በዶ/ር ኤዶም ገ/መድህን (በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ህክምና እስፔሻላይዜሽን ሲኒየር ሬዚደንት)
በአሁኑ ወቅት በአለማችን ላይ ወደ 500 ሚሊዮን የሚጠጉ የስኳር ህመም ታማሚዎች ይገኛሉ፡፡ የስኳር ህመም ለረዥም አመታት ያለ በቂ ቁጥጥር በሚቆይበት ወቅት በተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ላይ የጎንዮሽ ጉዳቶችን ያመጣል፡፡ ከነዚህም መካከል በእግር ላይ የሚደርስ ቁስለት እና መበስበስ (Gangrene) በዋነኛነት ይጠቀሳሉ፡፡ ይህ ህመም በአፋጣኝ ህክምና ካልተደረገለት የስኳር ህመም ታካሚዎችን ለዘላቂ የአካል ጉዳት ብሎም ለሞት ሊዳርጋቸው ይችላል፡፡
የስኳር ህሙማንን ለእግር ቁስለትና መበስበስ (Gangrene) ከሚያጋጧቸው ሁኔታዎች መካከል በስኳር ህመም ምክንያት የሚከሰት የነርቭ ህመም እና የደም ስር መጥበብ በዋነኝነት ይጠቀሳሉ፡፡
በስኳር ህመም ምክንያት የሚከሰት የነርቭ ህመም ከእግሮቻችን የሚመጣውን የህመም ስሜት የማወቅ አቅም በመቀነስ እንዲሁም ከቆዳ የሚመነጭን የላብ መጠን በመቀነስና የእግር ቆዳን ለድርቀት በመዳረግ በቀላሉ ለቁስለት ተጋላጭ ያደርገናል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከነርቭ ህመሙ ጋር ተያይዞ በሚከሰተው የህመም ስሜትን አለማወቅና ሚዛንን ያለመጠበቅ ችግር በእግር አጥንቶች ላይ የአቀማመጥ መዛባት ስለሚያስከትል በእግሮቻችን ላይ ተደጋጋሚ የመቁሰል ጉዳት እንዲከሰት አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡
ከስኳር ህመም ጋር ተያይዞ የሚከሰት የደም ስር መጥበብ ወደ እግሮቻችን የሚሄደውን የደም ዝውውር በመቀነስ በእግር ላይ የሚከሰቱ ቁስለቶች ቶሎ እንዳይድኑ ከማድረጉም በተጨማሪ በተለያዩ ባክቴሪያና ፈንገስ ለሚከሰቱ ኢንፌክሽኖች ተጋላጭ ያደርጋል፡፡
ከላይ በተጠቀሱት ምክኒያቶች ከስኳር ህመም ጋር ተያይዘው በእግር ላይ የሚከሰቱ ቁስለትና ኢንፌክሽን ከቆዳ ወደ ውስጥ በመዝለቅ የእግር ጡንቻዎችንንና አጥንቶችን በመጉዳት ለእግር መበስበስና መቆረጥ ያጋልጣሉ፡፡
ከስኳር ህመም ጋር ተያይዞ የሚፈጠርን የእግር ቁስለት እንዴት መከላከል ይቻላል?
- በሃኪም የታዘዙ መድሃኒቶችን በአግባቡ በመውሰድ፣
- አመጋገብን በማስተካከልና የአካል ብቃት እንቅስቃሴን በማዘውተር በደም ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን መቆጣጠር
- እግሮቻችንን ለጉዳት የሚያጋልጡ ልማዶችን መቀነስና በየቀኑ የራስን እግር መመርመር። ይህንንም ለማሳካት የሚከተሉትን ጥንቃቄዎች መከተል እንችላለን፡-
- በባዶ እግር እንዲሁም ክፍት ጫማዎችን አድረጎ አለመንቀሳቀስ
- ምቾት ያላቸውንና ሰፊ የሆኑ ሽፍን ጫማዎችን ማድረግና ንፁህ የጥጥ ካልሲዎችን ማዘውተር
- ጫማ ከመደረጉ በፊት በጫማው ውስጥ ምቾት የሚነሱ ነገሮች አለመኖራቸውን ማረጋገጥ
- የእግር ጣት ጥፍሮችን አሳጥሮ መቁረጥ
- በየቀኑ በእግር ላይ የተከሰተ አዲስ ቁስለት፣ ወይም እብጠት መኖር አለመኖሩን መመርመር (ለእይታ የማያመች ቦታ ከሆነ ይህንን መስታወት ወይም የቤተሰብ እርዳታ በመጠቀም ማከናወን ይቻላል፡፡)
- በየቀኑ እግርን በሳሙናና በቀዝቃዛ ወይም ለብ ባለውሃ መታጠብ፣ ከታጠቡ በኃላም እግርን በተለይም በጣቶች መካከል ያለውን ቦታ በንፁህ ፎጣ ማድረቅ
- የእግር ቆዳ እንዳይደርቅ የተለያዩ ቅባቶችን መቀባት
- በእግር ላይ ቁስለት ከታየ በአፋጣኝ ወደጤና ተቋም በመሄድ የህክምና እርዳታን ማግኘት እንዲሁም በየአመቱ በሀኪም የሚደረግ የእግር ምርመራን መከታተል
- በተለይም በእግር ላይ የሚሰማ የመጠዝጠዝ፣ የማቃጠል ወይም የመደንዘዝ ስሜት ከተሰማዎት፤ አልያም የእግር መቀዝቀዝ፣ መጥቆር ወይም በእንቅስቃሴ ጊዜ የሚሰማዎት ህመም ካለ ለሃኪሞ በቶሎ ማሳወቅ ያስፈልጋል።
- ሲጋራ ማጨስ ለደም ስር መጥበብና የደም ዝውውር መቀነስ ስለሚያጋልጥ ሲጋራ አለማጨስ በጥብቅ ይመከራል፡፡
- ለደም ግፊት ፣ ለልብ ወይም የኩላሊት ተጒዳኝ ህመሞች ተገቢውን ህክምና ማድረግ እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው።