(በፍሰሀ ሙሉጌታ Myungsung Medical college የህክምና ተማሪ-C1)

የመጀመሪያዎቹ 1000 የህይወት ቀናት ማለት በሴት ልጅ እርግዝና እና በልጇ ሁለተኛ    ልደት መካከል ያሉት ቀናቶች ናቸው፡፡   ይህም ጊዜ  ለሙሉ ጤና እና እድገት መሠረት  የሆነ   ነው።          በዚህ ጊዜ ውስጥ የልጁ አመጋገብ እና እንክብካቤ ህይወቱን ጤናውን ለመጠበቅ ብቻ ሳይሆን በልጁ  እድገት እና የመማር ችሎታ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራል፡፡ በዚህ ጊዜ አእምሯችን ከሌሎች ዕድሜ ክልሎች በበለጠ ፍጥነት ያድጋል። ስለዚህ ለልጁ ተገቢውን ንጥረ ነገር መመገብ በጣም አስፈላጊ ነው::

የመጀመሪያዎቹ 1000 ቀናት በ 3 ይከፋላሉ:-

1. የእርግዝና ጊዜ (0-9 ወር)

2. Infant (0-1 አመት)

3. Toddler (1-2 አመት)

1,የእርግዝና ጊዜ (0-9 ወር)

በእርግዝና ወቅት አዕምሮ በፍጥነት ማደግ ይጀምራል:: በእርግዝና የመጀመሪያ ወር መጨረሻ ላይ ፅንሱ 10,000 ነርቮች እንዳሉት ይገመታል፣በ 6ተኛው ወር መጨረሻ 10 ሚሊዮን ይደርሳል።፡ በዚህ ጊዜ ፅንሱ ከእናቱ የሚያገኘው ንጥረ ነገሮች  ነርቮቹን የመፍጠር ሂደት ላይ ትልቅ ሚና ይጫወታሉ፡፡ በዋነኝነት  አይረን፣ፕሮቲን፣ኮፐር፣ ፎሌት፣ ዚንክ ፣ አዮዲን እና ቅባቶች ናቸው፡፡ እነዚህንም ለማግኘት የሚከተሉትን ምግቦች ቢመገቡ ይመረጣል፡-

1. አትክልቶች እና ፍራፍሬዎች

2. ሥጋ

3. ምስር

4. አቮካዶ

5. የዱባ ፍሬ

6. የወተት ምርቶች

7. ስፒናች

8. ሰላጣ

9. ስኳር ድንች

በተቃራኒው እርግዝና ወቅት ከሚከተሉት ምግቦች መራቅ ይመከራል:-

1. ቱና እና ማርሊንን ጨምሮ ከፍተኛ የሜርኩሪ ዓሳን ያስወግዱ።

2. ያልበሰል ስጋ፣እንቁላል

3. ምንም እንኳን ጉበት ስጋ ጥሩ የቫይታሚን ኤ፣ቫይታሚን ቢ12፣ እና ፎሌት ምንጭ ነገር ግን ከመጠን በላይ ቫይታሚን ኤ መመገብ ፅንሱን ሊጎዳ ይችላል። ስለዚህ የሚበላውን መጠን ይገድቡ ፡፡

4.ፍራፍሬዎችና አትክልቶች ቶክሶፕላዝሞሲስ በተባሉ ተውሳኮች ሊበከሉ ይችላሉ፡፡ ሁሉንም ፍራፍሬዎችን እና አትክልቶችን በንጹህ ውሃ ማጠብ አስፈላጊ ነው፡፡

5. ሁሉንም የአልኮል ዓይነት ያስወግዱ፡፡ አልኮል መጠጣት የፅንስ መጨንገፍ እና የአእምሮ ዘገምተኝነትን ያስከትላል፡፡

2, Infant (0-1 አመት)

ሕፃን ልጅ ከተወለደበት ጊዜ አንስቶ እስከ አንድ አመት ድረስ ያለው ጊዜ ነው፡፡ ልክ በእርግዝና ጊዜ አመጋገብ ትልቅ ሚና እንደሚጫወተው በዚህም ጊዜ ወሳኝ ነው፡፡

ልጁ በዚህ ጊዜ ሊወስዳቸው ከሚገባቸው ምግቦች አንዱ እና ዋነኛው የጡት ወተት ነው፡፡ የአሜሪካ የሕፃናት ሕክምና ማህበር ለመጀመሪዎቹ 6 ወራት ጡት ማጥባት ብቻ ያለ ምንም ተጨማሪ ምግብ እና መጠጥ ይመከራል፡፡ ከዚያም በተጨማሪ ለ 1 አመት ያህል ከምግብ እና ፈሳሽ ጋር ጡት ማጥባት ተገቢ ነው፡፡  በቀን እስከ 20 ጊዜ ጠዋት እና ማታ ያጥቡ፡፡

 

ጡት ማጥባት ህፃኑን ብቻ ሳይሆን የሚጠቅመው እናቶችንም ከጡት እና ከማህፀን ካንሰር ለመከላከል ይረዳል፡፡

ምግብ ሲጀምሩ የሚከተሉትን ነገሮች አስተውሉ፡-

1. በመጀመሪያ አንደኛውን ጡት ሙሉ በሙሉ ባዶ ማድረግ ከዚያም ወደሌላኛው ጡት ይሂዱ። ይሄ ህፃኑ የሚቻለውን ያህል ንጥረነገር እንዲያገኝ ያግዛል፡፡

2. ልጅዎ ቢታመም በቀን የሚጠባበትን ቁጥር ይጨምሩ፡፡

3. ከወሊድ በኋላ ባሉት 45 ቀናት ውስጥ የቫይታሚን ኤ ታብሌቶች ወይም ምግቦችን ይውሰዱ፡፡

4. ልጅዎን በቀን ከ20-30 ደቂቃዎች የፀሀይ ብርሀን ያሙቁ፡፡

5. ምግብ በሚጀምሩበት ጊዜ ለልጅዎ በአንድ ጊዜ አንድ አዲስ ምግብ ብቻ ይስጡት – ድብልቅ ሳይሆን (እንደ ጥራጥሬ እና ፍራፍሬ ወይም ስጋ)። ሌላ አዲስ  ምግብ ከመጨመርዎ በፊት አዲሱን ምግብ ከ 3 እስከ 5 ቀናት በተከታታይ ይስጡት፡፡ በዚህ መንገድ ልጅዎ ለምን አይነት ምግቦች አለርጂክ ሊሆኑ እንደሚችሉ ማወቅ ይችላሉ።

6. በትንሽ መጠን አዲስ ምግብ ይጀምሩ – መጀመሪያ ላይ አንድ የሻይ ማንኪያ እና ቀስ በቀስ ወደ አንድ የሾርባ ማንኪያ ከፍ ያድርጉ።

7. በደረቅ የሩዝ እህል ይጀምሩ ከዛ አትክልቶች ፣ ፍራፍሬዎች እና ከዚያም ስጋዎች ይመገቡ፡፡

8. በቤት ውስጥ የተሰሩ የህጻናት ምግቦችን በምታዘጋጁበት ጊዜ ጨው ወይም ስኳርን አይጠቀሙ፡፡ የታሸጉ ምግቦች ከፍተኛ መጠን ያለው ጨው እና ስኳር ሊይዙ ስለሚችሉ ለህጻናት ምግብ መዋል የለባቸውም። ለተገቢ ያልሆነ ውፍረት ያጋልጣሉ፡፡

9. የላም ወተት ከ1 አመት በፊት መጀመር የለበትም፡፡

10. ሁልጊዜ ፍራፍሬዎችን እና አትክልቶችን ይጠቡ፣ ይላጡ እና ፍሬውን ያስወግዱ።

11. ከመሬት ጋር የሚገናኙ ፍራፍሬዎች፣ አትክልቶች እና ማር ላይ ልዩ ጥንቃቄ ያድርጉ፡፡ የምግብ መመረዝን የሚያስከትሉ የ ቦቱሊዝም(botulism) ንጥረ ነገሮችን ሊይዙ ይችላሉ፡፡ እስከ 1 አመት ድረስ ልጆች ማር መመገብ የለባቸውም፡፡

 

3,Toddler (1-2 አመት)

ህፃናት ልጆች እንዲያድጉ እና ተገቢ የሆነ የክብደት መጠን እንዲያገኙ  በፕሮቲን የበለጸጉ ምግቦችን ፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ስንዴ፣ ስኳር የሌለው ወተት እና ሌሎች የወተት ተዋጽኦዎች ያስፈልጋቸዋል፡፡ በዚህ ጊዜ የቅባት እና የስኳር መጠንን መመጠን አስፈላጊ ነው፡፡ የክብደት መጠን መጨመር በወደፊት ህይወት ላይ ለአላስፈላጊ በሽታዎች ይዳርጋል፡፡

የልጆች ባህሪን ለመቆጣጠር ምግብን ከመጠቀም ይልቅ የራሳቸውን ምግብ መጠን እንዲቆጣጠሩ መፍቀድ ይመከራል። ልጆች ወላጆቻቸውን እና ሞግዚታቸውን ይመለከታሉ፡፡ ስለዚህ አንድ ወላጅ ጤናማ ምግብ ሲመገብ ልጆቹም እንዲመገቡ ያነሳሳቸዋል።

ልጅዎ በቀን ግማሽ ሊትር ወተት ማግኘት አለበት፡፡ ይህም በቂ ካልሺየም፣ ቫይታሚን ዲ እና ስብ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል፡፡

1. ልጅዎ ከሁሉም የምግብ ዓይነቶች ማለትም ከአትክልቶች፣ ፍራፍሬዎች፣ ፕሮቲኖች፣ ጥራጥሬዎች እና የወተት ተዋጽኦዎች ምግብ ማግኘት አለበት።

2. ልጅዎን ጡጦ ሳይሆን ኩባያ እንዲጠቀም ያበረታቱት።

3. ሹካ/ማንኪያ መጠቀምን ጨምሮ የጠረጴዛ ስነምግባርን ማስተማር መጀምር

4. ታገሱ! ህፃናት አንድን ነገር አንድ ቀን መውደድ እና በሚቀጥለው ጊዜ መብላት እንደማይፈልጉ በመወሰን መራጭ ተመጋቢዎች ሊሆኑ ይችላሉ። ከሁሉም     ምግቦች ትንሽ ክፍሎች ያቅርቡ እና የምግብ ሰዓቱን አስደሳች ያድርጉት! የተለያየ ጣዕም ያላቸው ባለቀለም ምግቦችን ያቅርቡ። ዛሬ ምግብን እምቢ ቢሉም     ማገልገልዎን ይቀጥሉ እና እንዲሞክሩ ያበረታቷቸው፤ነገር ግን እንዲበሉ አያስገድዷቸው፡፡

5. መላው ቤተሰብ አንድ ላይ ቢመገብ ፤አንድ አይነት ምግብ ይመገቡ፤ በዚህ ተነሳስቶ ህጻኑም ተመሳሳይ ምግብ ይመገባል፡፡

6. ለልጅዎ በቀን ሶስት መደበኛ ምግቦች እና 2 መክሰስ ያቅርቡ፡፡

References

1. American Academy of Pediatrics

2. NUTRITION IN THE FIRST 1,000 DAYS: A Foundation for Brain Development and Learning. (n.d.).     Retrieved from https://thousanddays.org/.

3. Health, F. D. (2006). Complementary Feeding Recipes for Ethiopian Children 6-23 Months Old.

  • https://www.stanfordchildrens.org/en/topic/default?id=feeding-guide-for-the-first-year-90-P02209. (n.d.). Retrieved from https://www.stanfordchildrens.org.

 

ይህ ፅሁፍ በዶ/ር ትንሳኤ አለማየሁ (የህፃናት ህክምና ስፔሻሊስት/የተላላፊ በሽታዎች ሰብ ስፔሻሊስት) እና የጤና ወግ ኤዲተሮች የተገመገመ ነው።