የህመም ማስታገሻ መድሃኒቶች ህመምን በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ ጥቅም ቢኖራቸውም የራሳቸው የሆነ የጎንዮሽ ችግር እንዳላችው በመገንዘብ አጠቃቀም ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ህመም ማስታገሻ መድሃኒቶችን በከፍተኛ መጠን እና ለረጅም ግዜ መጠቀም የኩላሊት ችግር ሊያስከትል ይችላል፡፡ አብዛኛዎቹ የህመም ማስታገሻ መድሃኒቶች በባህሪያቸው ወደ ኩላሊት የሚሄደውን ደም መጠን ስለሚቀንሱ በተለይ የኩላሊት ስራ መቀነስ ችግር ያለባቸው ሰዎች የህመም ማስታገሻ መድሃኒቶችን ባይወስዱ ወይንም ሃኪም በሚያዘው መጠን ልክ ብቻ እንዲወስዱ ይመከራል፡፡
ከህመም ማስታገሻ መድሃኒቶች ጋር ተያይዞ የሚከሰት የኩላሊት ችግርን ቅድመ ጥንቃቄ በማድረግ መከላከል ይቻላል፡፡
የህመም ማስታገሻ መድሃኒቶች የምንላቸው መድሃኒቶች የትኞቹ ናቸው?
የህመም ማስታገሻ መድሃኒቶች ማለት ህመምን ትኩሳትን እና የሰውነት መቆጣትን ለመቀነስ የሚወሰዱ መድሃኒቶች ናቸው ፡፡ ከእነኚህ መድሃኒቶች ምሳሌ ለመጥቀስ ያህል ያለ ሃኪም ማዘዣ ከመድሃኒት ቤቶች በቀላሉ ልንገዛችው የምንችላችው እንደነ አስፕሪን ፤ ፓራሴታሞል(አሴታሚኖፌን)፤ አይቦፕሮፌን፤ ዳይክሎፌናክ የመሳሰሉትን ያካትታል፡፡
ከቅርብ ግዜ ወዲህ ደግሞ ወደ ገበያ እየመጡ ያሉ በአንድ እንክብል ሁለት እና ሶስት ህመም ማስታገሻዎችን የያዙ መድሃኒቶችንም ያካትታል፡፡ የህመም ማስታገሻ መድሃኒቶች ኩላሊትን ሊጎዱ ይችላሉ የኩላሊት ስራ መቀነስ ችግር ያለባቸው ሰዎች ማንኛውንም የህመም ማስታገሻ መድሃኒት ከመውሰዳችው በፊት ሃኪም ማማከር አለባቸው፡፡ ሁሉም ያለ ሃኪም ማዘዣ የሚገዙ የህመም ማስታገሻ መድሃኒቶች በከፍተኛ መጠን እና ለረጅም ግዜ ሲወሰዱ ኩላሊት ላይ ዘላቂ የሆነ ጥልቅ ጉዳት ሊያደርሱ ይችላሉ፡፡
አብዛኛዎቹን የህመም ማስታገሻ መድሃኒቶች ለህመም ማስታገሻነት ከአስር ቀናት እንዲሁም ለትኩሳት ከሶስት ቀናት በላይ ባይወሰዱ ይመከራል፡፡ ረዘም ያለ ግዜ የቆየ ህመምም ሆነ ትኩሳት ሲከሰት ሃኪም ማማከር እና ምርመራ ማድረግ ተገቢውን መፍትሄ ለማግኘት ይረዳል፡፡
ማንኛውም የኩላሊት ስራ መቀነስ ችግር ያለባቸው ሰዎች ከፍተኛ መጠን ያለው አስፕሪን ወይም NSAID ተብለው የሚመደቡ ህመም ማስታገሻ መድሃኒቶቸ ባይወስዱ ይመከራል፡፡ የኩላሊት ችግር የሌላቸውም ሰዎች ቢሆኑ ህመም ማስታገሻ መድሃኒቶቸን ሲጠቀሙ
- በሃኪም ትእዛዝ መሰረት ወይንም ከሚመከረው መጠን ሳያስበልጡ
- በአነስትኛው ተገቢ መጠን
- ለአነስተግኛ ተገቢ ግዜ ቢወስዱ ይመከራል፡፡
አስፕሪንን በመደበኛነት መውሰድ ጉዳት አለው?
የኩላሊት ችግር የሌላቸው ሰዎች በመደበኛነት አስፕሪንን በሃኪም ትእዛዝ መሰረት ቢወስዱ በኩላሊት ህመም የመያዝ እድልን አይጨምርም፤ ነገር ግን ከታዘዘው ወይም ከሚመከረው መጠን በላይ (በአብዛኛው በቀን ከ6 እስከ 8 እንክብሎች በላይ) አስፕሪን ሲወሰድ ለአጭር ግዜ ወይም ለዘለቄታው የኩላሊት ስራ መቀነስ ችግር ሊያስከትል ይችላል፡፡ የኩላሊት ስራ መቀነስ ችግር ፤ የጉበት ወይም የልብ ብሽታ ያላቸው ሰዎች ሃኪም ሳያማክሩ አስፕሪን ባይወስዱ ይመከራል፡፡
ሃኪም የልብ ችግርን ለመከላከል በየቀኑ የሚወሰድ አስፕሪን አዞልኛል፡ ይህ ኩላሊቴ ላይ ችግር ያስከትልብኝ ይሆን?
አያስከትልም፡፡ የልብ ችግርን ለመከላከል በየቀኑ የሚወሰድ አስፕሪን መጠን አነስተኛ ስለሆነ (81 እስከ 162mg) ኩላሊት ስራ መቀነስ ችግር ላለባቸውም ሆነ ለሌለባቸው ሰዎች ላይ ምንም አይነት ተጨማሪ ችግር አያስከትልም፡፡
የትኞቹ የህመም ማስታገሻዎች ናቸው ለኩላሊት ስራ መቀነስ ችግር ላለባቸው ሰዎች የሚፈቀዱት?
የኩላሊት ስራ መቀነስ ችግር ያለባቸው ሰዎች አሴታሚኖፌን (ፓራሴታሞል) የተባለው መድሃኒትን አልፎ አልፎ ለህመም ማስታገሻነት መጠቀም ይችላሉ፡፡ ነገር ግን እነኚህ የኩላሊት ስራ መቀነስ ችግር ላለባቸው ሰዎች በተደጋጋሚ ይህንን መድሃኒት መጠቀም ከፈለጉ ሃኪማቸውን ማማከር እንዲሁም የአልኮል መጠጥን አለመውሰድ ይኖርባቸዋል፡፡
NSAID ውስጥ የሚመደቡ መድሃኒቶች የትኞቹ ናቸው? ኩላሊት ላይስ ችግር ያስከትላሉ?
NSAID ውስጥ የሚመደቡ መድሃኒቶች እንደነ አይቦፕሮፌን፤ ዳይክሎፌናክ፡ ናፕሮክሴን የመሳሰሉት ናቸው፡፡ NSAID የተባሉትየህመም ማስታገሻ መድሃኒቶች አልፎ አልፎ ለህመም ማስታገሻነት መጠቀም በአብዛኛውችግር ባያስከትልም የኩላሊት ስራ መቀነስ ችግር ላለባቸው ሰዎች ባይወስዷቸው ይመከራል፡፡ እነኚህን መድሃኒቶች ለመውስድ የፈለጉ የኩላሊት፤የልብ ህመም ፤ ደም ግፊት ወይም ጉበት በሽታ ያላቸው ሰዎች እንዲሁም እድሜያቸው ከ65 አመት በላይ የሆነ ሰዎች በግዴታ ሃኪም ማማከር ይኖርባቸዋል፡፡ NSAID የተባሉትየህመም ማስታገሻ መድሃኒቶች ድንገተኛም ሆነ ቀስ በቀስ የሚከሰት የኩላሊት ስራ መቀነስ ችግር ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡
የመገጣጠሚያ ህመም አለኝ፤ ምን አይነት ኩላሊቴን ማይጎዳ ህመም ማስታገሻ መድሃኒቶችን ልውሰድ?
ሃኪሞትን አማክረው ለእርሶ የተሻለውን በጋራ ቢመርጡ ይመከራል፡፡ ተጨማሪ ህመሞች (ደም ግፊት፤ የኩላሊት፤የጉበት ወይም ልብ ህመም) ካሎት የህመም ማስታገሻ መድሃኒቶችን በሃኪምዎ ተእዛዝ እና የህክምና ክትትል እያደረጉ መጠቀም ይኖርቦታል፡፡
የህመም ማስታገሻ መድሃኒቶች በኩላሊቴ ላይ ጉዳት አድርሰው ከሆነ በምን ማወቅ እችላለሁ?
ሃኪም ጋር ሄደው በላቦራቶሪ የደም ምርመራ በማድረግ የኩላሊቶትን የጉዳት መጠን ለማወቅ ይችላሉ፡፡ ደም ምርመራውም ኩላሊትዎ በተገቢው መጠን በደም ውስጥ ያለ ቆሻሻን እያጣራ መሆን አለመሆኑን ማወቅም ያስችላል፡፡በተጨማሪም በሽንት ላይ ያለ የፕሮቲን መጠንን በመለካት በተዘዋዋሪ መንገድ የኩላሊትን ደህንነት ማወቅም ይቻላል፡፡
የአስፕሪን እና NSAID መድሃኒቶች ሌሎች ተጨማሪ የጎንዮሽ ችግሮች ምን ምን ናቸው?
ከአስፕሪን እና NSAID መድሃኒቶች የጎንዮሽ ችግሮች ዋና ዋናዎቹ ጭጓራ ቁስለት እና መድማትናችው፡፡ በተጨማሪም የድንገተኛ ወደ ልብ ወይም ወደ አንጎል የደም ፍሰት መቋረጥ እድልን ሊጨምር ይችላል፡፡
የኩላሊትን ጤንነት ለመጠበቅ ምን ማድረግ ያስፈልጋል?
ከህመም ማስታገሻ መድሃኒቶች ጋር ተያይዞ የሚከሰት የኩላሊት ችግር ቅድመ ጥንቃቄ በማድረግ መከላከል ይቻላል፡፡ ከዚህም በመቀጠል ማድረግ ከምንችላቸው ጥንቃቄዎች ጥቂቶቹ ተጠቅሰዋል፡፡
- ያለ ሃኪም ማዘዣ የሚገዙ የህመም ማስታገሻ መድሃኒቶችን ለህመም ማስታገሻነት ከአስር ቀናት እንዲሁም ለትኩሳት ከሶስት ቀናት በላይ አለመጠቀም፡፡
- ለረዘም ያለ ግዜ ህመምም ሆነ ትኩሳት ካሎት ወደ ሃኪም መሄድ፡፡
- በአንድ እንክብል ሁለት እና ሶስት ህመም ማስታገሻዎችን የያዙ መድሃኒቶችን (ለምሳሌ ያህል አስፕሪን አሴታሚኖፌን እና ካፌን ተቀላቅሎ በአንድ እንክብል) አለመውሰድ፡፡
- የህመም ማስታገሻ መድሃኒቶችን በሚወስዱበት ግዜ ብዙ ፈሳሽ መውሰድ፡፡ ( ከ ስድስት እስከ ስምንት ብርጭቆ ወይም እስከ ሁለት ሊትር በቀን)
- የህመም ማስታገሻ መድሃኒቶችን በሚወስዱበት ግዜ አልኮል መጠጥን አለመውሰድ፡፡
- የኩላሊት ስራ መቀነስ ችግር ካሎት ህመም ማስታገሻ መድሃኒቶችን በተለይም NSAID ወይም ከፍ ያለ መጠን ያለው አስፕሪን ከመውሰድዎ በፊት ሃኪሞትን ማማከር፡፡
- የኩላሊት፤የልብ ህመም ፤ ደም ግፊት ወይም ጉበት በሽታ ካሎት እንዲሁም እድሜዎት ከ65 አመት በላይ የሆነ ወይም ሽንት የሚያሸና መድሃኒት እየወሰዱ ከሆነ NSAID መደሃኒቶችን ከመውሰድዎ በፊት ሃኪሞን ማማከር
- ወደ ህክምና ቦታ ሲሄዱ የታወቀ ማንኛውምን ህመሞትን እንዲሁም የሚወስዷቸውን መድሃኒቶች ለጤና ባለመያው መግለጽ፡፡
- ያለ ሃኪም ማዘዣ የሚገዙ የህመም ማስታገሻ መድሃኒቶችን ሲጠቀሙ አብረው የሚያያዙትን የሚያያዙ የመረጃ ወረቀቶች በአጽኖት ማንበብ፡፡
በዶ/ር መታሰቢያ ወርቁ
ትዊተር : @DrMetiW
ከናሽናል ኪድኒ ፋውንዴሽን ገጽ ተወስዶ የተተረጎመ
Source : The National Kidney Foundation If you want to read the orginal article in English please click here.