን ወንዶችንም በበሽታው ሊያዙ ይችላሉ።

•እድሜ፡- የጡት ካንሰር የመያዝ እድል ከእድሜ ጋር ይጨምራል ፡፡ አብዛኛውን ጊዜ የጡት ካንሰር

ከ 50 ዓመት እድሜ በኋላ ይመጣል። 

•አንዳድ በዘር ውስጥ የሚመጡ የዘረመል ለውጦች (ሚውቴሽን) ፡-እነዚህን የዘር ለውጦች የወረሱ ሴቶች በከፍተኛ መልኩ የጡት እና የማህጸን ካንሰር የመያዝ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው ፡፡ 

ከወለዱ በኋላ ጡት አለማጥባት፡፡ 

ከ 12 ዓመት እድሜ በፊት የወር አበባ መምጣት እና ከ 55 ዓመት እድሜ በኋላ የወር አበባ ዘግየቶ መቆም ሴቶችን በሆርሞኖች ረዘም ላለ ጊዜ ያጋልጣሉ፡፡ ይህም የጡት ካንሰር የመያዝ ዕድልን  ከፍ 

ያደርገዋል ፡፡ 

ጥቅጥቅ ወይም ወፋፍራም ያሉ ጡቶች ካሉዎት ፡፡ ጥቅጥቅ ያሉ ጡቶች ብዙ ሕብረ ሕዋሳት አላቸው ፣ ይሄም በጡት ካንሰር የመጋለጥ እድላችንን ከፍ ያደርገዋል። በተጨማሪም ከእንደዚህ አይነት ጡቶች አንዳንድ ጊዜ ዕጢዎችን በማሞግራም ላይ ማየት ከባድ ያደርገዋል ፡፡ 

የጡት ካንሰር ከዚህ በፊት የተያዙ ወይም የተወሰኑ ካንሰር ያልሆኑ የጡት በሽታዎች ያጋጠማቸው ሴቶች ለሁለተኛ ጊዜ የጡት ካንሰር የመያዝ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው፡፡ 

የጡት ካንሰር የቤተሰብ ታሪክ፡- የመጀመሪያ-ደረጃ ዘመድ (አባት፣ እናት ፣ ወንድም፣ እህት ወይም ልጅ) 

በጡት ካንሰር ተይዘው የሚያውቁ ከሆነ በጡት ካንሰር የመያዝ ዕድሎ ይጨምራል፡፡ 

ከ 30 ዓመት ዕድሜ በፊት በደረት ላይ ወይም በጡት ላይ የጨረር ሕክምና የነበራቸው (እንደ ሆጅኪ ንስ ሊምፎማ ሕክምና ያሉ) በጡት ካንሰር የመያዝ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው ፡፡ 

የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እጥረት እና ከአቅም በላይ ውፍረት። 

ሆርሞኖችን መውሰድ– የወር አበባ ከቆመ በኋላ የሚወሰዱ ሆርሞኖች (ኤስትሮጅንና ፕሮጄስትሮን 

የተባሉትን) ከአምስት ዓመት በላይ ሲወሰድ ለጡት ካንሰር የመያዝ እድልን ከፍ ያደርጋሉ ፡፡ 

የመጀመሪያ እርግዝና ከ 30 ዓመት እድሜ በኋላ ከሆነ  እና ሙሉ ጊዜ(9 ወር) ሳይጨርሱ መውለድ የጡት  ካንሰርን የመያዝ ዕድልን ከፍ ሊያደርጉ ይችላሉ ፡፡ 

አልኮል መጠጣት፡- ጥናቶች እንደሚያመለክቱት አንዲት ሴት ለጡት ካንሰር የመጋለጥ እድሏ 

በምጠጣው አልኮል መጠጥ መጠን ይጨምራል ፡፡ 

አንዳንዶች የወሊድ መቆጣጠሪያ መድሀኒት የጡት ካንሰርን የመያዝ እድልን ከፍ ያደርጋል ይላሉ ነገር ግን 

የመውለድ እድሜያቸው ያላበቃ ሴቶችን አያጠቃልልም፡፡ ተጨማሪ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በአፍ 

የሚወሰድ የወሊድ መከላከያ የማህፀን ካንሰር የመያዝ እድልን ይቀንሳል ፡፡ 

በ ጡት ካንሰር የተያዘ የመጀመሪያ ደረጃ ዘመድ(አባት፣ እናት ፣ ወንድም፣ እህት ወይም ልጅ)  ካለዎት  ወይም በዚህ ጽሑፍ ላይ ከተዘረዘሩት ምልክቶች መካከል አንዱን ወይም ከዚያ በላይ ከተመለከቱ ሃኪምዎ  ጋር ይሂዱ፡፡

እነዚህ ምልክቶች ሲኖሩዎት የጡት ካንሰር አለብዎት ማለት አይደለም ነገር ግን ወደ ሐኪም በመሄድ ማረጋገጥ ያስፈልጋል ፡፡ 

1.4 የጡት ካንሰር ምርመራ 

ማሞግራም የጡት ራጅ(x-ray) ነው ፡፡ማሞግራም ምንም ምልክት በሌላቸው ሰዎች ውስጥ በሽታን 

ለማግኘት የሚያገለግል መሳርያ ነው፡፡ በአሜሪካ ካንሰር ማህበረሰብ መሠረት “ከ 40 እስከ 44 ዓመት 

ዕድሜ ያላቸው ሴቶች አመታዊ የማሞግራም ምርመራ ማድረግ ይችላሉ (ግዴታ አይደለም)፡፡ ከ 45 እስከ 

54 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ሴቶች ግን በየአመቱ ማሞግራም መነሳት አለባቸው ፡፡ ዕድሜያቸው ከ 55 

ዓመት እና ከዚያ በላይ የሆኑ ሴቶች በየ2 ዓመቱ ማሞሞግራም መነሳት አለባቸው ወይም በየዓመቱ 

ምርመራውን የመቀጠል ምርጫ አላቸው ፡፡ 

ክሊኒካዊ ( በአካላዊ ምርመራ እና ክትትል ብቻ ) -ማሞግራም መሳርያን ባለመጠቀም  የጡት 

ምርመራ በማንኛውም ዕድሜ ላይ ላሉ እና በአማካኝ ተጋላጭ ናቸው ተብለው ለሚታስቡ ሴቶች የጡት 

ካንሰርን ምርመራ ለማካሄድ አይመከርም፡፡”  ምንጭ American Cancer Society

1.5 የወንድ የጡት ካንሰር 

የወንድ የጡት ካንሰር እንደ ሴቶች የተለመደ ስላልሆነ በሽታው ከፍ ያለ ደረጃ እስኪደርስ ላይታወቅ ይችላል ። በዚያን ጊዜ ካንሰር ቀድሞውኑ ተሰራጭቶ ሊሆን ይችላል ፡፡ ስለዚህ ይህንን ጽሑፍ የሚያነቡ ወንዶች በጡት ጫፍ ወይም በጡት አካባቢ እብጠት ቢያገኙ እና በዚህ ጽሑፍ ላይ የተጻፉ ሌሎች 

ምልክቶችንም ቢመለከቱ ወዲያውኑ ወደ ሐኪም ሄዶ ምርመራውን እንዲያካሂዱ ይመከራል ፡፡ 

1.6 የጡት ካንሰር ሕክምና 

ለጡት ካንሰር ሕክምናዎች ዋነኞቹ ሕክምናዎች በካንሰር ደረጃ ላይ በመመርኮዝ የቀዶ ጥገና ፣ ኬሞቴራፒ 

፣ ሆርሞናዊ ቴራፒ እና ራዲዮቴራፒ ናቸው ፡፡ የቀዶ ጥገናው ካንሰሩን ሙሉ በሙሉ ማውጣት ወይም ሙሉውን ጡት መቆረጥ ሊያካትት ይችላል። ከዚያ በኋላ  አንዳንድ ሰዎች ተጨማሪ ኬሞ እና ራዲዮቴራፒ ያስፈልጋቸዋል ፡፡ 

የኬሞቴራፒ ሕክምናው እንደ ጡት ካንሰሩ አይነት እና ደረጃ የሚወሰን ነው። የኬሞቴራፒ መድኃኒቶች የበሽታውን መስፋፍት የሚከላከሉ እና ተመልሶ እንዳይመጣ የሚያረጉ መድኃኒቶች ሲሆኑ እንደ አይነታቸው የተለያዩ የጎንዮሽ ጉዳቶች አላቸው። ሕክምናውን ከመጀምርዎ በፊት ሐኪምዎ የመድሃንቶቹን አወሳሰድ ፣ ጥቅም እና የሚያስከትሉትን ጉዳቶች ዘርዝሮ ያስረዳዎታል። 

1.7 ማጠቃለያ 

የጡት ካንሰር በዓለም ላይ በ ብዛት ከሚከሰቱ እና ሴቶች ላይ ሞትን ከሚያስከትሉ ህመሞች አንዱ ነው።  በሽታውን አስቀድሞ  ለመከላከል እና ከታወቀም በኃላ የሚያመጣውን ጉዳት ለመቀነስ ስለ ህመሙ ማወቅና እና መረዳት ያስፈልጋል ።

 ኢትዮጵያ እያደገች ስትመጣ ይህንን በሽታ በበቂ ሁኔታ ለማከም በሁሉም ክልሎች ውስጥ 

ማዕከላት ይኖራሉ የሚል እምነት አለኝ ፡፡ ነገር ግን እስከዛ ድረስ እራሳችንን ከበሽታው እንጠብቅ፡፡ ጡት 

በማጥባት፣ በአካል ብቃት እንቅስቃሴ፣ ክብደታችንን በመቆጣጠር ፣ ተገቢ የሆነ መደበኛ የ ሕክምና ክትትል በማድረግ ለጡት ካንሰር የሚያጋልጡንን ጠንቆች በተወሰነ መልኩ መቀነስ እንችላለን።

Reviewed and Edited by Yetenaweg