በተስፋዬ ብርሃኑ (በጎንደር ዩ/ህ/ጤ/ሳ/ኮ የህክምና ተማሪ-C2)
መግቢያ
ሉፐስ ተላላፊ ያልሆነ የራስን መድኅን (በሽታ የመከላከል አቅም) የሚጎዳ የጤና እክል ሲሆን መንስኤው በውል አይታወቅም1፡፡ አንድ ሰው በዚህ ህመም በሚያዝበት ጊዜ በሽታ ተከላካይ ህዋሶቹ የራሱን የሰውነት ክፍሎች እንደ ባዕድ ቆጥረው ያጠቃሉ፡፡ ብዙ ሥርአተ-አካላትን ከማጥቃት ባህሪው አንጻር ምልክቱ፣ የቤተሙከራ ውጤቱ እና ግምታዊ ትንበያው (ፕሮግኖሲስ) የተለያየ ነው፡፡ በሽታው በሁሉም የእድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሰዎች ላይ ሊከሰት ቢችልም በአብዛኛው ጊዜ በመውለጃ የእድሜ ክልል (15-49) ውስጥ ያሉ ሴቶችን በተለይም ወጣቶችን (የሆርሞን ለውጥ መላምት) ያጠቃል2,3፡፡
የክስተትና የሥርጭት መጠን
ዓለምአቀፍ የበሽታው ስርጭት በዘረመል ልዩነት፣ ሥነሕዝባዊ ሁኔታ፣ ምጣኔሀብታዊና አካባቢያዊ ተጽእኖዎች የተነሣ የተለያየ ቢሆንም በአፍሪካ እና አውስትራሊያ በበሽታው አዲስ የሚያዙ ሆነ የተያዙ ሰዎች ስርጭት እምብዛም አይታወቅም፡፡ በዓለምአቀፍ ደረጃ የተሠራ ጥናት4 ከፍተኛው የበሽታው ክስተት (23.2/100,000) እና ስርጭት (241/100,000 ሰዎች-በዓመት) በሰሜን አሜሪካ መሆኑን ያሳያል፡፡ አነስተኛው የክስተት መጠን ከአፍሪካ እና ዩክሬን መሆኑን ሲገልጽ ዝቅተኛው የሥርጭት መጠን ከአዉስትራሊያ ተመዝግቧል፡፡ ሴቶች በሁሉም እድሜ እና ዘር ከወንዶች በበለጠ ተጠቂ ናቸው፡፡ ጥቁሮች (ወደ ምድር ወገብ በቀረብን ቁጥር ተጋላጭነት ይጨምራል) ከነጮች በበለጠ የበሽታው ክስተት እና ሥርጭት ያላቸው ሲሆን እንደ አጠቃላይ ግን የበሽታው ስርጭት በዓለምአቀፍ ደረጃ ከጊዜው ጋር አብሮ የመጨመር ዝንባሌ እያሳየ እንደሆነ በጥናቱ ተገልጿል፡፡
የበሽታው ምልክቶችና ውስብስብ ውጤቶቹ
የበሽታው አካሄድ የተለያየ ቢሆንም የድንገቴ ምልክቶች፣ የመባባስ እንዲሁም የማገገም ባህሪያት አሉት5፡፡ የመገጣጠሚያ ህመም፣ የቆዳ ሽፍታ (ፀሐይ ሲነካን)፣ የድካም ስሜት፣ የክብደት መቀነስ የተለመዱ ምልክቶቹ ሲሆኑ ክብ ቅርጽ ያለው ለምጽ፣ የኩላሊት መቆጣት፣ የልብ ማኅደር መቆጣት፣ እና የሚጥል በሽታ አንዳንድ ጊዜ ይከሰታሉ፡፡
በበሽታው የተጠቃን ሰው ለመመርመር በአሜሪካ ሪዩማቶሎጂ መካነ-ትምህርት መመዘኛ መስፈርት6 መሠረት ከ11ዱ ቢያንስ 4ቱን ምልክቶች ማሟላት አለበት፡፡ እነዚህም ምልክቶች የጉንጭ ሽፍታ፣ የቆዳ ለምጥ፣ ሳንባን/ልብን ከቦ የሚገኝ ንብርብር መቆጣት፣ የአፍ ቁስለት፣ የአንጓ ብግነት፣ ቆዳ ለፀሐይ ትብ መሆን፣ የደም ሕዋሳት መታወክ፣ የኩላሊት ሕመም፣ ፀረኒውክለስ ፀረባእድአካል በደም መገኘት፣ የመድኅን ችግር፣ የሥርአተ ነርቭ እክል ናቸው፡፡
የሕክምና አገልግሎት ለመሻት በሽታው ለብቻው 33% ያክል እንደ ምክንያት ሲጠቀስ የተቀሩት (66%) ህሙማን ከበሽታው ጋር ተያይዞ በሚከሰቱ ውስብስብ የጤና እክሎች ጤና ተቋምን ይጎበኛሉ7፡፡ እነዚህም ድንገት ብሶ የሚከሰት የመገጣጠሚያ ህመም፣ ኢንፌክሽን፣ የሳንባ መቆጣት፣ የልብ ሽፋን መቆጣት፣ የኩላሊት ህመም፣ ውርጃ ፣ ተጓዳኝ የመድኅን ችግር እና የአእምሮ ህመም ምልክቶች ዋነኞቹ ናቸው፡፡ በበሽታው የተጠቁ ሰዎች ካልተጠቁት ከ2-3 እጥፍ የመሞት እድል ሲኖራቸው ኢንፌክሽን፣ የልብና የደም ሥር በሽታዎች እንደ መንስኤ በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ4፡፡
ማጠቃለያ
ሉፐስ በሽታ በኢትዮጵያ ያለው የክስተት እና የሥርጭት መጠን በትክክል ባይታወቅም በምድር ወገብ አካባቢ እንደመገኘቷ የተጠቁ ሰዎች ከፍ ያለ የአሃዝ መጠን እንደሚኖራቸው አያጠያይቅም፡፡ ማኅበረሰቡም ሆነ የጤና ባለሙያው ስለ በሽታው ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛ መሆን፣ በሽታውን በምርመራ ለማወቅ የሚያስችል የጤና ተቋም ግብአት የተሟላ አለመሆን፣ እንዲሁም የስፔሻሊስት ሐኪሞች አናሳነት የበሽታውን ሥርጭትና ጫና ላለማወቃችን እንደ ምክንያት ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ በበሽታው የተጠቁ አብዛኞቹ ሰዎች የህክምና እርዳታ የሚሹት ውስብስብ የጤና እክሎችን ማስተዋል ሲጀምሩ በመሆኑ የሚሰጠውን ህክምና(ስቴሮይድ፣ ፀረ-ወባና ሌሎችም) ውጤታማነት ይቀንሳል፡፡ ስለሆነም በሽታው ወደ ከፋ ደረጃ ሳይሸጋገር በልየታና በምርመራ አረጋግጦ ህክምናውን ማግኘት ዘርፈብዙ ጥቅሙ የጎላ በመሆኑ ባለድርሻ አካላት ለበሽታው ትኩረት ሰጥተው የሚጠበቅባቸውን ያበረክቱ ዘንድ ለመጠቆም እፈልጋለሁ፡፡
ዋቢ ጥናታዊ ጽሑፎች:
- Mok CC, Lau CS. Pathogenesis of systemic lupus erythematosus. Journal of clinical pathology. 2003 Jul 1;56(7):481-90.
- Sube W, Mwamba P. Prevalence of systemic Lupus Erythematosus in Kentatta national hospital. East African Medical Journal. 2019;96(5).
- Rees F, Doherty M, Grainge MJ, Lanyon P, Zhang W. The worldwide incidence and prevalence of systemic lupus erythematosus: a systematic review of epidemiological studies. Rheumatology. 2017 Nov 1;56(11):1945-61.
- Barber MR, Drenkard C, Falasinnu T, Hoi A, Mak A, Kow NY, Svenungsson E, Peterson J, Clarke AE, Ramsey-Goldman R. Global epidemiology of systemic lupus erythematosus. Nature Reviews Rheumatology. 2021 Aug 3:1-8.
- Cojocaru M, Cojocaru IM, Silosi I, Vrabie CD. Manifestations of systemic lupus erythematosus. Maedica. 2011 Oct;6(4):330.
- Yu C, Gershwin ME, Chang C. Diagnostic criteria for systemic lupus erythematosus: a critical review. Journal of autoimmunity. 2014 Feb 1;48:10-3.
- Heller T, Ahmed M, Siddiqqi A, Wallrauch C, Bahlas S. Systemic lupus erythematosus in Saudi Arabia: morbidity and mortality in a multiethnic population. Lupus. 2007 Nov;16(11):908-14.
- Essouma M, Nkeck JR, Endomba FT, Bigna JJ, Singwe-Ngandeu M, Hachulla E. Systemic lupus erythematosus in Native sub-Saharan Africans: a systematic review and meta-analysis. Journal of autoimmunity. 2020 Jan 1;106:102348.
- Dubula, T., Mody, G.M. Spectrum of infections and outcome among hospitalized South Africans with systemic lupus erythematosus. Clin Rheumatol 34, 479–488 (2015). https://doi.org/10.1007/s10067-014-2847-0
- Gbané-Koné, M. , Ouattara, B. , Djaha, K. , Megne, E. , Ngandeu, A. , Coulibaly, A. , Eti, E. and Kouakou, M. (2015) Autoantibodies in Systemic Lupus Erythematosus, on Black African Subject, in Abidjan. Open Journal of Rheumatology and Autoimmune Diseases, 5, 28-35.
ይህ ፅሁፍ በዶ/ር ኤርሚያስ ካቻ (የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት/የሳምባና ፅኑ ህሙማን ሰብ ስፔሻሊስት) እና የጤና ወግ ኤዲተሮች የተገመገመ ነው።