የምጥ መሠናከል (Obstructed Labor)
በሀገራችን አዘውትረን ከምንሰማቸው የእናቶች ስቃይ እና ሞት ምክንያት አንዱና ዋነኛው በወሊድ ወቅት የሚፈጠር ችግር ሲሆን ለዚህም በምክንያትነት ከሚጠቀሱት አንዱ እስከ ቀናት የሚደርስ የምጥ ጊዜ መርዘም ነው፡፡ ለምጥ መርዘም ደግሞ የምጥ መሠናከል በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡
አብዛኛውን ጊዜ የሚከሰተው ያላደጉ እና አዳጊ ሃገራት ላይ ሲሆን ከአጠቃላይ ወሊዶች እስከ 8% የሚደርሱት የምጥ መሠናከል ያጋጥማቸዋል፡፡
የምጥ መሠናከል ምንድን ነው?
መሠረታዊ ሀሣቡን በቀላሉ ለመረዳት የሚወለደው ፅንስ እና የሚያልፍበት የማህፀን ክፍል አካላዊ አለመመጣጠን ሲከሰት የምጥ መሠናከል እንለዋለን፡፡ ተገቢውን መፍትሔ እስኪያገኝ ድረስም የምጥ ጊዜ መራዘምን ያመጣል፡፡
አንድ የተረገዘ ፅንስ ሲወለድ በምጥ ወቅት የሚከተሉት ሁኔታዎች በተያያዘ መልክ የውልደት ሂደቱን ያሳኩታል፡
1– በቂ የሆነ የማህፀን መኮማተር እና በምጥ ወቅት እናት ፅንሱን የምትገፋበት ሃይል
2– የተገፋው ፅንስ የሚያልፍበት ምቹ የማህፀን ክፍል፣ የዳሌ አጥንት እና በዙሪያው የሚገኙ አካላት
3– የፅንሱ ስፋት፣ ክብደት፣ ተፈጥሯዊ ቅርፅ፣ የማህፀን ውስጥ አቀማመጥ እና አቀራረብ
በተሰናከለ ምጥ ወቅት ከላይ ከተጠቀሱት ውስጥ (1) በበቂ ሁኔታ እያለ (2) ወይም (3) ላይ በተናጠል ወይም ተደራራቢ የሆኑ የተለያዩ እክሎችን እናገኛለን፡፡ ይህም ማለት ለውልደቱ እንቅፋት የሆነው የማህፀን መኮማተር እና ግፊት ሣይሆን በፅንስ እና ማህፀን ላይ የሚኖሩ አካላዊ አለመመጣጠኖች ናቸው፡፡
ምክንያቶቹስ?
ቀጥተኛ፡ በእናት እና ፅንስ ላይ ያሉትን ቀጥተኛ እክሎች በምክንያትነት ለማየት ለሁለት እንከፍላቸዋልን፡ የእናት አካላዊ እክሎች እና የፅንስ አካላዊ እክሎች
የእናት አካላዊ እክሎች
- ያልተለመደ ቅርፅ ያለው ወይም ጠባብ የዳሌ አጥንት
- የዳሌ አጥንት እጢዎች
- በማህፀን እና ተያያዥ አካላት ላይ የሚወጡ እጢዎች
- የማህፀን ወይም ተያያዥ አካላት ተፈጥሯዊ ቅርፅ መዛባት
የፅንስ አካላዊ እክሎች
- በማህፀን ውስጥ አመቺ ያልሆነ አቀማመጥ እና አቀራረብ
- መጠን ያለፈ ክብደት እና ስፋት
- ሁለት (መንታ) እና ከዚያ በላይ ፅንስ
- የተቆላለፉ ወይም የተጣበቁ መንታዎች
- ተፈጥሯዊ ወይም በሽታን ተከትሎ የሚመጣ ቅርፅ መዛባት
ተዘዋዋሪ፡
አብዛኛው ህብረተሰባችን ውስጥ ያለው የገንዘብ እጥረት፣ የግንዛቤ አለመኖር እና ወደ ጤና ማዕከል ለመሔድ የሚጠቅሙ የትራንስፖርት እና የመንገድ ችግር አሁን ካለን ሁሉን ያላዳረሰ የጤና ሥርዓት ጋር በመደመር እናቶች በእርግዝና እና በወሊድ ወቅት ተገቢውን ሕክምና እንዳያገኙ በማድረግ እንደ ምጥ መሠናከል ላሉ እና ተከትለው ለሚመጡ የጤና እክሎች ምክንያት ይሆናሉ፡፡
የምጥ መሠናከል ምልክቶች
- 24 ሠዓት ያለፈ ረጅም ምጥ
- የሽል ውሃ መፍሰስን ተከትሎ የምጥ መዘግየት
- ከማህፀን የሚወጣ መጥፎ ሽታ ያለው ፈሳሽ
- ቶሎ ቶሎ እየመጣ የሚጠፋ ጠንካራ ምጥ
- ምጥን ተከትሎ የሚመጣ የማህፀን ደም መፍሰስ
- ትኩሳት፣ ፍፁም ድካም ፣ የህመም ስሜት እና የእንቅልፍ እጦት
የምጥ መሠናከል ለምን ይዳርጋል?
ተገቢውን ክትትል እና ህክምና ካገኘ በቀላሉ መፍትሔ ማግኘት የሚችል እክል ነው፡፡ ነገር ግን ያለ ህክምና እናትንም የሚወለደውንም ፅንስ እስከሞት ለሚያደርሱ የተለያዩ ሁኔታዎች ይዳርጋል፡፡ እነሡንም ለሁለት ከፍለን እናያለን፡ እናት እና ፅንስ ላይ፡
እናት
- ኢንፌክሽን
- ድህረ-ወሊድ ደም መፍሰስ እና ደም ማነስ
- የመራቢያ አካላት እና የሽንት ፊኛ መጎዳት
- የነርቭ በሽታ
- የማህፀን ግድግዳ መሰንጠቅ
- መሃንነት
- ፊስቱላ (ሽንትና ሠገራን አለመቆጣጠር)
- ሥነልቦናዊ ጉዳት
ፅንስ
- መታፈን
- ኢንፌክሽን
- ጭንቅላት ውስጥ ደም መፍሰስ
- የነርቭ በሽታ
- አካል ጉዳት
የምጥ መሠናከል ለማስወገድ የሚደረጉ ቅድመ-ጥንቃቄዎች እና መፍትሔዎቹ
- ተገቢውን የቅድመ-ወሊድ፣ ወሊድ እና ድህረ-ወሊድ ክትትል በጤና ተቋም ማድረግ
- የቤት ውስጥ ወሊድን ማስቀረት
- በቂ የሆነ ዕውቀት እና ልምድ ወደሌላቸው አዋላጆች አለመሄድ
- የስነ-ተዋልዶ ዕውቀት እና ግንዛቤን መፍጠር (የወሊድ መቆጣጠሪያ ዘዴዎች፣ ያለዕድሜ ጋብቻ…)
- ሴት ልጆች አድገው ለዚህ አካላዊ እክል እንዳይዳረጉ የተመጣጠነ ምግብ መስጠት
- የጤና ተቋማትን በበቂ ሁኔታ ማዳረስ እና የትራንስፖርት እና የመንገድ ችግሮችን መቅረፍ
የምጥ መሠናከልን ለማስወገድ የተጠቀሱትን ቅድመ-ጥንቃቄዎች ካደረግን እንዲሁም ተገቢውን ምክር እና ክብካቤ ከተገቢ እና ብቁ የጤና ባለሙያ ካገኘን እና ከተገበርን የተሳካ የወሊድ ሂደት እናገኛለን፡፡ ሳይሆን ቀርቶም ተያያዥ የሆኑ እክሎች ካጋጠሙን ጊዜ ሳንፈጅ አቅራቢያ በሚገኝ ጤና ተቋም በመሄድ ከቀላል ክትትል እስከ መፍትሔ ሠጪ ቀዶ ጥገና፣ ተገቢ ህክምና በተጨማሪም ለቀጣይ እርግዝና በቂ ግንዛቤ ማግኘት እንችላለን፡፡
ዋቢ / REFERENCES
- OBSTETRICS: NORMAL AND PROBLEM PREGNANCY, 7TH Edition, 2019
- CURRENT DIAGNOSIS TREATMENT OBSTETRICS AND GYNECOLOGY, 11TH Edition, 2013
- UpToDate 21.6
- AYDER’S OBSTETRIC AND GYNECOLOGY, 1ST Edition, 2020
MANAGEMENT PROTOCOL ON SELECTED OBSTETRIC TOPICS, FMOH, 2010 E.C.
ይሄ አስተማሪ የህክምና ፅሁፍ የቀረበው የጤና ወግ እና የ ኢትዮጵያ ሕክምና ተማሪዎች ማህበር ባዘጋጁት የህክምና ተማሪዎችን የመረጃ አስበሰብ እና ህብረተሰቡን የማስተማር አቅማቸውን ለማዳበር ለታለመ የበጎ ፍቃድ ውድድር ነው። እያንዳንዱ ፅሁፍ በ ጤና ወግ የታየ እና እርማት ተደርጎበት የቀረበ ነው ።