በሁስኒያ አደም (ጎንደር ዩ/ህ/ጤ/ሳ/ኮ የህክምና ተማሪ-C2)

A mother with her newborn child at Dessie Referral Hospital in Afar region, Ethiopia. Save the Children staff refer girls and women with health problems from rural Amhara to the hospital and assist them in their journey there.

በእያንዳንዱ ቀን ከ2 ደቂቃ ባነሰ ጊዜ ውስጥ ማስቀረት በምንችላቸው ከእርግዝና እና ወሊድ ጋር በተያያዙ ምክንያቶች የሴት ልጅ ህይወት እንደሚያልፍ ያውቃሉን?

እ.ኤ.አ. በ2017 የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው 295,000 የሚሆኑ ሴቶች በእርግዝና እና ወሊድ ወቅት ህይወታቸው አልፏል። ከዚህም ውስጥ 94% የሚገኙት እያደጉ ባሉ ሀገራት ውስጥ ነው። ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሃገራት ውስጥ ብቻ 66% (196,000) የእናቶች ሞት ሲመዘገብ፣ ኢትዮጵያ 5% (14,000) ትይዛለች።

የእናቶች ሞት ማለት ምን ማለት ነው?

የእናቶች ሞት ማለት በእርግዝና ጊዜ ወይም ከወሊድ በኋላ በመጀመሪያ 42 ቀናቶች ውስጥ ከእርግዝናው ጋር ተያይዘው በሚመጡ የጤና ችግሮች ወይም በእርግዝናው ምክንያት ሊባባሱ በሚችሉ እና በህክምና አገልግሎት ችግር የሚከሰቱ የሴት ልጅ ሞት ማለት ነው።

በእርግዝና እና ወሊድ ጊዜ የሚከሰቱትን የጤና ችግሮች ለመቅረፍ የሚያስችሉ መፍትሄዎች በመኖራቸው አብዛኛውን የእናቶች ሞት መከላከል ይቻላል። በዋነኝነት ሁሉም የወሊድ አገልግሎት በትክክለኛ ጊዜ እንዲሁም ብቁ በሆኑ የጤና ባለሙያዎች መሰጠት አለበት። ይህም የአንድን እናት እንዲሁም የልጇን መኖር አለመኖር ይወስናል።

ለእናቶች ሞት የሚዳርጉ መንስኤዎች ምንድን ናቸው?

አብዛኛዎቹ የጤና ችግሮች በእርግዝና ወቅት የሚመጡ ሲሆኑ የቀሩት ከእርግዝና በፊት በነበሩ የጤና ችግሮች በእርግዝናው ምክንያት በመባባሳቸው የሚመጡ ናቸው።

ከባድ የደም መፍሰስ (በአብዛኛው ከወሊድ በኋላ የሚፈሰው ደም) ፣ በእርግዝና ወቅት የደም ግፊት መጨመር (pre-eclampsia and eclampsia) ፣ ኢንፌክሽን (sepsis) ፣ ከባድ ምጥ (Obstructed labour) እንዲሁም ከጤና ተቋም ውጪ ፣ ብቁ ባልሆኑ ባለሙያዎች እና በህክምና መሳርያ ያልታገዘ ውርጃ (Unsafe abortion) ለእናቶች ህይወት ማለፍ ዋነኛ መንስኤ ተደርገው ይወሰዳሉ።

የህክምና አገልግሎትን ለማግኘት ውሳኔን ማዘግየት ፣ ወደ ህክምና ተቋም ለመድረስ መዘግየት እና የጤና ተቋም ከደረሱ በኋላ አስፈላጊውን የህክምና አገልግሎት ሳያገኙ መዘግየት የእናቶችን ሞት የሚያስከትሉ ሶስቱ የመዘግየት ሞዴል (The Three Delays Model) በመባል ይታወቃሉ።

የእናቶች ሞት መጠን በእናቶች የእድሜ ክልል ይለያያል። በ 10 – 14 እድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ወጣት ልጃገረዶች በእርግዝና እና ወሊድ ምክንያት ከሌሎች የእድሜ ክልሎች በበለጠ ለሞት ይዳረጋሉ።

የእናቶችን ሞት እንዴት ማስቀረት እንችላለን?

. የአለም ጤና ድርጅት እንደሚያመለክተው የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት የእናቶችን ሞት በመቀነስ ዙሪያ ጉልህ ሚና ይጫወታል። ይህም ያልተፈለገ እርግዝናን በማስቀረት ከእርግዝና  እና      ውርጃ ጋር ተያይዞ የሚከሰተውን የእናቶችን ሞት ይቀንሳል። የአፍላ እድሜን እርግዝና በማዘግየት የወጣት ልጃገረድን ህይወት ይታደጋል። በተጨማሪም የልጆቻቸውን ቁጥር፣ መች እና     በምን ያህል ርቀት እንደሚወልዱ ለማቀድ ያስችላል።

. የቅድመ ወሊድ ክትትል አገልግሎት ጤናማ የእርግዝና ጊዜን ለማሳለፍ ሌላኛው መፍትሄ ነው።

. የቅድመ ወሊድ ክትትል አገልግሎት ብቻውን በቂ አይሆንም። የእናቶችን ሞት ለመቀነስ ጤናማ የእርግዝና ጊዜ ማሳለፍ አስፈላጊ እንደሆነ ሁሉ በወሊድ ወቅትም በጤና ተቋም ብቁ ባለሙያ ባለበት መሆኑ አስፈላጊ ነው።

በሀገራችንም ባለፉት 15 አመታት ውስጥ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት የሚጠቀሙ እናቶች መጠን በ27% ፣ የቅድመ ወሊድ ክትትል ያላቸው በ56% እንዲሁም በጤና ተቋም የወሊድ አገልግሎት ያገኙ በ22% መሻሻል አሳይቷል።

ከ1990 – 2015 የእናቶች ሞት መጠን ለውጥ ቢያሳይም አጥጋቢ አልነበረም። ውጤቱም ኢትዮጵያ ከምዕተ አመቱ የልማት ግቦች (MDGs) ጋር በተያያዘ ከታቀደው በታች መሆኑን ያሳያል።

በ2030ም EPMM (Ending Preventable Maternal Mortality) በእያንዳንዱ ሀገራት የሚከሰተውን የእናቶችን ሞት ቢያንስ በሁለት ሶስተኛ (2010ን መነሻ በማድረግ) ለመቀነስ ግብ አስቀምጧል።

 

ማጣቀሻ

  1. Ethiopian Public Health Institute (EPHI) and ICF. 2021. Ethiopia Mini Demographic and Health Survey 2019: Final Report. Rockville, Maryland, USA: EPHI and ICF.
  2. Organization WH. 2015. Strategies towards ending preventable maternal mortality (EPMM).
  3. Organization WH. 2019. Trends in maternal mortality 2000 to 2017: estimates by WHO, UNICEF, UNFPA, World Bank Group and the United Nations Population Division.
  4. Say L, Chou D, Gemmill A, Tunçalp Ö, Moller A-B, Daniels J, et al. 2014. Global causes of maternal death: a WHO systematic analysis. The Lancet global health. 2(6):e323-e33.
  5. Tessema GA, Laurence CO, Melaku YA, Misganaw A, Woldie SA, Hiruye A, et al. 2017. Trends and causes of maternal mortality in Ethiopia during 1990–2013: findings from the Global Burden of Diseases study 2013. BMC public health. 17(1):1-8.

ይህ ፅሁፍ በዶ/ር ዳዊት ወርቁ (የማህፀንና ፅንስ ስፔሻሊስ/የማህፀን ካንሰር ሰብ ስፔሻሊስት) እና የጤና ወግ ኤዲተሮች የተገመገመ ነው።