የህፃናት ዓይነት አንድ የስኳር ህመም| Type 1 Diabetes in Children

Written by Dr. Melika Bedru (GP)

Reviewed by Dr. Wuhib Zenebe

“ዶ/ር ምን ምን ባደርግ የስኳር ህመሜ ሊጠፋልኝ ይችላል?” 

የ12 ዓመት ታካሚዬ የጠየቀኝ ጥያቄ ነበር። በሽታው ከታወቀለት እና ህክምና ከጀመረ 2 ዓመት የሚሆነው ይህ ታካሚዬ አንድ ነገር እንዳስተውል አደረገኝ። ስለ ህመሙ በቂ ግንዛቤ እንደሌለው ቤተሰቦቹም ቢሆኑ በመጠኑ እንጂ ጥልቅ የሆነ ግንዛቤ እንደሌላቸው ተረዳሁ። ስለዚህ ዓይነት አንድ የስኳር ህመም ምን ይመስላል የሚለውን በአጭሩ እንወቅ።

 የስኳር ህመም ምንድን ነው?

የስኳር ህመም ዓይነት አንድ የስኳር ህመም እና እና ዓይነት ሁለት የስኳር ህመም በመባል ጠቅለል ባለ መልኩ ይከፈላል ፤ ነገር ግን ይህ ፅሑፍ ዓይነት አንድ የስኳር ህመም ላይ ትኩረት አድርጎ የሚተነትን ይሆናል። ከምንመገበው ምግብ የምናገኘው ስኳር ተፈጭቶ ከተጣራ በኋላ ወደ ደም ስር ይተላለፋል። ከደም ስር ደግሞ ኢንሱሊን (Insulin) በተባለ ተቆጣጣሪ ንጥረ ነገር (Hormone) አማካኝነት ወደ ሕዋሶች ይገባል። እነዚህን ኢንሱሊኖች የሚያመርተው በቆሽት ውስጥ የሚገኝ ‘ቤታ ሴል’ (Beta cell) የሚባል ሕዋስ ነው። ይህ ስኳር በሕዋሶች ውስጥ ከገባ በኋላ ለሰውነት ዋናውን ሀይል ማመንጨት ይጀምራል።ስለዚህ ሰውነታችን ስኳርን (Glucose) እንዴት መጠቀም እንዳለበት የሚያዛባ ወይም የሚያውክ የበሽታ ዓይነት የስኳር ህመም ይባላል። 

ዓይነት አንድ የስኳር ህመም አንዱ የስኳር ህመም አይነት ሲሆን በህፃናት ላይ በአብዛኛው የሚከሰት ነው። ይህ የስኳር ህመም ኮሽት (Pancreas) ማምረት የሚገባው የኢንሱሊን (Insulin) መጠን ዝቅተኛ መሆን ወይም አለመኖር ከ’ቤታ ሴል’ ውድመት ጋር ተያይዞ ሲመጣ የሚከሰት ነው። ይህ የኢንሱሊን እጥረት ወይም አለመኖር በደም ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን እንዲጨምር ያደርገዋል ፤ ምክንያቱም የኢንሱሊን ስራ ወደ ሕዋሶች ስኳርን ለማስገባት እንደ በር ቁልፍ ማገልገል ስለሆነ ነው።

 ምክንያቱስ ምን ይሆን?

የስኳር ህመም በዚህ ምክንያት ነው የሚከሰተው ብሎ በእርግጠኝነት መናገር ባይቻልም ይህ በሽታ እንዲከሰት መንስኤ ሊሆኑ የሚችሉ ሁኔታዎች ይኖራሉ። አብዛኛውን ጊዜ የዘረመል ተጋላጭነት እና የአካባቢ ሁኔታዎች ጋር ቁርኝት አንዳለ ጥናቶች ያመላክታሉ። ዓይነት አንድ የስኳር ህመም በህፃናት ላይ ከቅርብ የቤተሰብ አባላት በዘር የመወረስ ሁኔታው በጣም አነስተኛ ነው። 85% የዚህ በሽታ ተጠቂዎች ሁኔታ ከዘር መወረስ ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር የለም። የአካባቢ ሁኔታዎችን ስናይ ደግሞ በተለያዩ ቫይረሶች መጠቃት ፣ ከአንድ አመት በታች ለሆኑ ህፃናት የላም ወተት ማስጀመር ፣ የቫይታሚን D ፣ ቫይታሚን C ፣ ቫይታሚን E እና ኦሜጋ 3(Omega 3) እጥረት ህፃናት ለዓይነት አንድ የስኳር ህመም ተጋላጭ እንዲሆኑ ያደርጋል።

ህፃናት ላይ የትኛው የእድሜ ክልል ዉስጥ ሊከሰት ይችላል?

በየትኛውም የእድሜ ክልል ውስጥ ሊከሰት ይችላል ፤ ነገር ግን ህፃናት ላይ በአብዛኛው ከ5-7 አመት እና በጉርምስና እድሜ ላይ ነው የሚከሰተው። ከ 5-7 ባለው የእድሜ ክልል ውስጥ ህፃናት ትምህርት ቤት የሚጀምሩበት ጊዜ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ለተለያዩ ተላላፊ በሽታዎች (በቫይረሶች መጠቃትን ጨምሮ) ተጋላጭ ስለሚሆኑ ነው። በጉርምስና እድሜ ደግሞ ከፍተኛ የሰውነት እድገት በሚኖርበት ጊዜ ይህንን አድገት ለማገዝ የሚመነጩ ሆርሞኖች የኢንሱሊንን ስራ በተቃራኒው ሊያዛቡ ይችላሉ። ነገር ግን እነዚህ ሁሉ ሁኔታዎች የዘረመል ተጋላጭነት ያላቸው ህፃናት ላይ ነው ጉዳት የሚያደርሱት።

ምልክቶቹ ምንድን ናቸው?

  1. ቶሎ ቶሎ ሽንት መሽናት – ይህም የሚከሰተው ሰውነት ውስጥ ያለው የስኳር መጠን ከመጠን በላይ በመሆኑ ከሰውነት ውስጥ እንዲወገድ ኩላሊታችን በሽንት መልክ ያስወጣዋል።
  2. ቶሎ ቶሎ ውሃ መጠጣት – ብዙ ሽንት ስለሚወጣ የወጣውን ለመተካት ቶሎ ቶሎ የውሃ ጥማት ይኖራል።
  3. በየጊዜው መብላት መፈለግ – ሰውነት ከስኳር ያገኝ የነበረውን ሀይል በማጣቱ ቶሎ ቶሎ ረሀብ ስሜት እንዲሰማቸው እና እንዲበሉ ያደርጋቸዋል።
  4. ክብደት መቀነስ – የሚበሉት መጠን እና የሚበሉት ጊዜ ቢጨምርም ካላቸው የሰውነት ክብደት ግን ቢያንስ 10% ይቀንሳሉ። ይህም የሚሆንበት ምክንያት ሰውነት ካገኘው ምግብ ስኳርን እንደ ሀይል ምንጭ መጠቀም ባለመቻሉ ያለውን ስብ እና ጡንቻ እንደ ሀይል ይጠቀምባቸዋል። ስለዚህ ጥሩ የምግብ ፍላጎት ቢኖራቸውም ይከሳሉ ማለት ነው። 
  5. የድካም ስሜት – ሰውነት ስኳርን እንደ ሀይል ምንጭ መጠቀም ባለመቻሉ ቶሎ የመድከም ስሜት እንዲኖራቸው ያደርጋል።
  6. ለሊት በእንቅልፍ ሰዓት ሽንት እራስ ላይ መልቀቅ ወይም ለሊት ለሽንት ያለወትሮ በተደጋጋሚ መነሳት

ከ20-40% የሚሆኑ አዲስ የዓይነት አንድ ስኳር ህመም ተጠቂ ህፃናት የሚያሳዩት ምልክቶች ከዳያቤቲክ ኬቶ አሲዶሲስ (Diabetic ketoacidosis) ጋር የሚያያዝ ነው። ዳያቤቲክ ኬቶ አሲዶሲስ (DKA) ማለት በስኳር ህመም ምክንያት የሚመጣ ተጨማሪ በሽታ ሲሆን የሚከሰተው በሰውነት ውስጥ በቂ ኢንሱሊን ባለመኖሩ እና በደም ውስጥ የሚኖረው የስኳር መጠን ሲጨምር የሰውነት ህዋሶች ሀይል ለማመንጨት መጠቀም ስለማይችሉ በምትኩ ጉበት ለሀይል ማመንጨት ስብን ያቃጥላል፣ ይህ ሂደት ኬቶን የተባለ አሲድ ያመነጫል። ብዙ ኬቶኖች በጣም በፍጥነት በሚመረቱበት ጊዜ በሰውነት ውስጥ በአደገኛ ደረጃ ሊጨምሩ እና ሊከማቹ ይችላሉ። ይህ በሰውነት ውስጥ ከፍተኛ የኬቶን ክምችት የተለያዩ ምልክቶችን ሊያሳይ ይችላል። እነሱም ፦

  1. ራስን መሳት ወይም ኮማ ውስጥ መግባት

 

  1.  ቶሎ ቶሎ እና በጥልቅ መተንፈስ (Kussmaul Breathing)

 

  1. የሆድ ህመም 

 

  1. ማቅለሽለሽ እና ማስታወክ

 

  1. ከፍተኛ ድክመት ስሜት እና እንቅልፍ እንቅልፍ አይነት ስሜት

የስኳር በሽታ መሆኑን በምን ማወቅ ይቻላል?

ህፃናት ከላይ የተዘረዘሩትን ምልክቶች ኖረዋቸው ወደ ህክምና በሚመጡት ሰዓት የላቦራቶሪ ምርመራ ተደርጎ ህመሙ የስኳር በሽታ መሆኑን ማረጋገጥ ይቻላል። ይህም በደም ውስጥ የሚገኘውን የደም መጠን በመለካት ነው። ይህ የሚለካው ጠዋት ከቁርስ በፊት የደም ስኳር መጠን (Fasting Blood Sugar) ከ126mg/dl በላይ ሲሆን ወይም ከምግብ በኋላ የደም ስኳር መጠን (Random Blood Sugar) ከ200mg/dl በላይ ሲሆን አንድ ህፃን የስኳር በሽታ አለው ማለት ነው። ሌላኛው መለኪያ ደግሞ Hemoglobin A1c የሚባል ያለፈውን የሶስት ወር የደም ስኳር መጠን የሚለካ የምርመራ አይነት ሲሆን መጠኑ ከ6.5% በላይ ሲሆን የስኳር በሽታ መኖሩን ያመለክታል። ሌሎች ተጨማሪ ምርመራዎች ተጓዳኝ እና ተዛማጅ በሽታዎች መኖር አለመኖራቸውን የሚለዩልን ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ አንድ ህፃን በኬቶ አሲዶሲስ መጠቃቱ የሚታወቀው በሽንት ምርመራ የኬቶን መጠን ከመሀከለኛ እስከ ከፍተኛ ደረጃ ሲጨምር ነው። ይህ የኬቶን መጨመር ደግሞ የሰውነት አሲድ መጠን እንዲጨምር ያደርጋል። 

ህክምናው ምን ይመስላል?

የህክምናው ዋናው አላማ ከበሽታው ለመፈወስ ወይም ሙሉ ለሙሉ ለማዳን ሳይሆን በሽታው የሚያስከትለውን ችግር ለመቆጣጠር እና ለመቀነስ ነው። የአኗኗር ዘይቤ እንዲስተካከል እና ህፃናት ከጓደኞቻቸው እኩል ተጫውተው ተዝናንተው እንዲኖሩ ነው። የህክምናው ሂደት ከወላጆች እና ቤተሰብ ጋር በደንብ በግልፅ በመወያየት መጀመር ያለበት ሲሆን ሐኪም በወሰነው ጊዜ ቋሚ ክትትል የሚደረግ ይሆናል።

 ህክምናው የሚያካትተው ፦

  1. የአመጋገብ ስርዓትን ማስተካከል – ማንኛውንም ጣፋጭ ነገር መውሰድ ይከለከላል ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ በሚወሰደው መድሃኒት ምክንያት በደም ውስጥ ያለው ስኳር ሊያንስ ይችላል። በዚህን ጊዜ ስኳር ያለው ነገር መውሰድ አግባብ አለው። ጣፋጭ ሲባል እንደ ከረሜላ ፣  ቸኮሌት ፣ ለስላሳ መጠጦች ፣ ጁስ ፣ ስኳር የመሳሰሉት ናቸው። ከመደበኛ መመገቢያ ሰዓት በተጨማሪ ቀለል ያሉ ምግቦችን መውሰድም ይኖርባቸዋል። በተለይ የኢንሱሊን መድሃኒት የሚወስዱ ህፃናት በደማቸው ውስጥ ያለው የስኳር መጠን ስለሚቀንስ ምግብ የምንሰጣቸው ጊዜያትን በመጨመር በመቀነሱ ምክንያት የሚመጣውን ጉዳት እንከላከላለን።
  2. የኢንሱሊን ህክምና – ይህ ሰውነት የሚያመርተው የኢንሱሊን መጠን ዝቅተኛ በመሆኑ ከሰውነት ውጪ በተዘጋጀ መልኩ በመርፌ የሚወሰድ መድሃኒት ነው። በክብደት እና በአስፈላጊነት ደረጃው ተሰልቶ ይሰጣል። መርፌውን መውጋት ለቤተሰብ እና ለእራሳቸው ታካሚዎች በማሳየት ማስለመድ ያስፈልጋል። ስለ ኢንሱሊን አቀማመጥ እና አወሳሰድ በቂ ግንዛቤ መስጠትም ተገቢ ነው።
  3. የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ- መደበኛ የአካል እንቅስቃሴ ማድረግ በደም ውስጥ የሚገኘውን የስኳር መጠን እንዲስተካከል እና የሰውነት ጡንቻዎች እና አጥንቶች እንዲጠነክሩ ያደርጋል።
  4. የደም ውስጥ የስኳር መጠን መቆጣጠር – በአግባቡ ክትትል በመሄድ እና በመለካት ወይም አቅም ካለ የስኳር መለኪያ መሳሪያ በመግዛት ቤት ውስጥ በአግባቡ መለካት እና መመዝገብ። 

ከዓይነት አንድ ስኳር በሽታ ጋር የተዛመዱ ችግሮች ምንድን ናቸው?

መድሃኒቶችን በአግባቡ አለመውሰድ ፣ አመጋገብን አለማስተካከል እና ለኢንፌክሽኖች መጋለጥ እነዚህ ተዛማጅ ችግሮች  አንዲከሰቱ ያደርጋሉ። እነዚህ ተዛማጅ ችግሮች አጣዳፊ (Acute) እና ስር የሰደደ (Chronic) በሚል ይከፈላሉ።

አጣዳፊ የምንላቸው ችግሮች የደም ስኳር መጠን በጣም ሲቀንስ (Hypoglycemia) ወይም ከመጠን በላይ ሲጨምር (Hyperglycemia) የሚከሰቱ ናቸው።

ስር የሰደዱ ችግሮች ደግሞ የሚከተሉት ናቸው ፦

– የደም ስር እና የልብ ህመም 

– የነርቭ መጎዳት (Neuropathy)

– የኩላሊት መጎዳት (Nephropathy)

– የዓይን ጉዳት (Retinopathy)

– የእግር መጎዳት

– የቆዳ እና የአፍ በሽታዎች 

– የመስማት ችግር

– የመርሳት በሽታ (Alzhiemer’s Disease)

መከላከል ይቻል ይሆን?

ዓይነት አንድ የስኳር ህመም ህፃናት ላይ እንዳይከሰት ማድረግ አስቸጋሪ ቢሆንም አንዳንድ ልማዶችን በማስተካከል በተወሰነ ሁኔታ ልንከላከል እንችል ይሆናል። 

  1. የላም ወተት ከአንድ አመት በታች ለሆኑ ህፃናት በተቻለ መጠን አለመስጠት እና ጡት የሚጠባበትን ጊዜ ማርዘም ማለትም እስከ ሁለት አመቱ ድረስ። 
  2. የቫይታሚን ዲ (Vitamin D) እጥረት እንዳይኖር በአግባቡ ፀሐይ ማስሞቅ።
  3. ከ6ወር እድሜያቸው ጀምሮ ተጨማሪ የሚወስዷቸው ምግቦች  በቂ እና የተመጣጠነ የቫይታሚን ኢ ፣ ቫይታሚን ሲ እና የኦሜጋ 3 ንጥረ ነገሮች እንዲኖራቸው ማድረግ።

Key Words 

  1. ዓይነት ሁለት የስኳር ህም
  2. የቫይታሚን ዲ (Vitamin D) እጥረት
  3. አጣዳፊ (Acute) ተዛማጅ ችግሮች

     4.ስር የሰደዱ (Chronic) ተዛማጅ ችግሮች

  1. የቫይታሚን ሲ (Vitamin C) አና የቫይታሚን ኢ (Vitamin E) እጥረት

 

የጤና ወግ 

ጠቃሚ እና የተረጋገጠ መረጃ ለጤናዎ ።

የጤና ወግን በነዚህ ሊንኮች መከታትል ይችላሉ ።

https://linktr.ee/Yetena_Weg